1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

  የቀድሞ እስረኞች አስተያየት

ሐሙስ፣ ኅዳር 6 2011

በሀሰት እየተወነጀሉ መከሰሳቸውን፣ ያልፈጸሙትን ወንጀል ፈጽመናል ብለው እንዲያምኑ በመርማሪዎች ቁም ስቅል እንደተፈጸመባቸው DW ያነጋገራቸዉ 3 የቀድሞ እሥረኞች ተናግረዋል። በተለምዶ ማዕከላዊ በሚባለው እስር ቤት፣ በቃሊቲ እና በቅሊንጦ በአጠቃላይ ለ12 ዓመታት የታሰረው ከፍያለው ተፈራ እንደተናገረዉ የተፈጸመበት ግን ተወዳዳሪ ያለው አይመስልም።

https://p.dw.com/p/38GP1
Logo FDRE Federal Attorney Äthiopien

  የቀድሞ እስረኞች አስተያየት

በኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል የተጠረጠሩ የመንግሥት የቀድሞ ባለሥልጣናት በቁጥጥር ስር መዋላቸው በየእስር ቤቱ ልዩ ልዩ ግፍ፤ ስቃይ እና በደል ለተፈጸመባቸው ዜጎች ልዩ ትርጉም የሚሰጥ መሆኑን DW ያነጋገራቸው የቀድሞ እሥረኞች ተናገሩ። በእስር ቤቶች የአካል ጉዳትን ጨምሮ የተለያዩ የሰብዓዊ ጥሰቶች እንደደረሰባቸው የሚናገሩት እነዚሁ ሰለባዎች በደል አድራሾቹ በህግ እንዲጠየቁ መያዛቸው የህግ የበላይነትን የሚያሳይ እርምጃ ነው ብለዋል። ጅምሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል። በሀሰት እየተወነጀሉ መከሰሳቸውን፣ ያልፈጸሙትን ወንጀል ፈጽመናል ብለው እንዲያምኑ በመርማሪዎች ቁም ስቅል እንደተፈጸመባቸው DW ያነጋገራቸዉ ሦስት የቀድሞ እሥረኞች ተናግረዋል። በተለምዶ ማዕከላዊ በሚባለው እስር ቤት፣ በቃሊቲ እና በቅሊንጦ በአጠቃላይ ለ12 ዓመታት የታሰረው ከፍያለው ተፈራ እንደተናገረዉ የተፈጸመበት ግን ተወዳዳሪ ያለው አይመስልም። ከፍያለው ከ12 ዓመት በፊት በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የ3ተኛ ዓመት ተማሪ ነበር። ያኔ ትምህርት ቤት በተዘጋበት ወቅት ከጓደኞቹ ጋር ከወለቴ ሰበታ ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ላይ ሳሉ ተኩስ ተከፍቶባቸው ሦስት ጓደኞቹ ሲሞቱ እርሱ ግን ቆስሎ ይያዛል። 
«አንድ እግሬ ተጎድቶ አንድ እግሬ ቆስሎ እያለ ፖሊስ ሆስፒታል ውስጥ እንደገና እግሮቼን 3 ቦታ ቆረጡት 3 ጊዜ አንደኛው ቀኝ እግሬ ሶስቴ ነው የተቆረጠው።ከዛ በኋላ ማዕከላዊ ሄጄ በቁስሌ ለረዥም ጊዜ ሲያሰቃዩኝ ነበር። ቁስሌን በፒንሳ ይጎትታሉ፣ይወጋሉ፣ረዥም ጊዜ ጨለማ ቤት ውስጥ ሲሰቃይ ነበር። ለሊት ለሊት 9 ሰዓት 8 ሰዓት አካባቢ ያነሱኛል።ይጥሉኛል። አፌ ውስጥ በጣም የሚሸት ካልሲ አፌ ውስጥ ይወትፉ ያስሩ ነበር።»  
ከፍያለው  ለዚህ ሁሉ ስቃይ የተዳረገው ከኦነግ አመራሮች ትዕዛዝ እየተቀበልክ ቦምብ ታፈነዳለህ፣ ህገ ወጥ መሣሪያ ወደ ሀገር ታስገባለህ እየተባለ ነበር። ሁለት እግሮቹን ያጣው ከፍያለው እንደሚለው ይሄ ሁሉ የሀሰት ውንጀላ ነው። የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባል እና ደራሲ አህመዲን ጀበልን ሐምሌ 2004 ከያዙት ሰዎች መካከል፣ አሁን የታሰሩት ባለሥልጣናት ይገኙበታል። አህመዲን በእርስ ቤቶ ቆይታው የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደደረሱበት ያስታውሳል።
«እኔ በተያዝኩበት ሰዓት ላይ አካላዊ ድብደባ ነበር ።ፊቴን አስረውኝ በኮሮላ መኪና ይዘውኝ ነው ደህንነት ቢሮ የወሰዱኝ  ።አንድ ምሽትም እዛ ነው ያደርኩት ያደርኩትም በኋላ ላይ እንዳወቅኩት ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ አዲስ አበባ «ኢትዮ ጥበብ» ሆስፒታል ፊት ለፊት የሆነ ቦታ ነው። ስድብ ከዛም አልፎ በሰደፍ መደብደብ ሌሊቱን በማንገላታት ነበር ።በማግስቱ ነው ወደ ማዕከላዊ የተወሰድኩት። ከነሐሴ 3 ጀምሮ ያሉት 10 ቀናት ለ16 ሰዓት ያህል አስሮ ማቆም፣ ቀዝቃዛ እና ጨለማ ክፍል ውስጥ ማንገላታት ከዛም አልፎ  ድብደባ አጸያፊ የሆኑ ስድቦች ሆን ብለው ሞራል ለመንካት ከመፈለግ አንጻር።»
5 ዓመት ከስድስት ወር የታሰረው አህመዲን ማስፈራራት፤ ዛቻም ይደርስበት እንደነበር በሀሰት መወንጀሉን እና በሀሰት እንዲመሰክርም ሲያግባቡት እንደነበር ገልጿል። ከ9 ጊዜ በላይ መታሰሯን የምትናገረው ፖለቲከኛ ወይንሸት ሞላ በተለያዩ እስር ቤቶች የደረሰባትን እና ሌሎች ሴት ታሳሪዎች ተፈጸመብን ሲሉ የሰማችውንም እንዲህ ገልጻዋለች።
«በ2006 ጭንቅላቴን ፈንክተውኝ እንዲሁም እጄን ሰብረው ነበር። ያኔ ያለምንም ህክምና ረዥም ሰዓት ደም እየፈሰሰኝ ረዥም ሰዓት ራሴን ለመሳት በሚያቀርብ ሰመመን ውስጥ  ሆኜ ምርመራ ይደረግብኝ ነበር። ሌሊቱን በሙሉ ዛቻ ማስፈራሪያ ከፖለቲካ እንድንወጣ እንዲሁም የተለያዩ ሰብዓዊ መብቶችን የሚጥሱ ስድቦች እና ድብደባዎች ይደርሱብናል።ባዶ ክፍል ውስጥ ብቻዬን አስረውኝ ያውቃሉ። በአጋጣሚ በኔ ላይ አልደረሰም እንጂ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አካባቢ በተለይ በጦላይ ማሰልጠኛ ካምፕ በታሰርኩበት ጊዜ ወደ 250 አካባቢ የሚሆኑ ሴቶች ነበሩ።ከመደፈር ጀምሮ ጫካ ውስጥ ብቻቸውን ከመታሰር ጥፍራቸውን እስከመንቀል ድረስ ብዙ ደረሰብን ይላሉ።»  
በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ የብሔራዊ የመረጃ እና ደህንነት፤ የፖሊስ እና የማረሚያ ቤት ሃላፊዎች እና ሠራተኞች መከሰሳቸዉ ለከፍያለው የህግ የበላይነትን የሚያረጋግጥ ነው። ይሁን እና በርሱ አመለካከት በዚህ ወንጀል መጠየቅ የሚገባቸው አሁን የተያዙት ብቻ አይደሉም።    
ድምጽ ከፍያለው 
«አሁን ትንሽ ሰዎች ናቸው የታሰሩት ከላይ፤ከስር ብዙ ሰዎች ይሰራሉ። አሁን ቃሊቲ በጠራራ ፀሐይ ሰዎችን አውጥተው እያሰቃዩ እየደበደቡ ሰው እየጮኽ ሲገድሉ የነበሩ ሰዎች እስካሁን አሉ። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነርም አሉ። ይቀጥልበትና ለሌላ ሰዎች ትምሕርት ቢሆን ደስ ይለኛል።»
ወይንሸትም የከፋያለውን ሀሳብ ነው የምትደግፈው። ወይንሸት ጅምሩን ግን ሳታደንቅ አላለፈችም። 
«ጥሩ ጅማሮ ነው ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም ትክክለኛ ፍትህን ለማስፈን እየተንቀሳቀስን ከሆነ ወንጀለኞችን በወንጀላቸው እንዲጠየቁ ማድረግ ትልቅ ነገር ነው።»
አህመዲን ጀበል ሰሞኑን በደህንነት እና በእስር ቤት ሃላፊዎች ላይ የተወሰደውን እርምጃ አስተማሪ ይለዋል።
«ለኔ በሁለቱ ቀናት የተከሰቱት ክስተቶች ምናልባት ከሰዎቹ ማንነትና ከያዙት ሥልጣን ከነበሩበት ሁኔታ አንጻር በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ አስተማሪ ወደፊትም መሠረታዊ ትምሕርት የሚገኝበት ክስተት ነው ብዬ እውስደዋለሁ።»
ከፍያለው የተፈጸመው በደል በካሳ ይመለሳል የሚል እምነት የለውም። ሆኖም በእስር ቤት አያያዝ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ፣በመታሰራቸው ከስራቸው ለተፈናቀሉና መውደቂያ ላጡ ዜጎች መንግሥት የተቻለውን ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል የሚል እምነት አለው።

Äthiopien verhaftet 63 wegen Verdachts auf Menschenrechtsverletzungen, Korruption. Der Generalstaatsanwalt Berhanu Tsegaye sagte heute (03.11.2018) lokalen Journalisten, dass die Inhaftierung nach fünf Monaten Ermittlungen erfolgt.
ምስል DW/Y. Geberegziabeher
Police have detained Major General Kinfe Dagnew, former Director General of the state-owned Metals and Engineering Corporation
ምስል Ethiopian government communication
Ahmedin Jebel -  muslimischer Gelehrter
ምስል Privat

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ