1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስራ እና የገበያ እንቅስቃሴ ማቆም አድማ በኢትዮጵያ 

Merga Yonas Bula
ሰኞ፣ የካቲት 26 2010

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈዉ ዓርብ  ያፀደቀው አወዛጋቢ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ተቃዉሞ ገጥሞታል።

https://p.dw.com/p/2tj82
Äthiopien Jimma Geschlossene Geschäfte
ምስል DW User via Whatsapp

ተቃዉሞዉን ተከትሎ የፀጥታ አካላት ወሰዱ በተባለዉ የኃይል ርምጃ በጭሮ፣ ግንጭ፣ በአምቦ፣ በጉደር፣ በባኮ፣ በነቀምቴ፣ በናጆ፣ በግምብ፣ በደምቢዶሎ፣  እንዲሁም በሌሎች ቦታዎች ሰዎች እንደሞቱ፣ እንደቆሰሉና ንብረት እንደወደመ ከአካባቢው የተገኙ ዘገባዎች ይጠቁማሉ። አዋጁን በመቃወምም ከዛሬ ጀምሮ ሶስት ቀን የሚዘልቅ የስራና የገበያ እንቅስቃሴ ማቆም አድማ መጠራቱ ተሰምቷል።

በዛሬዉ እለት የተጠራዉን አድማ በተመለከተ ዶይቼ ቬሌ አድማው በቀጠለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን ስለሁኔታው አነጋግሯል።

ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አንድ የኢጃጅ ከተማ ነዋሪ፣ «በምዕራብ ሸዋ ዞን በኢሉ ጋላን በኢጃጅ ከተማ ነዉ የምንኖረዉ። እስካሁን ምንም ነገር የለም። ሁሉም ቤታቸዉን ዘግተው ቤት ዉስጥ ነዉ ያሉት። የግብይት ማቆሙን አድማም እያካሄዱ ይገኛሉ። የሚንቀሳቀስ ተሸከርካሪ የለም። የተከፈተ ሱቅ የለም። በከተማዉ ዉስጥ የሚንቀሳቀስ ምንም ነገር የለም።»

በምስራቅ ሃራርጌ ዞን በጭናቅሳን ወረዳ ዉስጥ የሁለተኛ ደረጃ መምህር የሆኑት ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ ግለሰብም የአድማው አንደምታም በአከባቢያቸዉ እየታየ መሆኑን ተናግረዋል፣ « በሃረርጌ አከባቢ ሁኔታው ከዛሬ ከጥዋት ጀምሮ  እስካሁን ድረስ ሁሉም ነገር፣ ምግብ ቤትንና ባንክን ጨምሮ  ዝግ ናቸዉ። ወደ ጥዋት አከባቢ ባንክ ለመክፈት የሞከሩ ነበሩ ፤ ግን እነሱም 20 ደቂቃ ሳይሞላ፣ ከሌላ ቦታ ስልክ ከተደወለላቸው በኋላ  ዘግተዋል።»

በዶይቼ ቬሌ የዋትስአፕ ቁጥር ላይ የፅሁፍ አስተያየት በላኩልን መሰረት፣ ከአዲስ አበባ ወደ በሰበታ በሚወስደው  መንገድ ላይ  ከወለቴ ጀምሮ ሱቆች እና ማንኛውም አገልግሎት ፣ ትራንስፖርትም እንዲሁ ሙሉ በሙሉ ቆሟል፣  ሌሎችም «እኛ አካባቢ አሻዋ ሜዳ ሱቅም መኪናም የለም፣ በተለይ በቀን ገቢ ለምንተዳደር ሰዎች ሁኔታው በጣም አሰቸጋሪ ሆኖብናል» ብለዋል። 

ሁሉም አስተያየት ሰጭዎች ለዚህ አድማ ምክንያት የሆነዉ አሁን የታወጀዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሆኑን ይገልፃሉ።

የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሼን ጉዳዮች አላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ዛሬ ጥዋት በፌስቡክ ገፃቸዉ ላይ ባሰፈሩት መረጃ መሰረት አሁን በቀጠለው ተቃዉሞ የሰዉ ሕይወት ማለፉን አረጋግጠው በዛሬዉ እለትም የስራና የገበያ እንቅስቃሴ አድማ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከማህበረሰቡ ጥያቄ ጎን እንደሚቆም ጠቅሰዉ  ሕብረተሰቡ ስራዉን እየሰራ ጥያቄዉን ለመንግስት ማቅረብ እንዳለበት አሳስበዋል።

የተደነገገዉ «የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ማወክ፤ የህዝብ አገልግሎት ማስተጓጎል፣ ያልተፈቀዱ ሰልፍ» ማድረግና  እና ሌሎች አድማን የሚከለክለው የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከጅምሩም አያስፈልግም፣  ሕጋዊም አይደለም በሚል ብዙዎች አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው።

ሙሉ ዘገባዉን ለማዳመጥ ከላይ ያለዉን የድምፅ ዘገባ ይጫኑ።

መርጋ ዮናስ

አርያም ተክሌ