1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

ረቡዕ፣ ግንቦት 30 2015

“ታንክ ማራኪው ጀግና” የሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ ስርዓተ ቀብር ዛሬ ተፈጸመ። አሊ በርኬ፥ በ1960ዎቹ መጨረሻ የሶማሊያው የዚያድባሬን ጦር ለመመከት በካራማራም ጀብዱ ከሰሩ ሰራዊት ስማቸው ጎልቶ ይጠቀሳል። ሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ከትናንት በስትያ ሰኞ በ72 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወሳል ።

https://p.dw.com/p/4SJTG
Äthiopien | Beisetzung Ali Berke
ምስል Seyoum Getu/DW

የሻለቃ ባሻ አሊ በርኪ የቀብር ስነስረዓት ተፈጸመ

“ታንክ ማራኪው ጀግና” በሚል ስም የሚታወቁት  የሻለቃ ባሻ አሊ በርኪ ስርዓተ ቀብር ዛሬ ተፈጸመ። 

የቀድሞው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል የነበሩ አሊ በርኬ፥ በ1960ዎቹ መጨረሻ የሶማሊያው የዚያድባሬን ጦር ለመመከት በካራማራም ጀብዱ ከሰሩ ሰራዊት ስማቸው ጎልቶ ይጠቀሳል። ሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ከትናንት በስትያ ሰኞ በ72 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወሳል፤  ወዳጅ ዘመዶቻቸው የትግል አጋሮቻቸው በተገኙበት ዛሬ በብሔራዊ የአስከሬን ሽንት ታጅቦ ስርዓተ ቀብራቸው በአዲስ አበባ ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።

“አባቴ እኛን ከማሳደግ ከከፈለው ዋጋ ይልቅ ለአገር እራሱን የሰጠበት መንገድ ልቃል ብዬ አምናለሁ፡፡ በአገር ከመጣ በእኛ በልጆቹም ብሆን እንደማደራደር ነው እየነገረን ያሳደገን፡፡ እሱ ከየትኛውም የፖለቲካ አስተሳሰብ የፀዳ እውነተኛ የአገር ፍቅር ያለው ሰው ነው፡፡ ከእረኝነት ቀጥታ ወደ ውትድርና የወሰደውም ይህ የአገር ፍቅሩ ነው፡፡ ግን ይህን የሚመጥን ክብር ከአገሩ አግንቷል ብ አላምንም፡፡ አሁን በስተመጨረሻም ብሆን ግን የተሰጠው ክብር ታሪክ እንዲያብብ ሚያደርግ ነውና ይህን በማየቴ እራሴን እንደ እድለኛ እቆትራለሁ፡፡” የካራመራው ጀግና የሻለቃ አሊ በርኬ ልጅ በክሪ አሊ ዛሬ በስርኣተ ቀብራቸው ላይ ለዶቼ ቬለ የሰጡት አስተያየት ነበር፡፡

የሶማሊያ መሪ የነበሩት ዚያድባሬ እስከ አፍንጫው በታጠቀው ጦሩ ወደ አሁኑ የኢትዮጵያ ምስራቃዊ ግዛት በገባ ጊዜ፥ ግንባር ዘምተው በኢትዮጵያ ምንጊዜም የሚዘከረውን የካራማራ ጦርነት በድል ለማጠናቀቅ በተደረገው ደም አፋሳሽ ጦርነት ጎልቶ ከሚነሱ የጦር ሜዳ ጀብዱዎች በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ስሞች አንደኛው አሊ በርኬ ነው። ወረራውን ተከትሎ የወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም፥ ሚያዚያ 4 ቀን 1969 ዓ.ም የሀገር አድን ጥሪን ሲያውጁ፤ ከቀድሞው ወለጋ ክፍለ ሀገር ቤጊ ወረዳ ከአባታቸው በርኬ ቱቾ እና ከእናታቸው አሙና ቡልቻ የተወለዱት ሻለቃ አሊ በርኬ ጥሪውን በመቀበል ቀድሞ ኦጋዴን ከደረሱ ዘማቾች ተጠቃሽ ነበሩ። 

“ታንክ ማራኪው ጀግና” በሚል ስም የሚታወቁት  የሻለቃ ባሻ አሊ በርኪ ስርዓተ ቀብር ዛሬ ተፈጸመ። 
“ታንክ ማራኪው ጀግና” በሚል ስም የሚታወቁት  የሻለቃ ባሻ አሊ በርኪ ስርዓተ ቀብር ዛሬ ተፈጸመ። ምስል Seyoum Getu/DW

በታዳጊነት እድሜያቸው በኦጋዴን አቡሸሪፍ ግንባር በተደረገ ከባድ ውጊያ የሶማሊያ ሀይል ቲ-55 የተሰኙ 3 ታንኮችን በእጅ ቦምብ በማጋየት 2ቱን ማርከው ትልቅ ጀብድ የሰሩ  ይባልላቸዋልም። ገና በልጅነታቸው አንበሳ፣ ጎሽ እና ነብር በማደን ያሳለፉት አሊ በጦርነት ግንባር ኢላማቸውም ወደር የለሽ ሰው ይባልላቸዋል፡፡ አሊን በአካል በዚያ በጦር ሜዳ የሚያውቃቸው ጓዶቻቸው ስለእሳቸው አውርተው አይጠግቡም፡፡

መቶ አለቃ በቀለ በላይ በ1969ኙ የሶማሊያ ወረራ ወቅት በምስራቅ ኢትዮጵያው ጦርነት በ18 ዓመታቸው የተሳተፉና ከሻለቃ አሊ በርኬ ጋር የተዋደቁ ናቸው፡፡ በወቅቱ ከወለጋ ክፍላገር የዘመተው ታናሹ አሊ እድሜህ ትንሽ ነው ብባልም አሻፈረን ብሎ ወደ ጦር ሜዳ ማቅናቱንም ያወሳሉ፡፡

የ50 ዓለቃ ብርሃኑ አማረ ደግሞ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት የድጋፍ እና የልማት ማህበር ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡ አሊ በርኬን ለጦር ሜዳ ጀግንነት የተፈጠረ ሃገሩን የሚወድ ብለውአቸዋል፡፡

“የአገር ፍቅር ያናወዘው አሊ፤ ከፊቱም የሚንቦገቦግ ነበልባል ማንነቱን የሚያበስር” ይሉታል፡፡ “በኦጋዴን ምድር ጀግናው አሊ ያልረገጠው ምድር አልነበረም፡፡ በሀረር፣ ባቢሌ፣ ፈዲስ፣ ጅግጅጋ፣ ቀብሪዳሃር፣ ደጋሃቡድ፣ ጎዴ፣ ቀላፎ፣ መስታየል ዋርደር ውጊያ ፈጽሟል፡፡ ከምንም የሚጎላው ግን አቦሸር በተባለች ስፍራ ታንኮችን ያጋየበት ነው” ይላሉ ጓዶቹ፡፡

ይህ የላቀው የጦር ሜዳ የጀግና ውሎያቸውም፤ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት መንግስቱ ኃይለማሪያም የጀግና ኒሻን ሽልማት አሸለማቸው፡፡ ከጦር ሜዳ ሲመለሱም በወቅቱ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር የጀግና አቀባበል ተደረገላቸው፡፡ ከዚያን በኋላ በየትኛም አገራዊ በዓላትም ሆነ ታላላቅ ስነስርዓቶች ላይ የመጀመሪያው የክብር ወንበር የሚያዝላቸው ሆነ፡፡

ይሁንና በአገሪቱ ከፖለቲካ ስርዓት ለውጥና ከመንግስት ግልበጣ በኋላ የአሊ ህይወት ይመሰቃቀል ያዘ፡፡ በተወለደባት ወለጋ ክፍላገር ህይወቱንም መምራት ያልቻለው የአገር ባለውለታ “በደርግ ሰራዊት አባልነት” ተፈርጀው ቤተሰቦቻቸውን በታትነው የመከራ ህይወትን ተያያዙ፡፡ ለ11 ዓመታት ገደማ ያለፍርድ በእስር እንደታጎሩም በግለታሪካቸው ላይ ተጠቅሷል፡፡ 

“የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ” የተባለላቸው አሊ በርኬ ከ11 ዓመታት በላይ የእስር ቤት ቆይታቸው በኋላም ከሚገባቸው ክብር ይልቅ በተቃራኒው አገርን ነጻ ባወጡበት ትከሻቸው ድንጋይን ተሸክመው በቀን ስራ ህይወታቸውን መግፋታቸውን አብሮት የታገሉ በቁጭት ያነሳሉ፡፡ የሻለቃ አሊ በርኬ ጓደችም ጀግና ባሉት ሰው ፍጻሜ የተደበላለቀ ስሜት ይሰማቸዋል፡፡ “ለአገር የዋለውን ውለታ ያህል መከበር ሲገባው በስርዓት ለውጥ ብቻ የደርግ ወታደር በሚል ታርጋ ዋጋ ከፍሏል” ያሉት የአሊ ጓዶች “በስተመጨረሻም እንዲህ ያለ የጀግና ክብር አሸኛኘት መደረጉ ደስታን የሚሰጥ” ብለውታል፡፡  

የካራማራው ጀግና ሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ በመጨረሻም በዛሬው እለት ስርዓተ ቀብራቸው ሲፈጸም የጀግና ክብር ተሰጥቶአቸው የአገር መከላከያ ተወካዮች፣ የቀድሞ ሰራዊት ጓዶቻቸው እና ቤተሰብ ወዶጆቻቸው በተገኙበት በመንበረ ጸባዮች ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቀብራቸው በደማቅ ስርዓት ተፈጸመ፡፡ የ72 ዓመቱ አሊ የሰባት ልጆች አባት ነበሩ፡፡

ሥዩም ጌቱ

ታምራት ዲንሳ

ነጋሽ መሐመድ