1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የባህል ቅኝት በተሰናባቹ 2016

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 20 2009

የዓመቱን የአዉሮጳ ማዕከል በማስተዋወቅ የጀመረዉ  የጎርጎርዮሱ 2016 ኢህአዴግ ሥልጣን የያዘበትን 25 ዓመት በተመለከተ በመንግሥታት ለዉጦች በተለይ በአማርኛ ቋንቋ ላይ ያሳደረዉን ተጽኖ  የቃኘንበት ፤ የሰማዕቱ ብፁዕ አባታችን አቡነ ጴጥሮስ በቀደመ መካናቸው መመለስ ጎልተዉ ከወጡ ዝግጅቶች ነበሩ።

https://p.dw.com/p/2V1bv
Abune Petros Denkmal Addis Abeba
ምስል DW/A. Desalegn

«ትግሌ» ሂስ የታከለበት ህትመት

 

 

የአዉሮጳ ኅብረት ዓባል ሃገራት ባህላቸዉን እንዲተዋወቁ ብሎም ለዓለም እንዲያሳዉቁ በሚል የኅብረቱ ዓባል ሃገራት ከጎርጎረሳዉያኑ 1985 ዓ,ም ጀምሮ የአንድ ሃገር ከተማን በመምረጥ የዓመቱ የባህል ከተማ ሲሉ ያስተዋዉቃሉ። በርግጥ የአዉሮጳ ኅብረት ከ 17 ዓመት ወዲህ የባህል ከተሞች ሲል በዓመት ሁለት የአባል ሃገራቱን ከተሞች በመሰየም በከተሞች ዉስጥ የሚታዩት የተለያዩ ባህሎች ታሪክ ቋንቋና አኗኗን በአዲስ ማስተዋወቁን መጀመሩም ይታወቃል።

በጎርጎረሳዉያኑ 2015 ዓ,ም የቤልጂሟ ሞንስ ከተማና የቼክ ሪፐብሊኳ ፒልስን ከተማ፤ ዓመቱን ሙሉ የተለያዩ ዝግጅቶችን በማቅረብ ፤ በከተሞቻቸዉ ዉስጥ የሚታዩትን የተለያዩ ባህልና አኗኗር በመተረክ፤ ዓዉደ ርዕዮችን በመዘርጋት ታሪክን በማሳየት ከአዉሮጳ ብሎም ከዓለም ሃገራት ነዋሪዎችን ጎብኝዎችን ራሳቸዉን አስተዋዉቀዋል። ዘንድሮ የአዉሮጳ የባህል ማዕከል ተብለዉ ከተሰየሙት ሁለት የአዉሮጳ ሃገራት ከተሞች መካከል በፖላንድዋ ብሪስላዉ ፖላንድ ከሦስት አስርተ ዓመታት በላይ ነዋሪ የሆኑት ኢትዮጵያዊዉ አቶ መርሻ ወልዴ በተሰናባቹ የጎርጎረሳዉያን ዓመት የአዉሮጳ የባህል ማዕከል ሆና ዓመቱን የዘለቀችዉ ብሪስላዉ ከተማ አጠገብ ነዋሪ ናቸዉ። አቶመርሻ ፖላንዳዉያን እንደ ኢትዮጵያዉያን ሁሉ እንግዳ ተቀባዮች ናቸዉ ሲሉ ነግረዉናል። በጎርጎረሳዉያኑ 2004 ዓ,ም የአዉሮጳን ኅብረት በተቀላቀለችዉ ፖላንድ የኢትዮጵያዉያን ቁጥር ጥቂት መሆኑንም  አቶ መርሻ ወልዴ ተናግረዋል። ደቡባዊ ምዕራብ ፖላንድዋ ዉስጥ የምትገኘዉ የዘንድሮዋ አንዷ የአዉሮጳ የባህል ማዕከል ብሪስላዉ 600 ሺህ ነዋሪዎችም አልዋት። ከቼክ ሪፐብሊክ የሚፈልቀና ፖላንድና ጀርመንን በድንበር የሚከፍለዉ የኦደር ወንዝን ተቀብላ ወዳ ባልቲክ ባህርም ትሸኛለች። 

Deutschland Mein Kampf
ምስል picture alliance/AP Photo/M. Schrader

ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1933ዓ,ም እስከ 1945 ጀርመንን የገዛዉ አምባገነን መሪ የግዛቱን ሥርዓት በተመለከተ አሳትሞት የነበረዉ መጽሐፍ ከሞተ ከ 70 ዓመታት በኋላ ከምሑራን ትችትና ማብራርያ ትግሌ በሚል ስያሜ ጋር ዳግም ለአንባብያን መቅረቡ በዚሁ በተሰናባቹ የጎርጎረሳዉያን ዓመት መጀመርያ ላይ የበጀርመን የነበረ አንድ ትልቅ ክስተት ነበር። እንዳይታተም ታግዶ የነበረዉና በጀርመንኛ ስያሚ «ማይን ካንፍ » ሲተረጎም «ትግሌ» የሚል ርዕሥን የያዘዉ ይህ መጽሐፍ የበርካታ አንባብያንን ትኩረት የሳበና በዓመት ዉስጥ ለተደጋጋሚ ጊዜ የታተመ መጽሐፍ ሆንዋል። የዚህ መጽሐፍ ይዘት ምን ይሆን? ከርዕሱ ጀምሮ እንዲያስረዱን በጀርመን ታዋቂ የሆኑት ደራሲና የታሪክ ምሁር እንዲሁም የአፍሪቃና መካከለኛዉ ምስራቅ ጉዳዮች አማካሪ ልጅ ዶክተር አስፋወሰን አስራተን ጠይቀናቸዉ ነበር። 

«አዋጅ አዋጅ አዋጅ ጥር 29 ቀን 2008 ዓ.ም  ሰምዓቱ ብፁዕ አባታችን አቡነ ጴጥሮስ በቀደመ መካናቸው ላይ በክብር ይመለሳሉና የአዲስ አበባ እና የአካባቢው ህዝብ በሆታ እና በአጀብ አክብር ተብለሀል! » ሲሉ ዜናዉን ያበሰሩን የዝግጅታችን ተከታታይ የፊልም ሥራ አዋቂዉ አቶ ያሪድ ሹመቴ ነበሩ። በአዲስ አበባ ከተማ ተጀመሮ በነበረዉ የቀላል ባቡር መሥመር ግንባታ ምክንያት ተነስቶ የነበረዉ የሰማዕቱና የአርበኛዉ የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሐዉልት ዳግም በቦታዉ መመለስ በርካታ ኢትዮጵያዉያንን በተለይ የመዲናዋን ነዋሪዎች አስፈንድቆአል፤ የባህል መድረካችንም ይህንኑ ደስታ በዚሁ በተሰናባቹ የጎርጎረሳዉያን 2016 ዓ,ም ሁለተኛ ወር ላይ መሰናዶ በማቅረብ ተካፍሎአል። የዝግጅታችን የዘወትር ተከታታይና ተሳታፊ ታዋቂዉ ገጣሚ አበባዉ መላኩ የአቡነ ጴጥሮስ ሐዉልት ወደ ቦታዉ መመለስን በተመለከተ እንዲህ ነበር የገለፀልን።

 ዘንድሮ በፍቅረኛሞች ዘንድ ታስቦ የዋለዉን የፍቅረኛሞች ቀን ማለት « ቫለንታይን ዴይ » ን በማስመልከት የባህል መድረካችን በሃገራችን የሴቶች መብት ምን ያህል ይከበራል ሲል ጠይቆአል። በምዕራባዉያኑ ዘንድ በቀይ ጽጌረዳና ልብስ ደምቆ የሚታሰበዉ ይህ ቀን በሃገራችን በተለይ በከተሜዉ ወጣቶች ዘንድ እየተዘወተረ መጥቶአል። እና በሃገራችን ሴትች መብት ምን ያህል ይከበራል? የዝግጅታችን ተሳታፊና ጋዜጠኛ የትነበርክ ታደለ እንደ ገለፁልን ሴት ልጅ የሚገባትን መብት አግኝታለች የሚል እምነት እንደሌላቸዉ ነግረዋዉናል።

የሴቶችን መብት በተመለከተ መንግሥት ብዙ ሥራ ቢያከናዉንም ሕግጋትን ቢያወጣም የሴት እኩልነትን ማኅበረሰቡ ተግባራዊ እስኪያደርገዉ ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅበታል ሲሉ የገለፁልን በኢትዮጵያ የመጀመሪያዉን ጥቃት ለደረሰባቸዉ ሴቶች ቤት ያቋቋሙት ወ/ሮ ማሪያ ሙኒር ናቸዉ።

«BMW» በመባል የሚታወቀዉና በዓለም ከፍተኛ ቃዋቂነትና ተወዳጅነትን ያተረፈዉ የጀርመኑ የተሽከርካሪ ኩባንያ በዚሁ በተሰናባቹ 2016 ዓ,ም መጀመርያ ወራቶች ላይ የተመሠረተበትን 100 ኛ ዓመት በደማቅ አቅብሮአል። ድርጅቱ በጎርጎርዮሳዊ 1916 ዓ,ም መጋቢት ሰባት የባየር አዉሮፕላን ሞተር አምራች ኩባንያ ሆኖ ነበር የተመሰረተዉ።   መኪናን በጥራትና በጥንካሪ በማምረት ምልክትና ባህላቸዉ ያደረጉት ጀርመናዉያን ፤ ተሽከርካሪዎቻቸዉ ከዓለም ቀዳሚ ቦታን የያዘ ነዉ የሚገኙት ያሉን  በጀርመን የመኪና ኩባንያ ዉስጥ የሚያገለግሉት ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ፤ በጀርመን መኪና መመረት የተጀመረዉ ሲሉ እንዲህ አስረድተዋል።

ምንም እንኳ ኩባንያዉ በዓለም ዙርያን ተወዳጅነትና ታዋቂነት ያግኝ እንጅ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በፊት አምራች ኩባንያዉ አስገድዶ ሰራተኞችንና በናዚ ማጎርያ ጣብያ የሚገኙ ታሳሪዎችን ጉልበት በዝብዞአል የሚለዉ ጥናት ገሃድ መሆኑ ድርጅቱ ታሪክ ላይ ጥቁር የታሪክ ጠባሳን መጣሉ አልቀረም።

በአጼ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት በ1900 ዓ,ም ገደማ ፤ ጀርመናዊዉ ነጋዴ አርኖልድ ሆልዝ ወደ ኢትዮጵያ መኪና ማስገባቱን ሆኖም ግን ከዚህ ቀደም ሲል አጼ ምኒሊክ ከእንጊሊዝ አገር አንድ መኪና አስመጥተዉ እንደነበር ታሪክ ያሳየናል ያሉን፤ በመጀርመን የመንጃ ፈቃዳቸዉን የያዙት የመጀመርያዉ ኢትዮጵያዊ የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ የልጅ ልጅ አቶ ታደለ ይድነቃቸዉ ተሰማ እሸቴ ናቸዉ።

በዚሁ በሚጠናቀቀዉ የጎርጎረሳዉያኑ አመት ሕወሀት ኢህአዴግ ሀገሪቱን የተቆጣጠረበትን 25ኛ ዓመት ሲያከብር የአማርኛ ቋንቋ በመንግሥታት ለዉጥ በሚል የአማርናን ቋንቋ ከእንጊሊዘኛ ጋር የመደባለቅ አባዜ አሳሰቢነቱን፤ በአጠቃላይ የአማርኛ ቋንቋችን አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑን ምሁራን የገለፁበት ዝግጅትን ይዘን ቀርበን ነበር።

በደቡባዊ ጀርመን ባየር ግዛት በሙኒክ ከተማ በሚገኝ ዩንቨርስቲ በምርምር ሥራ ላይ የሚገኙት በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በጥንታዊ ጽሑፎች ጥናት ረዳት ፕሮፊሰር አምሳሉ ተፈራ የሰጡን አስተያየት አሳሳቢ የሆነዉ ይላሉ

የሃገራት መንግስታቶች ሲለዋወጡ ብቻ ሳይሆን በአንድ ሃገር በማንኛዉም ጊዜ የፖለቲካ፤ የማኅበራዊ፤ የባህል፤ የኤኮኖሚ ለዉጦች ሲኖሩ አብረዉ የሚመጡት አዳዲስ አስተሳሰቦች፤ ቁሶችና፤ ከአዲስ የአኗኗር ዘይቤዎች ጋር አዳዲስ

Kunst Festival in Addis Abeba
ምስል DW/A. T. Hahn

በዚሁ ርዕስ ጉዳይ የዶይቼ የአማርኛዉ ቋንቋ የፊስ ቡክ ተከታታዮች መተካካት ተሻለ፤ ልማቱ ፈጠነ ፤ ቦንድነህ አባይ፤ ኑሮ ዉድነህ የተባሉ አዳዲስ ስሞች ያልዋቸዉን ጨምሮ ፤ በደርግ ዘመን አድሃሪ፣ወንበዴ፣አብዬታዊ እርምጃ፣አንድነት፣ነፃ እርምጃ፣ጓዶች የተሰኙትን በርካታ ቃላትና አባባሎችን በዚሁ ሊሰናበት ሳምንት ባልቀረዉ ዓመት አካፍለዉናል ።

የኦሮሞ ማሕበረሰብ የሚከተለዉ ባሕላዊ የአስተዳደር እና የሥልጣን ሽግግር ሥርዓት ገዳ  በተባበሩት መንግሥታት የትምሕርት የሳይንስና የባሕል ድርጅት (UNESCO) የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡና ለኢትዮጵያ ድል፤ ለባሕሉ ባለቤቶች እርካታ መሆኑን በዚሁ በተሰናባቾቹ የፈረንጆቹ ዓመት የባህል መድረካችን በስፋት ያየዉ ርዕስ ነበር።  500ኛ ዓመት ያስቆጠረዉ የጀርመኑ የቢራ አጠማመቅ ዘዴ ፤ በኑረንበርግ 25ኛ ዓመት የደፈነዉ የኢትዮጵያዉያኑ ማኅበር  እንዲሁም ዝክረ ቅዱስ ያሬድ በሃገረ ጀርመን ፤ በሚል የቀረቡት የባህል መሰናዶዎችም ተጠቃሽ ናቸዉ። አድማጮች ለዝግጅቱ መሳካት ተሳታፊዎችን ፤  አስተያየት ጥቆማ ሂስ ለላካችሁልን ሁሉ በዶይቼ ቬለ ስም እያመሰገንኩ፤ ተሳትፎዎአችሁ እንዳይለየን በትህትና በመጠየቅ በጤና በፍቅር የዓመት ሠዉ እንዲለን በመመኘት ልሰናበት አዜብ ታደሰ ነኝ ጤና ይስጥልኝ።

 

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ