1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሳማንታ ፓወር የኢትዮጵያ ጉብኝት

ሐሙስ፣ ሐምሌ 29 2013

የአሜሪካ ሰብዓዊ ተራድኦ ድርጅት (USAID) ኃላፊ ሳማንታ ፓወር በኢትዮጵያ ያደረጉትን የሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት ትናንት ሲያጠናቅቁ ማምሻውን ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፤ የሀገራቸው ፍላጎት ከኢትዮጵያውያንና መንግሥታቸው ጋር በመሆን አሁን በአገሪቱ ግጭት ላስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ እልባት መስጠት ነው ብለዋል።

https://p.dw.com/p/3yaci
Äthiopien Die Chefin von USAID  Samanta Power
ምስል Seyoum Getu/DW

ጉብኝታቸውን ሲያጠናቅቁ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል

ዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያን እንደ ጠንካራ አጋር መመልከቷን እንደምትቀጥልና በሀገሪቱም ያለ አድልዎ ሰብዓዊ ድጋፎችን እንደምታደርግ የአሜሪካ ሰብዓዊ ተራድኦ ድርጅት (USAID) ኃላፊ ሳማንታ ፓወር ገለጹ። ኃላፊዋ በኢትዮጵያ ያደረጉትን የሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት ትናንት ሲያጠናቅቁ ማምሻውን ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፤ የሀገራቸው ፍላጎት ከኢትዮጵያውያንና መንግሥታቸው ጋር በመሆን አሁን በአገሪቱ ግጭት ላስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ እልባት መስጠት ነው ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን አግኝተው የመነጋገር ውጥናቸው ባይሳካም ከሰላም ሚኒስትሯ ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል። 

Äthiopien Die Friedens Ministerin Muferiat Kamil
የሰላም ሚኒስትር ሙፋሪያት ካሚልምስል Seyoum Getu/DW

ሳማንታ ፓወር በዋና መዲና አዲስ አበባ አቅራቢያ የሚገኘውን የUSAID ሰብዓዊ ድጋፍ ቁሳቁስ መጋዘንም ጎብኝተዋል። በትግራይ ክልል ያለውን የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት ለማሳካት በሳምንት ከ500 እስከ 600 የርዳታ ቁሳቁስ የጫኑ ተሸከርካሪዎች መግባት አለባቸው ያሉት ኃላፊዋ የርዳታ ሠራተኞች ከዘለፋ ነጻ ሆነው እንዲሠሩ ጥበቃ እንዲደረግላቸው መነጋገራቸውንም አክለዋል። ከዚህም ሌላ የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚልም በበኩላቸው ለጋዜጠኞች የተናገሩት የጠራ መረጃ እንዲይዙ ማብራሪያ እንደተደረገላቸውና በሰሜን ኢትዮጵያ የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ ሁለንተናዊ መሆን እንደሚገባው መስማማታቸውን ገልጸዋል። በአፋር 76 ሺህ እና በአማራ ክልል የትግራይ አዋሳኝ አከባቢዎች 150 ሺህ ዜጎች የመፈናቀላቸው መረጃ ደርሶናል ያሉት ሳማንታ ፓወር በበኩላቸው ያለ አድሎ ድጋፉን ለማድረስ ቁርጠኛ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

ስዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ