1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሲዳማ ምክር ቤት 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ተጀመረ

ሰኞ፣ መጋቢት 11 2015

የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ማካሄድ ተጀመረ። ለጉባኤው ባለፉት ሰባት ወራት በኑሮ ውድነት ቅነሳ እና በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራቱ ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/4OwXx
Äthiopien | Sidama Versammlungsrat
ምስል Sidama National Regional State President office

«ጉባኤው ለሁለት ቀናት ይዘልቃል»

የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ማካሄድ ጀመሯል። የመንግሥታቸውን የሥራ አፈጻጸም ዘገባ ለጉባኤው ያቀረቡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ባለፉት ሰባት ወራት በኑሮ ውድነት ቅነሳ እና በሥራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራቱን ተናግረዋል። በኑሮ ውድነትና በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የተከናወኑ ተግባራትን መልካም ጅማሬ ያሉት የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው አሁንካለው የችግሩ ስፋት እንፃር ግን ይህ በቂ ባለመሆኑ ከዚህ በላይ ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ማካሄድ ጀመሯል። ምክር ቤቱ መደበኛ ጉባዔውን የጀመረው በርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ የቀረበለትን የሰባት ወራት የሥራ ክንውን ዘገባ በማድመጥ ነው።  ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ባለፉት ሰባት ወራት በግብርና፣ በጤና ፣ በትምህርት እና በመሠረተ ልማት ግንባታዎች ረገድ መንግሥታቸው አከናውኗል ያሏቸውን ሥራዎች በኀሃዝ በማስደገፍ አብራርተዋል።  

በተለይም የክልሉ ዋነኛ ችግሮች በሆኑት በኑሮ ውድነትና በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን አቶ ደስታ አንስተዋል። የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ከኅብረት ሥራ ማሕበራት እና ከገበሬዎች ዩኒየን ጋር በመቀናጀት 1,626 ቶን የምግብ እህሎችን ጨምሮ የተለያዩ የፍጆታ ምርቶች ለሸማቾች እንዲቀርቡ መደረጉንም ተናግረዋል።

በክልሉ አያሻቀበ የሚገኘውን የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስም ተሰፋ ሰጪ ሥራዎች መከናወናቸውን የገለጹት አቶ ደስታ «ኢንተርፕራይዞችን በመጠቀም ባለፉት ሰባት ወራት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ጥረት ተደርጓል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ30 ሺህ በላይ ለሆኑ ሰዎች አዳዲስ የሥራ ዕድል ፈጥረናል። በኢንርፕራይዝ ለተደራጁት ለእነኝሁ ወጣቶች 236 ሄክታር መሬት የሥራ ቦታ ተዘጋጅቶ የተሰጣቸው ሲሆን 76 የማምረቻ ሼዶችንም አቅርበናል። ለኢንተርፕራይዞቹ በመንቀሳቀሻ ወረትነት የሚያገለግል 62.3 ሚሊየን ብር የብድር ካፒታል ከመቅረቡም በላይ በተመቻቸው የገበያ ትስስር አማካኝነት የ132 ሚሊየን ብር  ግብይት ተከናውኗል» ብለዋል።

በርዕስ መስተዳድሩ የሥራ ዘገባ አስመልክቶ በዶቼ ቬለ አስተያየታቸውን የተጠየቁት የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው በኑሮ ውድነትና በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የተከናወኑ ተግባራት መልካም ጅማሬ ናቸው ይላሉ። ይሁንእንጂ ከችግሩ ስፋት እንፃር በቂ ባለመሆናቸው በቀጣይ ከዚህ በላይ ሊሠራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ምክር ቤቱ አስፈጻሚውን አካል ለመቆጣጠር በተሠጠው ሥልጣን መሠረት በርዕሰ መስተዳድሩ  በቀረበው የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ  ጥልቅ ውይይት እንደሚያካሄድበት የዛሬውን የክልሉን ምክር ቤት ውሎ አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ ገልጸዋል።

Äthiopien | Sidama Versammlungsrat
የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት 4ኛ መደበኛ ጉባኤምስል Sidama National Regional State President office

በክልሉ ከልማት ሥራዎች ጎን ለጎን ሙስናና ብልሹ አሥራሮችን በማስተካከል ረገድ መንግሥታችሁ ምን እየሠራ ነው በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ዋና አፈ ጉባኤዋ ሲመልሱ «ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል እንደ አገር የተቋቋመው ኮሚቴ በእኛም ክልል ተቋቁሞ ወደ ሥራ ተገብቷል። አሁን  ጠቅለል ያለውን ሪፖርት ገምግመን ስላልጨረሰን እንጂ በርካታ ጥቆማዎች እየቀረቡ ይገኛሉ። እንደምክር ቤት የቀረቡ ጥቆማዎችን በማጣራት ሙሰኞችን ለፍትህ አካላት ማቅረብ በሚቻልበት ሂደት ላይ የቅርብ ክትትል እያደረግን እንገኛለን» ብለዋል።

ዛሬ የተጀመረው የሲዳማ ክልል 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በርዕሰ መስተዳድሩ በቀረበው የሥራ አፈጻጸም ዘገባ ላይ ተወያይቶ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። በተጨማሪም የመሬት አስተዳድርን ጨምሮ የተለያዩ አዋጆችን አንደሚያጸድቅና ሹመቶችን እንደሚሰጥ የምክር ቤት የውይይት መረሃ ግብር ያመለክታል።

 ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ