1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የቡና ላኪዎች በአትኩሮት የሚከታተሉት የዓለም ገበያ በኮሮና ዘመን

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 7 2012

የኢትዮጵያ ቡና ዋንኛ ደንበኞች በሆኑት ጃፓን፣ ጀርመን፣ ጣሊያን እና ፈረንሳይ በመሳሰሉ አገሮች በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ የለት ተለት እንቅስሴ ተገድቧል። ቡና ቤቶች፣ የመገበያያ ማዕከላት ተዘግተዋል። ወረርሽኙ ከኢትዮጵያ ቀዳሚ የውጭ ምንዛሪ ምንጮች አንዱ በሆነው የቡና ግብይት ላይ ምን ተፅዕኖ አሳደረ? ወደ ፊትስ ምን ጣጣ ይዞ ይመጣል?

https://p.dw.com/p/3avzl
Kafeeernte in Äthiopien
ምስል Reuters/M. Haileselassie

የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች የኮሮና ትኩሳት በግብይቱ ላይ ታዝበዋል

በዓለም ገበያ የነዳጅ ዘይት ፍላጎት እና ዋጋ ሲያሽቆለቁል የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች በጥንቃቄ ይታዘባሉ። ባለፉት ጥቂት ወራት መዋዠቅ የበረታበት ግን ነዳጅ ዘይት ብቻ አይደለም። የብረት፣ ነሐስ እና የወርቅ ግብይት ጭምር እንደወትሮው አይደለም። የኮሮና ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ የእያንዳንዱ አስፈላጊ ሸቀጥ ዋጋ በዓለም ገበያ ቀንሷል።

የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ዋና ጸሐፊ አቶ ግዛት ወርቁ «በሽታው በዋናነት ያጠቃው የእኛን ዋና [የቡና] ገዢዎች ነው። ጀርመን ከ22 እስከ 23 በመቶ የኢትዮጵያን ቡና ትገዛለች። አሜሪካም ተመሳሳይ ነው። ጃፓን፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን ፣ቤልጅየም እና ስዊትዘርላንድ የእኛ ገዢዎች ናቸው» በማለት የኢትዮጵያ ነጋዴዎች ዓለም አቀፉን ቀውስ በአንክሮ የሚከታተሉበትን ምክንያት ያስረዳሉ።

መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገው ሉሲ ቡና ለአሜሪካ፣ ብሪታኒያ፣ ስዊትዘርላንድ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓን እና ደቡብ አፍሪካ ገበያዎች የኢትዮጵያን ቡና ሲልክ አመታት ተቆጠሩ። ኩባንያው በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል የሚሸምተውን ቡና በዓለም ገበያ ለደንበኞቹ ያቀርባል።  የኮሮና ወረርሽኝ የዓለም ገበያን ማተራመስ የጀመረው የኩባንያው መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ብርሀኑ ተድላ አሜሪካን ለሚገኝ ኩባንያ ቡና ለመሸጥ ውል ሊፈራረሙ ዝግጅት ላይ ሳሉ ነው። «ደንበኛዬ ኮንትራቱን ከላከ በኋላ አሁን የተፈጠረው ችግር አስቸጋሪ ስለሆነ የተወሰነ ጊዜ እንስጠው ብሎ አዘግይቶታል» ሲሉ የገጠማቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አቶ ብርሀኑ ለጣልያን እና ለጀርመን ገበያዎች ሊልኩ ያዘጋጁት ቡናም ቢሆን በወቅቱ አልተላከም።

«ጣልያን እና ጀርመን ብዙ ኮንቴነሮች ለመላክ ኮንትራት ነበረኝ። እነዚያን ኮንትራቶች በችግሩ ምክንያት ደንበኞቼ `ችግሩ ስላለ አሁን ኤልሲ መክፈት አንችልም። አቆይልን። ችግሩ ቶሎ ከተቀረፈ ኮንትራታችንን እንደገና እናድሳለን። ችግሩ ካልተቀረፈ ግን ይቆያል` ብለውኛል » ሲሉ አቶ ብርሀኑ ያክላሉ።

ይኸ በኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች እና ደንበኞቻቸው መካከል የሚፈጠር መስተጓጎል በሁለቱም ላይ ጣጣ ያስከትላል። በተለይ ለኢትዮጵያ ምጣኔ-ሐብት ዳፋው የከፋ ነው። ኢትዮጵያ በየአመቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከምታገኝባቸው ዘርፎች አንዱ ይኸው የቡና ግብይት ነው። ወደ 15 ሚሊዮን ገደማ የአገሪቱ ዜጎች የለት ተለት ኑሮ ከቡና ጋር የተሳሰረ ነው።

Kafeeernte in Äthiopien
የ15 ሚሊዮን ገደማ ኢትዮጵያውያን የለት ተለት ኑሮ ከቡና ጋር የተሳሰረ ነው።​​​​​​ምስል Reuters/M. Haileselassie

የኦሮሚያ ቡና አምራች ገበሬዎች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ዑመር ዋቤ «ለምሳሌ እኛ በአንድ አመት ውስጥ ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ ቡና ለመሰብሰብ ወጪ እናደርጋለን። ስለዚህ ታች ወርደን ቡና ለማሰባሰብ ተፅዕኖ አለው» ሲሉ የኮሮና ወረርሽኝ ቢበረታ ሊያስከትል የሚችለውን እክል ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። «የእኛን ቡና 30 በመቶ የምትገዛው አሜሪካ ነች። ሳዑዲ አረቢያ፣ ጀርመን እና ፈረንሳይ ይከተላሉ። በእነዚህ አገሮች ደግሞ በሽታው በከፍተኛ ደረጃ የተስፋፋባቸው ስለሆኑ በዚያ ያለው ኹኔታ ካልተሻሻለ ጫናው ወደ እኛም ሊመጣ ይችላል። አሁን እንኳ ብር ለማዘዋወር ጭምር የተቸገሩበት ኹኔታ አለ። አንዳንድ ኩባንያዎች በአገራቸው ተረጋግተው በቢሮ እየሰሩ ስላልሆነ የተወሰነ መስተጓጎል ተፈጥሯል» ይላሉ አቶ ዑመር።

ግዙፉ ስታር ባክስ ኩባንያ በአሜሪካ እና አውሮፓ ከነበሩት ቡና ቤቶች በርካቶቹ ተዘግተዋል። ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና ጣሊያንን ጨምሮ በበርካታ አገራት የቡና መሸጫ ሱቆች ደጃፎቻቸውን ከዘጉ ሰነባበቱ። በአውሮፓ አገራት ትኩስ ቡና፣ ማኪያቶ አሊያም ላቴ ለመሸጥ የተከፈቱ በጣት የሚቆጠሩ ቢኖሩም ግልጋሎት የሚሰጡት ይዘው ለሚሔዱ ደንበኞቻቸው ብቻ ነው። የኮሮና ወረርሽኝ የበረታባቸው አገራት ገቢራዊ ያደረጓቸው ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደቦች ዜጎቻቸውን ብቻ ሳይሆን ገበያዎቻቸውን ጭምር እጅ ተወርች ጠፍሯል። የኦሮሚያ ቡና አምራች ገበሬዎች ማኅበር ሰራተኞቹን ቀንሶም ቢሆን የዓለም ገበያን ውጣ ውረድ እየታዘበ ነው። አቶ ዑመር እንደሚሉት የኮሮና ወረርሽኝ የቡና ዋጋ እንዲቀንስ የሚያስገድድበት ዕድል ሊኖር ይችላል።

«የእኛ ገዢዎች ለቸርቻሪዎች ነው ቡናውን የሚሰጡት። በዚያ አካባቢ ያሉ ቡና ቤቶች ከተዘጉ እና የእኛ ደንበኛ የመግዛት ፍላጎት ከወረደ ዋጋው ሊቀንስ ይችላል። ከእኛ ጋር የሚሰራ አንድ ኩባንያ እገዛለሁ ብሎ ቡናውን አዘጋጅተናል። ነገር ግን ኤልሲ አልገባልንም። ይኸ ኩባንያ ያንን ቡና ካልወሰደው ቡናው ካደረ ዋጋው ይወድቃል» ሲሉ አቶ ዑመር ተጨማሪ ሥጋቶቻቸውን ይገልጻሉ።

እስካሁን በግብይት ላይ በታየው የኮሮና ወረርሽኝ ተፅዕኖ ወደ ውጪ መላክ የነበረበትን ቡና ከማዘግየት ባሻገር ኪሳራ ማስከተል ጀምሯል። ከባንክ ተበድረው ቡና ወደ ውጪ አገራት ለሚልኩ እንደ ሉሲ አይነት ኩባንያዎች ግብይት በመዘግየቱ የባንክ ወለድ ጭማሪ ተጋርጦባቸዋል።

Coronavirus Österreich Wien Lockerung Ausgangssperre
ምስል AFP/APA/H. Fohringer

አቶ ብርሀኑ «ቡና የተወሰነ ጊዜ ይቀመጣል። ችግሩ መቼ ይፈታ ባናውቀውም የተወሰነ ጊዜ መቀመጡ ችግር ላይኖረው ይችላል። ደንበኞቻችን ይቀራል የሚል ውሳኔ አልወሰኑም። ቡናው በመቆየቱ እኛን የሚጎዳን ከባንክ ተበድረን ነው ቡናውን የገዛንው። የባንክ ዕዳችን ወለድ እየወለደ ነው። እሱ ትልቅ ጉዳት ነው። ከባንክ የተበደርንውን መልሰን ለመክፈል ያለን ጊዜ የ90 ቀን ብድር ነው። እስከ ስድስት ወር ያለ ብድር ነው። ያንን ሳንከፍል ስንቀር አንደኛ ወለዱ ይጨምራል። ሁለተኛ ከባንኩ ጋር ያለንን ግንኙነት ሊያበላሽብን ይችላል» ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም ገበያ ካሳደረው ተፅዕኖ አኳያ በቡና ግብይት ላይ የታየው ጫና የከፋ አለመሆኑን የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ዋና ጸሐፊ አቶ ግዛት ወርቁ ይናገራሉ። «የተወሰነ ግብረ መልስ ከላኪዎች ሰብስበናል» የሚሉት አቶ ወርቁ «የተወሰነ ኮንትራት እንዲራዘምላቸው የሚጠይቁ አሉ። የሚላክበት ቀን የደረሰ ከሆነ ደግሞ ቶሎ እንዲጫንላቸው የሚፈልጉ አሉ። እስከ መጋቢት መጨረሻ ባለው መረጃ ግን ወደ ውጭ የሚላከው ቡና ያን ያክል አልተጎዳም። ይኸ በሽታ የፈጠረው የኤኮኖሚ መቀዛቀዝ የማይነካካው የለም። ማንኛውም ነገር በጣም የተሳሰረ ስለሆነ በወረርሽኙ ይነካል። የፋይናንስ ዘርፉ፣ የአገልግሎት ዘርፉም ይሁን ቱሪዝም ተነክቷል። እንዲያውም ቡና እስከ መጋቢት 30 ባለው ጉዳቱ አነስተኛ ነው። ለወደፊቱ ስናስብ ቡና በሚመለከት ቀጥሎ ምንድነው የሚሆነው? አናውቅም» ሲሉ መጪው ጊዜ የበለጠ ውስብስብ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር አባል ድርጅቶች ገዢ ካገኙ በእጃቸው ያለውን ቡና በጊዜ እንዲሸጡ ይመክራል። ማኅበሩን ከእንዲህ አይነት አቋም ያደረሰው ወረርሽኙ የሚያስከትለው ቀውስ ምን አይነት ሊሆን እንደሚችል አለመታወቁ ነው። ከቡና ንግድ በተጨማሪ በሆቴል ሥራ የተሰማሩት አቶ ብርሀኑ ወረርሽኙ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ቢሉም «ቫይረሱ በኢትዮጵያ ከተገኘ አንድ ወር አካባቢ ሆኖታል። በዚህ ጊዜ ውስጥ የፈጠረው ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ቀላል አይደለም። ይኸ በሽታ እየተስፋፋ ከሔደ በጣም አደገኛ ቀውስ ነው የሚፈጥርብን። ለሰራተኞቻችን ደሞዝ የመክፈል ችግር ይገጥመናል። የከፍተኛ የባንክ ዕዳዎችን የመክፈል ችግር ይገጥመናል። የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር በእጅጉ ያባብስብናል» ሲሉ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ