1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሙዚቃ

የሶል ሙዚቃ ንግስት - አሪታ ፍራንክሊን

እሑድ፣ ነሐሴ 13 2010

የሶል ሙዚቃ ንግስት በመባል የምትጠራው የ76 ዓመቷ አሪታ ፍራንክሊን ባለፈው ሐሙስ ነሐሴ 10 ቀን 2010 ዓ. ም. አርፋለች። አሪታ ፍራንክሊን ለ40 ተከታታይ ዓመታት የሙዚቃውን ዓለም በዝና የተቆጣጠረች ሴት ነበረች።

https://p.dw.com/p/33OYr
Aretha Franklin gestorben (picture alliance/AP Photo/A. Sancetta)
ምስል picture alliance/AP Photo

የሶል ሙዚቃ ንግስት - አሪታ ፍራንክሊን

አሪታ ሊውስ ፍራንክሊን እንደ ጎርጎሮሳዊው በ1942 ዓ. ም. በዩናይትድ ስቴትስ በቴኔሲ ክፍለ ግዛት ነው የተወለደችው። ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ ሀገራት ያሉ የአንዳንድ ሙዚቀኞች የኋላ ታሪክ ሲታይ የቤተክርስቲያን ዘማሪዎች አንዳንዶቹም ዲያቆናት የነበሩ ናቸው። አሪታ ፍራንክሊንም የቤተ ክርስቲያን ዘማሪ ነበረች። የምትዘምርበት ቦታም ኒው ቤተል ባፕቲስት የተባለ የቤተሰብ ቤተክርስቲያን መሆኑን ታሪኳ ያወሳል። 

ዝነኛዋ አሪታ ፍራንክሊን እንደ ጎርጎሮሳዊው 1967 ዓ. ም.  respect natural women፣ በተከታዩ ዓመት ደግሞ I say a little prayer በተባሉ ዘፈኖቿ ነበር በዘመኑ የታወቀችው። የዚህች የሶል ንግስት ዘፈኖች ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሻገር፣ ለሰዎች ነጻነት እና ለሰብዓዊ ክብር የተዘፈኑ፣ የጥቁር አሜሪካውያን በደል ያወሱ እና የሚያወሱ ናቸው። 

አሪታ ፍራንክሊን ለ40 ተከታታይ ዓመታት የሙዚቃውን ዓለም በዝና የተቆጣጠረች ሴት ነበረች። አሪታ 40 በነጠላ የተለቀቁ እና ዝናን ያጎናጸፏት ዘፈኖች እንዳሏትም በህይወት ታሪኳ ተገልጿል።  ጾታ ሳይለይ ከዓለማችን 100 ምርጥ የሙዚቃ ሰዎች ሲመረጡ ከተጠቀሱት አንዷ ሆና ክብሩን አግኝታለች። አሪታ ፍራንክሊን በነበረባት የካንሰር በሽታ ምክንያት ባለፈው ሐሙስ ነሐሴ 10 ቀን 2010 ዓ. ም. ስታርፍ በቤተሰቦቿ፣ ልጆቿ እና የልጅ ልጆቿ ታጅባ ነበር።

መክብብ ሸዋ

ተስፋለም ወልደየስ