1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስኳር እና የዘይት እጥረት

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 28 2009

ኢትዮጵያ ውስጥ የስኳር እና የዘይት አቅርቦት እጥረት መዲናዪቱ አዲስ አበባን ጨምሮ በአንዳንድ አካባቢዎች የመከሰቱ ዜና በገና ዋዜማም መነጋገሪያ ኾኖ ዘልቋል። በርካቶች የተከሰተውን እጥረት ወደ ቀልድ እና ምጸት ምንጭነት ቀይረውታል።  

https://p.dw.com/p/2VOmQ
Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

የስኳር እና የዘይት እጥረትን በተመለከተ ዋዜማ ሬዲዮ ዘለግ ያለ ጽሑፍ በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ለንባብ ካበቃ በኋላ ርእሰ-ጉዳዩ የበርካታ ሰዎች መነጋገሪያ ኾኗል። የአብዛኞቹ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ጽሑፎች በምጸት እና ቀልዶች የተሞሉ ናቸው። 

ሲቲና ኑሪ በትዊተር የማኅበራዊ መገናኛ ገጿ ያቀረበችው ጽሑፍ፦ አንድ ሰው ፍቅረኛውን ስጦታ ሊያበረክትላት ሲያማርጣት የሚያደርጉት ቃለ-ምልልስን የያዘ ነው። «የኔ ውድ ለልደትሽ ምን ልስጥሽ? የስንብት ቀለማትን?» ሲል የወንድ ጓደኛ ጥያቄውን ያቀርባል።የሴት ጓደኛ «አ አይ» ስትል ትመልሳለች። በነገራችን ላይ የስንብት ቀለማት የአዳም ረታ ረዥም ልቦለድ መጸሐፍ ርእስ ነው። ጓደኛ ጥያቄ ማቅረቡን ይቀጥላል፦ «ያቺ የምትወጃትን ሽቶ?» «አያይ ኖ» የጓደኛ ውትወታ አልተቋረጠም፤ ይቀጥላል «እሺ በቀደም ያየሻትን የኤች ኤንድ ኤም ቦርሳ» እሷ፦ «አ አ አይ እ አንድ ኪሎ ስኳር!» ስትል እቅጩን ትነግረዋለች። ይህን የትዊተር ጽሑፍ ሲቲና ኑሪ «በዚ አይነት ስኳር የጥሎሽ ዝርዝር ውስጥ መግባቱ አይቀርም» የሚል ርእስ ሰጥታዋለች። 

የብዙዎች መነጋገሪያ የሆነውን ርእሰ-ጉዳይ ዋዜማ ሬዲዮ በፌስቡክ እና በትዊተር ገጹ ዘለግ ባለ ጽሑፍ ያስነበበው «አዲስ አበባ በስኳርና በዘይት ሰልፎች ተጨንቃለች» በሚል ርእስ ነው። «በኢህአዴግ መንግሥት ከፍተኛ ምዝበራና የሕዝብ ሐብት ብክነት ተፈጽሞባቸዋል ተብለው ከሚገመቱ በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ዉስጥ የሰባቱ አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች ቅድሚያ እንደሚይዙ በብዙዎች ዘንድ» ይታመናል ሲል አስነብቧል፡፡ 

ጋዜጠኛ ደረጄ ሐብተወልድ  በፌስቡክ ገጹ፦ ከስኳሩ መጥፋት በላይ ፈገግ የሚያሰኘው እነ ወይዘሮ ፋና በጤና ፕሮግራማቸው ከምግቦቻችሁ እና መጠጦቻችሁ ውስጥ ስኳርን አስወግዱ እያሉ ሲመክሩ መሰንበታቸው ነው» ብሏል። 

Zucker
ምስል bit24 - Fotolia

«በሌለ ስኳር  ስኳር አትጠቀሙ የሚል መካሪ ምን ይባላል?» ያለው ደረጄ «ወይዘሮ ፋና አይጨነቁ» እያለ ይቀጥላል። «እነ አባይ ፀሐዬ የስኳር ፕሮጀክቶች ሚኒስትር ሆነው ተሹመውና በትንሹ እስከ ዐስር የሚደርሱ የስኳር ፋብሪካዎችን እንዲተክሉ መቶ ሚሊዮኖች ተመድቦላቸው በቆይታቸው አንድም ፋብሪካ ሳያስተክሉ በጀቱን ( ስኳሩን) ልሰው ስለጨረሱት እንኳን በምግባችን በቡናችን ውስጥ የምንጨምረው ስኳር ስለሌለን አታስቡ በማለት የሙስና ተግባሩን አሳፋሪነት ገልጧል። 

«በአዲስ አበባ በዱቄት እና ዘይት ላይ የተወሰነ የአቅርቦት መዘግየት ተስተውሏል» በሚል ርእስ ዘለግ ያለ ሌላ መልእክት በድረ-ገጽ ያወጣው ደግሞ ለመንግስት ቅርበት ያለው ፋና ብሮድካስቲንግ ነው። ፋና ታኅሣሥ 27 ቀን፣ 2009 ዓም ለንባብ ያበቃው ጽሑፍ፦ በአዲስ አበባ በሚገኙ የሸማች ኅበረት ሥራ ማኅበራት ሱቆች «በዱቄት እና ዘይት ላይ የተወሰነ አቅርቦት መዘግየት» መስተዋሉን ገልጧል። ሆኖም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ለንባብ ከበቃው የዋዜማ ራዲዮ በተቃራኒ ፋና «በተደረገው ቅኝትም በጉለሌ እና በአራዳ ክፍለ ከተሞች አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው የስኳር እጥረት በሚፈለገው ደረጃ መቀረፉን መታዘብ ተችሏል» ብሏል።

ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ የዋዜማን ጽሑፍ በከፊል ነቅሶ በፌስቡክ እና ትዊተር ገጹ አካፍሏል። «ከድሬዳዋ እንደመጣ ለዋዜማ ሪፖርተር የገለጸውና በሞያው መምህር የኾነው አቶ የሺዋስ በሸጎሌ የሸማቾች ማኅበር ከረዥምና እጅግ አታካች ሰልፍ በኋላ ስኳር ለመግዛት ቢሞክርም የቀበሌው ቋሚ ነዋሪ ካልሆንክ አይቻልም በሚል እንደተከለከለ ይናገራል፡፡ የታደሰ የቀበሌ መታወቂያ ወይም ከድሬዳዋ መሸኛ ይዘህ ካልመጣህ ስኳር አንሸጥልህም ብለውኛል ይላል፡፡ ‘ሻይ አፍልቼ ለመጠጣት ኢትዮጵያዊ መኾኔ አይበቃም ወይ? ብላቸውም ሊሰሙኝ ፍቃደኛ አልሆኑም’ ሲል በመገረም የደረሰበትን ያብራራል፡፡ (ግርም ቢለኝ ነው...ወዲህ ለውይይት ያመጣሁት)» ሲል ኢብራሒም ጽሑፉን አጠቃሏል። 

«የስኳር እና ዘይት ግብይት ችግር» በሚል ርእስ ላቀረብነው የሬዲዮ ዝግጅት በዶይቸ ቬለ የአማርኛው ክፍል ፌስቡክ ገጽ ላይ የተሰጡ የተወሰኑ አስተያየቶችን አብረን እንመልከት። አኅላም ሐሳል፦ «ሱኳርን የኢሕአዴግ  ባለስልጣን እና መሰሎቻቸው ይጠቀሙበት እንጂ ድሀ ማገኘት አይችልም» ብሏል። ደምስ ካሴ ደግሞ፦ «እንደዚህ ዓይነት ስኳርና ዘይት አይተንም አናውቅም። እኛ ጋ የሚመጣው ፍግ የመሰለ ስኳርና አተላ የመሠለ ዘይት ነው። ይሄም ጠፍቷል» የሚል አስተያየት ሰጥቷል።
አካልና ጥላ የተባለ የፌስቡክ ተከታታያችን ደግሞ «ፋብሪካዎቻችን??? ለመሆኑ ስንት ናቸው? እሺ ይሁን ግን በውሸት ተጠገበ ህዝብ እስከመቸ ጥጋቡን ይችለዋል??? በወር ለአንድ ቤተሰብ 2 ኪሎ ተመድቦ፤ ከዚያም በላይ ቤት አልባው ህዝብ እንዳያገኝ ታግዶ፡ ከዚያም በላይ ስኳር የሚገዛ ሁሉ ለስለላ ራሱን አጋልጦ መረጃውን በሙሉ ሰጥቶ፡ ከዚያም በላይ ለመናገር ያሳፍራልና ልተወው» የሚል አስተያየት አስፍሯል።

iPad tablet PC Apple
ምስል picture-alliance/dpa

የአዲስ ስታንዳርድ መጽሄት ዋና አዘጋጅ ጸዳለ ለማ፦ በአዲስ አበባ ስኳር እና ዘይት ለማግኘት ያለውን የሰልፍ ውጣ ውረድ ትዊተር ገጿ ላይ በእንግሊዝኛ ባቀረበችው ጽሑፍ እንዲህ ገልጣዋለች። «ለመሰለፍ ትሰለፋለህ። ከዚያም መታወቂያህን ታሳይና ትመዘገባለህ፤ እናም የምግብ ዘይትህን እና ስኳርህን ለማግኘት ትሰለፋለህ» ስትል የሰልፉን አታካችነት አስነብባለች። 

በላይ አዱኛ በትዊተር ገጹ ቀጣዩን አጠር ያለ ጽሑፍ  አቅርቧል። «አባዎራ፤ እስኪ ቡና ስጪኝ የቤት ሠራተኛ፤ ስኳር የለም። አባዎራ፤ ምነው ፖለቲካውን ትተሽ በጨው ብትሰጪኝ»

የዘይት እና የስኳርን ነገር  ሳሙኤል ተሾመ በፌስቡክ ባቀረበው አዝናኝ ጽሑፍ እናጠቃል።  «ስኳርና ዘይት በመታወቂያ» ይላል የሳሙኤል ጽሑፍ ርእስ። «ዛሬ ጠዋት ጨው ብጤ ለመግዛት ሰፈራችን ወዳለው ሱቅ ሄጄ ነበር እና አንድ አሮጊት ሴትዮ ናቸው ሱቁ በራፍ ላይ ቆመው "ማነህ ባለሱቅ እስቲ ሩብ ስኳር ወዲህ በል"ይሉታል። ባለሱቁም መታወቂያ ይዘዋል እማማ ይላቸዋል። ደሞ የምን መታወቂያ አመጣህብኝ? አሉ ሴትየዋ። ባለሱቁም አይ መንግስት ያለመታወቂያ እንዳትሸጡ ብሏል ይላቸዋል። ምን ቢሉ ጥሩ ነው? እኔ ስኳር ሽጥልኝ እንጅ ፊልም አከራየኝ ብየሀለሁ እንዴ!»

በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የተባሉ የመንግስት አመራሮችን ጨምሮ  130 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ስለማስታወቁ  በተለይ ለመንግስት ቅርበት ባላቸው የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች ዘንድ መነጋገሪያ ኾኗል።  

“በጸረ ሽብር ሕግ” ምክንያት በወጣው አዋጅ የ 18 ዓመት እስራት የተበየነበት ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛና አምደኛ እስክንድር ነጋ እንዲሁም የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ምስል በማኅበራዊ መገናኛ አውታርም በስፋት ተዘዋውሯል።

የአቶ በቀለ ገርባ እና የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ምስል በግል የፌስቡክ ገፃቸው በጻፉት ፅሑፍ ለተከሰሱት የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ምስክርነት የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደቀረቡ የተነሳ መሆኑ ተጠቅሷል።  አቶ በቀለ ገርባ ሙሉ ለሙሉ ቢጫ ልብስ ያደረጉ ሲሆን ጋዜጠኛ እስክንድር ሙሉ ጥቁር ልብስ ለብሶ ታይቷል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ