1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

የ“ሶልቭ ኢት” የፈጠራ ውድድር አሸናፊዎች

ረቡዕ፣ ነሐሴ 15 2011

ባለፈው ዓመት የተጀመረው “ሶልቭ ኢት” የተሰኘ ሀገር አቀፍ የፈጠራ ውድድር ዘንድሮም ተካሂዷል። በ15 ከተሞች ለወራት ሲካሄድ የቆየው ውድድር ባለፈው ቅዳሜ ነሐሴ 11 ቀን 2011 በአዲስ አበባ ተጠናቅቋል። በማጠቃለያ ስነስርዓቱ ላይም የሀገር አቀፍ ውድድሩን የአሸነፉ ሶስት ፕሮጀክቶች ከ100 እስከ 25 ሺህ ብር ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል።

https://p.dw.com/p/3OI4U
2019 Solve IT national innovation competition
ምስል US Embassy Addis Ababa

የ“ሶልቭ ኢት” የፈጠራ ውድድር አሸናፊዎች

መንበሩ ዘለቀ እና መልካሙ ታደሰ ይባላሉ። የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የዘንድሮ ተመራቂዎች ናቸው። ከአምስት አመት ልፋት በኋላ ጥቁር ጋዋን ለመልበስ፣ መነሳነስ የተንጠለጠበት ቆብ ለመጫን መብቃታቸው ብቻ አይደለም የእዚህ አመት ስኬታቸው። በመላው ኢትዮጵያ ካሉ በሺህዎች ከሚቆጠሩ ወጣቶች ጋር ተወዳድረው ባስመዘገቡት አመርቂ ውጤትም ስማቸው ከፍ ብሎ ተጠርቷል።

እነ መንበሩ ያሸነፉበት ውድድር “ሶልቭ ኢት” (Solve IT) ስያሜ አለው። ባለፈው ዓመት የተጀመረ ሀገር አቀፍ የፈጠራ ውድድር ነው። ሁለት ሺህ ያህል አመልካቾችን መሳብ የቻለው የእዚህ ዓመት ውድድር በመላው ኢትዮጵያ ባሉ 15 ከተሞች ለወራት ሲከናወን ቆይቷል። በየከተማው ሲደረግ የቆየውን ውድድር በበላይነት በማጠናቀቅ አዲስ አበባ ላይ ለተደረገው የመጨረሻው ዙር ውድድር ማለፍ የቻሉቱ 63 ፕሮጀክቶች ብቻ ናቸው። 

2019 Solve IT national innovation competition
ምስል iCog Labs/Solve IT

በባህር ዳር ካሉ ተፎካካሪዎቻቸው ብልጫ አሳይተው ወደ አዲስ አበባ የመጡት መንበሩ እና መልካሙ ድላቸውን በሀገር አቀፍ ደረጃም ደግመውታል። ሁለቱ ወጣት ተወዳዳሪዎች የ100 ሺህ ብር ሽልማት ያስገኘላቸው የ“ስሪ ዲ” (3D) ማተሚያ ማሽን ነው። በባህርዳር ዩኒቨርስቲ የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል ተማሪ የነበሩት መንበሩ እና መልካሙ የማሽኑን ሀሳብ የጠነሰሱት ለውድድር ብለው አልነበረም። በዩኒቨርስቲ ማጠናቀቂያቸው ለመመረቂያ የሚሆን የፈጠራ ስራ ማቅረብ ስለነበረባቸው የወጠኑት ፕሮጀክት ነው።

መልካሙ ፈቃደ የተባለ ሌላ የትምህርት ክፍላቸውን ተማሪ ጨምረው ስራውን የጀመሩት ዕጩ ተመራቂዎች የ“ሶልቭ ኢት”ን የውድድር ጥሪ ይመለከታሉ። ከዚያ በኋላ በአራት ወራት ውስጥ ለውድድሩም፤ ለመመረቂያውም የበቃ ማሽን መስራታቸውን መንበሩ ይናገራል። 

ተመራቂ ተማሪዎቹን ለሽልማት ያበቃቸው የ“ስሪ ዲ” ማተሚያ ማሽን ከዚህ ቀደም ያልነበረ አዲስ ፈጠራ አይደለም። ቻርለስ ደብሊው ሁል በተሰኙት የፈጠራ ሰው አማካኝነት የተፈበረከው የመጀመሪያው የ“ስሪ ዲ” ማተሚያ ማሽን  እንኳ ሰላሳ አምስት አመት ደፍኗል። ያኔ አገልግሎት ላይ የዋለው ማሽን ከ100 ሺህ ዶላር እና ከዚያ በላይ የሚያወጣ፤ ዋጋው ለተራው ተጠቃሚ የማይቀመስ ነበር። አርባ እና ሃምሳ ሺህ ብር ይሸጥ የነበረን የ“ስሪ ዲ” ማተሚያ ማሽን በ6,500 ብር ብቻ መስራታቸው የእነርሱን የተለየ እንደሚያደርገው መንበሩ ይናገራል።  

2019 Solve IT national innovation competition
ምስል iCog Labs/Solve IT

እነ መንበሩ በባህር ዳር በነበረው ውድድር ሲያሸነፉ በሀገር አቀፉም ጥሩ ውጤት ሊያስገኝላቸው እንደሚችል ገምተው ነበር። በዚያ ውድድር እነርሱን ተከትለው ሁለተኛ የወጡት ሀና ወርቅነህ እና ዳዊት ጌታቸው የተባሉ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች በሀገር አቀፉም ተመሳሳይ ውጤት ማስመዘገባቸው ግን ያልተጠበቀ ግጥምጥሞሽ ሆኗል። እነ ሀና ለውድድር ያቀረቡት የፈጠራ ስራ የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን ወደ ነዳጅ የሚቀይር ነው። የነዳጅ ዋጋን በ50 በመቶ ለመቀነስ ያስችላል የተባለው ይህ ማሽን ሁለተኛ ደረጃን በመቆናጠጥ ለእነ ሀና የ50 ሺህ ብር ሽልማት አስገኝቷል።

ሶስተኛ በመውጣት የ25 ሺህ ብር ተሸላሚዎች የሆኑት ሃና ጥላሁን እና ሁሜ ደግቤሳ የተባሉ የአዲስ አበባ ተወዳዳሪዎች ናቸው። ሁለቱ እንስቶች ለነፍሰ ጡር እናቶች አገልግሎት እንዲሰጥ የሰሩትን ማሽናቸውን “የእኛ” የሚል ስያሜ ሰጥተውታል። ማሽኑ የምጥ ድግግሞሽ እና ጥንካሬን ለመለካት እንደዚሁም ሊወልዱ የተቃረቡ ነፍሰ ጡሮች የሚያስፈልጋቸውን የመድኃኒት መጠን ለመቆጣጠር የሚያስችል ነው።

የእነዚህን ተወዳዳሪዎች ስራዎች መዝነው ለሽልማት ያበቋቸው በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ ሶስት ኢትዮጵያውያን እና ሁለት ጃፓናውያን ናቸው። ተወዳዳሪዎች ከእነዚህ ዳኞች ፊት ቀርበው ሙያዊ ምዘና ከማግኘታቸው በፊት በአዲስ አበባ በነበራቸው የ12 ቀናት ቆይታ ተገቢው ስልጠና እንደተሰጣቸው የ“ሶልቭ ኢት” ፕሮጀክት አማካሪ ቤተልሔም ደሴ ትናገራለች። ካለፈው ዓመት በተለየ መልኩ ተወዳዳሪዎች ከመጀመሪያው ጀምሮ በስራዎቻቸው ላይ ክትትል እና ድጋፍ ይደረግላቸው እንደነበርም ታስረዳለች። አማካሪዋ “የእዚህን ዓመት ውድድር ለየት የሚያደርጉ ሌሎች ተጨማሪ ነገሮች አሉ” ትላለች።

2019 Solve IT national innovation competition
ምስል iCog Labs/Solve IT

ቤተልሔም በዚህ ዓመት ለውድድር የቀረቡ የፈጠራ ስራዎች ጥራት ከዚህ ቀደም ከታየው ከፍ ብሏል ትላለች። ሆኖም በባለፈው ዓመትም ሆነ በዘንድሮው ውድድር ተደጋግመው የሚመጡ የፈጠራ ሀሳቦችን አስተውላለች። ውድድሩ በተካሄደባቸው ከተሞች ስትዘዋወር ለፈጠራ ባለሙያዎች ማነቆ የሆነም ችግርም ታዝባለች። 

የተሻለ ሀሳብ ይዘው ለመጡ የሀገር አቀፉ ውድድር አሸናፊዎች የሽልማት ገንዘብ ከመስጠት ባሻገር የውድድሩን ፕሮጀክት በሚያስተባብረው “አይኮግ ላብ” በኩል ምን እየተደረገ እንዳለ ቤተልሔምን ጠይቀናት ነበር። ያለፈው ዓመት አሸናፊዎችን በምሳሌነት በመጥቀስ የቅርብ ክትትል እንደሚደረግላቸው ምላሽ ሰጥታለች። በሚቀጥለው ዓመት ህዳር ወር ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው “ሶልቭ ኢት አክስለሬተር” (Solve IT accelerator) መርኃ ግብርም ሀሳባቸው ለገበያ ሊቀርቡ በሚችለው ላይ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ እንዳቀዱም ጠቁማለች። በአዲሱ መርኃ ግብር በውድድሩ ያሸነፉት ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ተወዳዳሪ ሊሳተፍ እንደሚችልም ታስረዳለች። በዚህም ቢሆን ግን አንድ የማይቀር ነገር አለ - ውድድር።

ሙሉ መሰናዶውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ተስፋለም ወልደየስ

አዜብ ታደሰ