1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

“የሲዳማ ህዝብ ራሱን ለማስተዳደር ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ነው” - አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ

ቅዳሜ፣ የካቲት 2 2011

የሲዳማ ህዝብ እራሱን በራሱ ለማስተዳደር የሚያስችለውን ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ አስታወቁ፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ያሉት ዛሬ በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው የኦሮሞና የሲዳማ ሊህቃን የምክክር መድረክ ላይ ነው። 

https://p.dw.com/p/3D3fT
12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

“የሲዳማ ህዝብ ራሱን ለማስተዳደር ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ነው” - አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ በሀዋሳው ስብሰባ ለተሳተፉ ታዳሚያን ባሰሙት ንግግር “የሲዳማ ህዝብ በዚህች አገር ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት ባደረገው አስተዋጽኦ ልክ ተጠቃሚ የመሆን ፍላጎት አለው” ብለዋል፡፡ የሁለቱን ህዝቦች ሊህቃንን ያገናኘው የዛሬው መድረክ “የሲዳማ ህዝብ እራሱን በራሱ ለማስተዳደር ዝግጅት እያደረገ ባለበት ወቅት [መካሄዱ] ልዩ ያደርገዋል” ሲሉም አክለዋል፡፡ 

የዛሬ የሀዋሳው የምክክር መድረክ ዓላማ “ሁለቱን ህዝቦች የሚወክሉ ፖለቲከኞች ልምዳቸውን ለመጋራት እና በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ሀሳብ ለመለዋወጥ” እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በውይይት መድረኩ ላይም አንጋፋና ወጣት ፖለቲከኞች ተሳትፈዋል፡፡ በቅርቡ በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ ወደ አገር ቤት የገቡት የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) እና የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) መስራቾች እና አመራሮች የውይይቱ ተሳታፊዎች ነበሩ።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ  “በኢትዮጵያ አሁን የተገኘው የፖለቲካ ለውጥ አዲስ የኢትዮጵያዊነት ፍልስፍና የተገኘበት ነው” ብለዋል፡፡ “ቀደምሲል የነበረው ኢትዮጵያዊነት ከዝንጉርጉርነት ይልቅ አንድ አይነት ቀለም የሚታይበት ነበር” ያሉት አቶ ሌንጮ “ከዚህ በኋላ ማንነትህን ከደጅ ጥለህ ኢትዮጵያዊ ትሆናለህ የሚለው አካሄድ ተቀባይነት የለውም” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። 

ሌላው የመድረኩ ተናጋሪ የኦዴግ አመራር አቶ ሌንጮ ባቲ በበኩላቸው “ወጣቶች ማለቂያ በሌለው ተቃውሞ ውስጥ በመግባት አሁን የተገኘው የፖለቲካ ምህዳር እንዳይበላሽ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል። ወጣቶች “በተለይም የሚያዳምጥ መንግስት ሲገኝ ጥያቄዎችን በሰከነ እና ሰላማዊና በሆነ መንገድ ማቅረብ እንደሚገባቸው” ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ 

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ተስፋለም ወልደየስ