1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሴቶቹ ሹመት በአቅም ወይስ ለውክልና?

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 6 2011

ጠቅላይ ምኒስትር ዐብይ አሕመድ የካቢኔያቸውን ቁጥር ወደ 20 ዝቅ አድርገው እንደገና ሲያዋቅሩ ከፍተኛ እና ቁልፍ የሚባሉ ሥልጣኖች ላይ እንስቶች ተሾመዋል። ሹመቱ ምሥጋና እና ትችት አላጣውም። የሴቶቹ ሹመት በአቅም ወይስ ለውክልና? ለሚለው ጥያቄ የየራሳቸውን ማብራሪያ ያቀረቡ ባለሙያዎች አሉ። ጠቅላይ ምኒስትሩ ግን በብቃት እንደሆነ ገልጸዋል

https://p.dw.com/p/36eAS
Äthiopien Parlament bestätigt neues Kabinett
ምስል Federal Government Communication Affairs Office of Ethiopia

የሴቶቹ ሹመት በአቅም ወይስ ለውክልና?

ጠቅላይ ምኒስትር ዐብይ አሕመድ የካቢኔያቸውን ቁጥር ወደ 20 ዝቅ አድርገው እንደገና ሲያዋቅሩ ከፍተኛ እና ቁልፍ የሚባሉ ሥልጣኖች ላይ እንስቶች ተሾመዋል። በዛሬው ሹመት መሠረት የኮንስትራክሽን ሚኒስትር የነበሩት የምኅንድስና ባለሙያዋ ወይዘሮ አይሻ መሐመድ የመከላከያ ሚኒስቴርን እንዲመሩ ተሰይመዋል። አዲስ የተቋቋመው የሰላም ሚኒስቴር በቀድሞዋ አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ይመራል። የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት እና የፌደራል ፖሊስን የመሳሰሉ ተቋማት ተጠሪነታቸው ለወይዘሮ ሙፈሪያት ሆኗል። 
ሴቶቹ እነ ማን ናቸው?
ከወይዘሮ ሙፈሪያት እና ወይዘሮ አይሻ በተጨማሪ  ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምኒስትር ሆነው ተሾመዋል።  ወይዘሮ ፈትለወርቅ በምኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከልን ይመሩ ነበር። የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ የነበሩት ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የትራንስፖርትር ምኒስትር ሆነዋል።  ዶ/ር ወይዘሮ ሒሩት ወልደማርያም የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ምኒስትር፣ ወይዘሮ ያለም ጸጋይ አስፋው የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር፣ ዶ/ር ሒሩት ካሳው የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ሆነው ተሾመዋል። የአዳማ ከተማ ከንቲባ፣ የኦሮሚያ የፍትኅ ቢሮ ኃላፊ ሆነው የሰሩት እና በአሁኑ ወቅት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የጽህፈት ቤትን የሚመሩት ወይዘሮ አዳነች አበቤ የገቢዎች ምኒስትር ናቸው። ዶ/ር ፍጹም አሰፋ  የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ተሾመዋል። 

Äthiopien Abiy Ahmed Premierminister
ምስል picture-alliance/AP Photo/Saudi Press Agency

አዲስ የተቋቋመው እና ወይዘሮ ሙፈሪያት የተሾሙበት የሰላም ሚኒስቴር ስም እና ግብር ገና ካሁኑ መነጋገሪያ ሆኗል። በአዲሱ የኢትዮጵያ መንግሥት አወቃቀር መሠረት የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ፣ የፋይናንስ ደኅንነት መረጃ ማዕከል፣ የፌድራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የኢሚግሬሽን ዜግነት እና ወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ፣ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ፣ የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲቲዩት ተጠሪነታቸው ለዚሁ ተቋም ሆኗል። 
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር 

ሚሊዮን ኃይለስላሴ

ሸዋዬ ለገሠ


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ