1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«የሲዳማን ክልልነት አውጇል፤ የሚቀረው የመንግሥት ድርሻ ነው»-ኤጄቶ

እሑድ፣ ሐምሌ 7 2011

የሲዳማ ወጣቶች ክልላዊ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስፈልጋቸውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን አስታወቁ። የሲዳማ ወጣቶች፣ ያገር ሽማግሌዎች እና በርካታ ታዳሚዎች የሲዳማ ክልል በሚመሰረትበት ሁኔታ ላይ ውይይት አድርገዋል። የኤጄቶ ተወካይ የሆነው ወጣት ጌታሁን ደጉዬ «ኤጄቶ የሲዳማን ክልልነት አውጇል፤ ቀሪው ሥራ የመንግሥት ነው» ሲል ተናግሯል።

https://p.dw.com/p/3M4Gb
Äthiopien Ethnie der Sidama
ምስል DW/S. Wegayehu

ታዳሚዎች የሲዳማ ክልል ይሆናል የተባለ ሰንደቅ ዓላማ ሰቅለዋል

ዛሬ እሁድ ማለዳ በሀዋሳ ሀይቅ ዳርቻ በሚገኘውና ጉዱማሌ ተብሎ በሚጠራው ባህላዊ የመሰባሰቢያ ስፍራ ላይ የተገኙት የሲዳማ የአገር ሽማግሌዎች ውይይቱን የጀመሩት በባህላዊ ጸሎትና ምርቃት ነው  ።

የአገር ሽማግሌዎቹ እና ወጣቶቹ በባህላዊ ስፍራው በሚገኙት የዋርካ ዛፍ ጥላዎች ስር የተሰባሰቡት በብሄሩ አጠራር አፊኒ በሚባለው የምክክር ልማድ መሰረት ነው። 

ሁለቱ ወገኖች በምክክራቸው ውጥረት ባንዣበበት የክልል መዋቅር ጥያቄ ዙሪያ ሀሳብ ተለዋውጠዋል ፣ በመጨረሻም የጋራ ያሉትንም አቋም አንጸባርቀዋል።

ለሲዳማ ህዝብ የራስ መስተዳድር እንደሚታገል የሚገልጸውና ኤጄቶ የተባለው የወጣቶች ቡድን ተወካይ ጌታሁን ደጉዬ ኤጄቶ «ድርሻውን ጨርሷል፤ ክልልነቱን አውጇል። የሚቀረው የመንግሥት ድርሻ ነው» ሲል ተናግሯል።

Äthiopien Ethnie der Sidama
የኤጄቶ ተወካይ ወጣት ጌታሁን ደጉዬምስል DW/S. Wegayehu

የሲዳማ ዞን ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሔድ ከጠየቀ በመጪው ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. አንድ አመት ይሞላዋል። ክልሉን የሚያስተዳድረው ደኢሕዴን የሲዳማን ጨምሮ ክልል ለመሆን በቀረቡ ጥያቄዎች ላይ ውይይት እያደረገ ይገኛል።

በመክክሩ ላይ የተሳተፉ የአገረ ሽማግሌቸ ተወካይ ኤጄቶ የተባለው የወጣቶች ቡድን ያቀረበውን ክልል የመሆን ወሳኔ መቀበላቸውን ገልጸዋል። 

Äthiopien Ethnie der Sidama
ምስል DW/S. Wegayehu

በምክክሩ ማጠቃለያ ላይ ተጨማሪም የፌደራሉንና በቀጣይ የሲዳማ የሆናል ተበሎ የታሰበውን ሰንደቅ ዓላማዎች ግራና ቀኝ የመሰቀል ሰነ ስረዓት ተከናወኗል ።   

በዛሬው ባህላዊ ምክክር ላይ በቡዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችና የሲዳማ የአገር ሽማግሌዎች የተገኙ ቢሆንም ከዞንም ሆነ ከክልል የተወከሉ የመስተዳድር ሃላፊዎች ግን በስፈራው አልነበሩም ።

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

እሸቴ በቀለ