1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቡድን 7 መርሕ፣ ጉባኤና ተቃዉሞዉ

ሰኞ፣ ሰኔ 20 2014

ቡድን 7። የምጣኔ ሐብት ቀዉስ የወለደዉ፣በምጣኔ ሐብታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር፣ ምጣኔ ሐብታዊ ስብስብ ነበር።የዩናይትድ ስቴትሱ የገንዘብ ሚንስትር ጆርጅ ሹልስ የያኔ ዉጥናቸዉ ዛሬ የደረሰበትን ቢያዩ የሚሉትን ከመጠየቅ ባለፍ በርግጥ አናዉቀዉም።

https://p.dw.com/p/4DJse
G7 Gipfel auf Schloss Elmauin Deutschland
ምስል Stefan Rousseau/PA/empics/picture alliance

ቡድን 7 ምጣኔ ሐብታዊ ወይስ ፖለቲካዊ?

ግማሽ ያሕሉ የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሆነዉ ባለፈዉ ሳምንት ብራስልስ ላይ ተሰብስበዉ ነበር።ከተቀሩት ሁለቱ የጋራ ብልፅግና (ኮመንዌልዝ) መሪና አባል ሆነዉ ኪጋሊ-ሩዋንዳ ተሰብስበዉ ነበር።ትናንት ቡድን 7 ሆነዉ ኤልማዉ-ጀርመን ዉስጥ ተሰበሰቡ።ነገ ደግሞ ሌሎችን አስከትለዉ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) አባላት ሆነዉ ማድሪድ-ስጳኝ ይሰበሳባሉ።የየስብሰባዉ ትልቅ ርዕሳቸዉ፣ የአዉሮጳ ሕብረት ምክር ቤት ፕሬዝደንት ሻርልስ ሚሼል ትናንት እንዳሉት የሩሲያን የጦር ማሺን እስትንፋስን መበጠስ ነዉ።የሩሲያን ሕልቅት ለመፈጥረቅ የሚጣጣሩት መንግስታት መሪዎች ሕዳር ላይ ባሊ ኢንዶኒዚያ ዉስጥ ቡድን 20 ጉባኤ ላይ ከሩሲያዉ መሪ ጋር ፊትለፊት ሲጋፈጡ-የሚሉ የሚያደርጉት ካሁኑ ብዙዎችን እያነጋገረ፣ አንዳዶቹን እያጓጓ ነዉ።የበለፀጉ ሐገራትን መርሕ የሚቃወሙ ወገኖች እንደሚሉት የአብዛኛዉ ዓለም ሕዝብ ትልቅ ችግር-ችጋር፣ስደት ጦርነት ነዉ።የቡድን 7 ጉባኤ መነሻ፣ የተቃዋሚዎቻቸዉ ጥያቄ ማጣቃሻ፣ የመርሐቸዉ እንዴትነት መድረሻችን ነዉ ።
 ባለፈዉ መጋቢት የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅትም፣ የቡድን ሰባትም አባላት ሆነዉ ብራስልስ-ቤልጂግ ዉስጥ ተሰብስበዉ ነበር።የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ያኔ እንዳሉት ከወር በፊት የኔቶ አባል ሆነዉ ተሰብስበዉ ነበር።የሁለቱም ስብሰባዎች ዓላማ አንድ ነዉ።ዩክሬንን መደገፍ-ሩሲያን ማዳካም።
«የሩሲያ አረመኔዊ ወረራ ዩክሬን ላይ ከተጀመረ ዛሬ አንድ ወር ሆነዉ።ወረራዉ በተጀመረ ማግስት የኔቶ ጉባኤ አድርገን ነበር።በዚያ ጊዜ ከኔቶና ካዉሮጳ ወዳጆቻችን ጋር የተስማንባቸዉ በሰወስት በጣም አስፈላጊ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ፍፁም አንድ አቋም መያዝ ነበር።»
ባይደን ቁልፍ እና በጣም አስፈላጊ ካሏቸዉ 3 ጉዳዮች ሁለቱ፣-«የመጀመሪያዉ ለዩክሬን ወታደራዊና ሰብአዊ ድጋፍ መስጠት ነዉ።ሁለተኛዉ የፑቲንን ኤኮኖሚ ለማሽመድመድና ለእርምጃዉ ለመቅጣት  በሩሲያ ላይ በጣም ጠንካራ ምጣኔ ሐብታዊ ማዕቀብ መጣል ነዉ።»
ከያኔ እስካሁን የምዕራባዉያን ምርጥ ጦር መሳሪያ ወደ ዩክሬን ይጋዛል።አንዲት ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ለዩክሬን ያስታጠቀችዉ ጦር መሳሪያ ዋጋ 4.6 ቢሊዮን ዶላር ያወጣል።ጆ ባይደን የኔቶና «የአዉሮጳ ወዳጆቻችን» ያሏቸዉ ሐገራት፣ከጃፓን፣ከካናዳና ከአዉስትሬሊያ ጋር በጋራና በተናጥል፣ ለዩክሬን ያቀበሉት ጦር ዩናይትድ ስቴትስ ካለከችዉ ይበልጣል።
እነዚሕ መንግስታት ከየአየር ክልል እገዳ-እስከ ገንዘብ ዝዉዉር በሚደርስ ማዕቀብ ሩሲያን ቀጥተዋል።ከመኪና አምራች ኩባንዮቻቸዉ  እስከ ሽቶ ቸርቻሪ ሱቆች፣ ከማዕድን አዉጪ ኢንዱስትሪዎች እስከ ሳንዲዊች ሺያጭ መደብሮቻቸዉ ያሉ ተቋሞቻቸዉን ከሩሲያ አስወጥተዋል።ዩክሬን ግን ዛሬም ትወድማለች።ሺዎች ይረግፉባታል፤ሚሊዮኖች ይሰደዱባታል፤ከ20 ከመቶ የሚበልጠዉ ግዛትዋ በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ሥር ነዉ።አራት ወር።
የዘንድሮዉ የቡድን 7 ጉባኤ አስተናጋጅ የጀርመኑ መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስ ግን ፑቲን ጨርሶ  ያልጠበቁትን መልዕክት አስተላልፈናል ይላሉ።አንድ ነን።
«ጥሩዉ መልዕክት ሁላችንም በያዝነዉ አንድነት መፅናታቻን ነዉ።ይህን በግልፅ እንደሚታወቀዉ ፑቲን ጨርሶ አልጠበቁትም ነበር።»ፑቲን የጠበቁና ያልጠበቁትን በርግጥ አልነገሩንም።ባይደን ግን የሾልስን አባባል ደገሙት።
«በጋራ አቋማችን መቀጠል አለብን።ምክንያቱም ፑቲን ከመጀመሪያዉ ጀምሮ የሚጠብቁት የኔቶና የቡድን 7 (አንድነት)ይከፋፈላል ብለዉ ነበር።ግን አልተከፋፈልንም።አንከፋፈልምም።»
ቡድን 7። የምጣኔ ሐብት ቀዉስ የወለደዉ፣በምጣኔ ሐብታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር፣ ምጣኔ ሐብታዊ ስብስብ ነበር።የዩናይትድ ስቴትሱ የገንዘብ ሚንስትር ጆርጅ ሹልስ  የያኔ ዉጥናቸዉ ዛሬ የደረሰበትን ቢያዩ የሚሉትን ከመጠየቅ ባለፍ በርግጥ አናዉቀዉም።
አረቦች በተለይም ግብፅና ሶሪያ በ1973 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከእስራኤል ጋር በገጠሙት ጦርነት ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎችዋ እስራኤልን መደገፋቸዉን በመቃወም ነዳጅ አምራች የዓረብ ሐገራት የዳጅ ሽያጭ ማዕቀብ ጣሉ።ዓለም በጣሙን ብዙ ነዳጅ የሚጠጣዉ ባለኢንዱስትሪዉ ዓለም ደነገጠ።
ሹልስ መጋቢት 25፣ 1973 የምዕራብ ጀርመን፣ የፈረንሳይና የብሪታንያ የገንዘብ ሚንስትሮችን ዋሽግተን ላይ ስብሰባ የጠሩትም  የደረሰዉን የምጣኔ ሐብት ድቀት የሚከላከሉበትን ብልሐት ለመፈለግ ነበር።የገንዘብ ሚንስትሮቹ የመጀመሪያ ስብሰባ ዋይት ሐዉስ ቤተ-መፅሐፍት ዉስጥ በመደረጉ «የቤተ-መፅሐፍቱ ቡድን» ይባል የነበረዉ ስብስብ ባመቱ ጃፓንን አምስተኛ ቀይጦ ቡድን 5 ይባል ያዘ።
የፈረንሳይ ገንዘብ ሚንስትር ሆነዉ በመጀመሪያዉና በሁለተኛዉ ስብሰባ ላይ የተካፈሉት ቫለሪ ዢስካር ዴስታ የፕሬዝደንትነቱን ሥልጣን በያዙ ባመቱ በ1975 የአራቱን ሐገራትና የኢጣሊያን መሪዎች ጉባኤ ጠሩ።ቡድኑ የስድስቶች፣ ስብሰባዉም የመሪዎች ሆነ።ርዕሱ ግን አሁንም  ምጣኔ ሐብታዊ በጣሙን የነዳጅ ዘይት ቀዉስና የብሪተን ዉድስ የገንዘብ ሥርዓት መፍረስ ያስከተለዉ  ቀዉስ ነበር።
ባመቱ ካናዳ ተቀየጠች።ከ1977 ጀምሮ መጀመሪያ የአዉሮጳ  የምጣኔ ሐብት ማሕበረብ፣ ቀጥሎ የአዉሮጳ ሕብረት መሪዎች በየጉባኤዉ ይሳተፋሉ።ማሕበራቱ ግን የስብስቡ ሙሉ አባል አይደሉም።ሶቭየት ሕብረት ከተፈረካከሰች በኋላ በ1990ዎቹ ማብቂያ የዋሽግተንና የሞስኮዎች ፍቅር በጠናበት ሰሞን ሩሲያ የቡድኑ ተጨማሪ አባል ሆና ነበር።ቡድኑም ሩሲያ የዩክሬን የሚባለዉን የክሪሚያ ግዛት ከግዛትዋ እስከ ቀላቀለችበት እስከ 2014 ድረስ አንዳዴ ቡድን 8፣ ሌላ ጊዜ ቡድን 7+1 ይባል ነበር።ያ ፅሕፈት ቤት፣ ስራ አስፈፃሚ እና ቋሚ መሪ የሌለዉ ስብስብ ታዛቢዎች እንደሚሉት ከምጣኔ ሐብታዊነቱ ይብስ ፖለቲካዊነቱ፣ከዓለም አቀፋዊነቱ ይልቅ ምዕራባዊነቱ፣ ከፍትሐዊነቱ ይበልጥ የከበርቴዎችን ጥቅም አስከባሪነቱ፣ ከሰላም ይልቅ የኃይል እርምጃን ቅድሚያ መስጠቱ በግልፅ ይመሰከር ያዘ።
የዘንድሮዉ ጉባኤተኞችም ከሩሲያ ጋር የገጠሙትን ጠብ በድርድር የመፍታት ሐሰብ አላነሱም።የተነጋገሩና የተስማሙትም  የሩሲያን ወርቅ ላለመግዛት ተጨማሪ ማዕቀብ መጣል፣የዩክሬን መንግስትን ለመደገፍ ተጨማሪ ገንዘብ ማዉጣት ነዉ።
ሐገራቸዉ ዉስጥ አንዴ የኮሮና ሕግ በመጣስ፣ ሌላ ጊዜ ወዳጃቸዉን በማስቀጠር ቅሌት የሚወቀሱት የብሪታንያዉ  ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን የጉባኤዉን ትኩረት አልሸሸጉም።የዩክሬን መንግስትን መደገፍ ሊሰለቸን አይገባም አሉ።
 «እዚሕ ጀርመን ዉስጥ ከዓለም በጣም ሐብታም ሐገራት ጋር እንገኛለን።ትኩረታችን ዩክሬን እና በሕዝቡና በፖለቲከኞች ዘንድ መሰላቸት ባለበት በዚሕ ወቅት ዩክሬንን በጋራ የሚረዳዉ ሕብረት እንዴት መቀጠል እንዳለበት (ለመነጋገር) ነዉ።»
ቦሪስ ጆንሰን።ሐገራቸዉ ከአዉሮጳ ሕብረት አባልነት እንድትወጣ አጥብቀዉ የታገሉት ሕብረትና ትብብርን ጠልተዉ፣ ጎጂነቱን ሰብከዉ  ነበር።ዛሬ ግን በሕብረትና በአንድነት የመቆምን ጥቅም ይደሰኩራሉ።
«ፑቲን ዩክሬንን በመዉረራቸዉ ምዕራባዉያን ከሰጡት አፀፋ በጣም የማይታመነዉ ነገር በሕብረት መቆማቸዉ ነዉ።የኔቶ አንድነት ጠንካራ ነዉ።የቡድን 7 አንድነት ጠንካራ ነዉ።እንደጠነከርን እንቀጥላለን።»
የአዉሮጳ ሕብረት ምክር ቤት ፕሬዝደንት ሻርልስ ሚሼል ደግሞ ስለ ጉባኤዉን ዓላማ ሁሉንም አሉት።«ከቡድን 7 አባል ሐገራት ጋር ሁላችንም ተመሳሳይ ግብ እንጋራለን።ለኛ እና ለወዳጆቻችን ኤኮኖሚ ጥንቃቄ በማድረግ የሩሲያን የጦር ማሽን ኦክስጂን እንበጥሰዋለን።የአዉሮጳ ሕብረት የዩክሬን ሕዝብ ሉዓላዊነቱንና የግዛት አንድነቱን  ለማስከበር በሚያደርገዉ ትግል ለረጅም ጊዜ ከጎኑ ይቆማል፤ የጠንካራ ዴሞክራሲያዊ እሴቶቻችንም እንከላከላለን።»
ኪየቭ ግን ትናንት በሚሳዬል ትነድ፣ ነዋሪዎችዋ ይገደሉ፣ ይላቀሱም ነበር።4ኛ ወር።ጉባኤተኞች ካንጀት ይሁን ካንገት ባይታወቅም በድሆቹ ሐገራት የመሰረተ ልማት አዉታሮችን ለመገንባት 6 ቢሊዮን ዶላር እንደሚመድቡ  አስታዉቀዋል።ገንዘቡን የሚመድቡት ግን ቻይና በድሆቹ ሐገራት ላይ የምታሳድረዉን ተፅዕኖ ለመሻማት እንጂ በርግጥ ድሆቹን ለማልማት ከልብ አስበዉ እንዳልሆነ አልሸሸጉም።
በዓመቱ እንደሚደረገዉ ሁሉ የጉባኤተኞችን መርሕ፣ ዓላማና ዕቅድ የሚቃወሙ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች ካለፈዉ ቅዳሜ ጀምሮ ከሙዩኒክ እስከ ጉባኤዉ አዳራሽ የሚገኙ ከተሞችን በሰልፍ አጥለቅልቀዋቸዋል።ከሰልፈኞቹ አስተባባሪዎች አንዱ፣ አንዲት ጀርመን የተሰኘዉ ስብስብ መሪ  ሽሪውዊን  ሳኢዲ እንደሚሉት የጉባኤተኞች መርሕና የሚገቡት ቃል  ለድሆችን ከማስራብ በስተቀር የተከረዉ የለም።
«የበለፀጉት ሐገራት በየጊዜዉ ቃል ቢገቡም  ከ2017 ጀምሮ በተጨባጭ የምናየዉ ተቃራኒዉን ነዉ።ዛሬ በ2022 በምግብ እጥረት የሚሰቃየዉ ሕዝብ በ2015 ከነበረዉ በ150 ሚሊዮን መጨመሩን ነዉ። ከሚገባዉ ቃል በተቃራኒ ያለዉ ዕዉነት ይሕ ነዉ።»
ኦክስፋም የተባለዉ ዓለም አቀፍ ድርጅት ባልደረባ ቻርሎት ቤከር ደግሞ በኢንዱስትሪ የበለፀገዉ ዓለም ከራሱ ጥቅም ባለፍ ሌላዉን ዘንግቶታል ባይ ናቸዉ።በቁጥርም ያጋልጣሉ።
«የኮሮና ተሕዋሲ በተሰራጨበት ወቅት ከቡድን 7 ትላልቅ ኩባንዮች የተሰበሰበዉ የትርፍ ቀረጥ ቢያንስ  430 ቢሊዮን ዶላር ነዉ።ይሕ ገንዘብ ከመላዉ ዓለም ድሕነትና ረሐብን ለማቃለል በቂ ነበር።እንዲሕ አይነቱን ቀረጥ ለሚፈለገዉ ጉዳዩ ማዋሉ ግን ፖለቲካዊ ፈቃደኝነትን የሚጠይቅ ነዉ።»
ተቃዋሚዎቹ ተሰለፉ- አወገዙ፣ ጉባኤተኞችም ተናገሩ፣ተወያዩ፣ ተስማሙም።ነገ ደግሞ ሌላ ጉባኤ አለባቸዉ።ማድሪድ-ስጳኝ።የሰሜን አትላንቲካ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጉባኤ።ጉባኤዉ በቅርቡ የኔቶ አባል ለመሆን ካመለከቱት ሐገራት መካከል የፊንላንድና የስዊድንን አባልነት ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።ይሁንና ጉባኤተኞች የቱርክን ተቃዉሞ የሚያረግቡበትን ብልሐት ለማወቅ የጉባኤዉን ሒደት መጠበቅ ግድ ነዉ።

Deutschland G7 Gipfel Protest
ምስል Wolfgang Rattay/REUTERS
Deutschland G7 Gipfel Protest
ምስል Angelika Warmuth/dpa/picture-alliance
G7-Gipfel 2022 · Ankunft der Gäste, Joe Biden
ምስል Susan Walsh/AP/dpa
G7 Gipfel Schalte mit Selenskyj
ምስል Tobias Schwarz/AFP

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ