1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን ታጣቂዎች ጥቃት በምዕራብ ጎንደር

ሐሙስ፣ ግንቦት 19 2013

የሱዳን ታጣቂዎችና በሱዳን ይደገፋሉ የተባሉ የኢትዮጵያ አማፂያን ምዕራብ ጎንደር ዉስጥ በተለያዩ አካባቢ የሚገኙ የእርሻና የከብት ማርቢያ ማዕከላትን ማቃጠልና መዝረፋቸዉን መቀጠላቸዉ እየተነገረ ነዉ።

https://p.dw.com/p/3u4Ij
Äthiopien - Gonder
ምስል DW/A. Mekonnen

በጥቃቱ የኢትዮጵያ አማፂያንም አሉበት ይባላል

የሱዳን ታጣቂዎችና በሱዳን ይደገፋሉ የተባሉ የኢትዮጵያ አማፂያን ምዕራብ ጎንደር ዉስጥ በተለያዩ አካባቢ የሚገኙ የእርሻና የከብት ማርቢያ ማዕከላትን ማቃጠልና መዝረፋቸዉን መቀጠላቸዉ እየተነገረ ነዉ። ሐብት ንብረታችን ተዘረፈ ወይም ተቃጠለ የሚሉ ባለሐብቶች፣ ነዋሪዎችና ባለስልጣናት እንዳሉት ታጣቂዎቹ ከባለፈዉ ዕሁድ አንስቶ መተማ ወረዳ የሚገኝ አንድ ቀበሌን  ወርረዉ የአንድ ባለሐብትን የተለያዩ ንብረቶች አቃጥለዋል ወይም ዘርፈዋል።  ከሱዳን ታጣቂዎች ጋርም ሌሎች ኢትዮጵያውያን ተቃዋሚ ኃይሎች ተባብረው ጥቃት መሰንዘራቸውንም የአካባቢው ነዋሪዎች ተመናገራቸው የባሕርዳሩ ወኪላችን ዓለምነዉ መኮንን የላከልን ዘገባ ይጠቁማል። 

የሱዳን ታጣቂዎችና ሌሎች በሱዳን ኃይሎች የሚታገዙ አካላት በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ቱመት መንዶካ በተባለ ቀበሌ ባለፈው እሁድና ትናንትና ጥቃት አድርሰው ንብረት መዝረፋቸውንና ማቃጠላቸውን የአካባቢው የግብርና ባለሀብቶች፣ ነዋሪዎችና የቀበሌው አስተዳደር አስታወቁ፡፡ ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ የሱዳን ታጣቂዎች በምዓራብ አቅጣጫ ደንበር አልፈው ወደ ኢትዮጵያ ግዛት በመግባት ጥቃቶችን በማድረስ ዘረፋ እንደሚፈፅሙና፣ ንብረትም እንደሚያቃጥሉ ቀደም ሲል የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ አመለክቷል፡፡ በሚያደርሱት ጥቃትም የበርካታ ባለሀብቶች ንብረት የወደመና የተዘረፈ ሲሆን የባለሀብቶችን የእርሻ ቦታም ወርረው በመያዝ ከአካባቢው አፈናቅለዋል፣ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የቀን ሰራተኞችም ተበትነዋል፡፡

ባለፈው እሁድ እነኚሁ ታጣቂዎች ቱመት መንዶካ ቀበሌ ሀስክኒትና እንዲብሎ በተባሉ አካባቢዎች ዘረፋና በንብረት ላይ ቃጠሎ መፈፀማቸውን ጉዳቱ የደረሰባቸው ባለሀብት አቶ ሞገስ ተሻገር ለዶይቼ ቬለ በስልክ ገልፀዋል፡፡ እንደ አቶ ሞገስ 600 ከብቶች፣ 120 ዘር ጥጥ ፍሬ፣ 50 ዘር ማሽላ፣ 14 ኩንታል ሰሊጥ፣ 100 በግ፣ 100 ዶሮዎች ተዘርፈዋል፡፡ 7 ቆርቆሮ የሰራተኛ ቤቶች አንድ መጋዝን ተቃጥሏል ብለዋል፡፡ አንድ የዓይን እማኝ ይህ ድርጊት በአካባቢው መፈፀሙን መስክረዋል፡፡ ሌላው የአካባቢው ነዋሪ እንዳሉት ለመላው ኢትዮጵያ ማምረት የሚችል ለም መሬት በአካባቢው እንዳለ ጠቁመው ግን የአካባበው አርሶ አደሮች በከፍተኛ ስጋት ላይ በመሆናቸው ወደ ስራ ለመግባት ተቸግረዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በአካባቢው ችግሩን እየፈጠሩ ያሉት የሱዳን ኃይሎች ብቻ ሳይሆኑ እንዳንድ የኢትዮጵያን መንግስት የሚቃወሙ ኢትዮጵያዊያን ታጣቂዎችም አሉበት ነው ያሉት አስተያየት ሰጪው፡፡ በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ የቱመት መንዶካ ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ ዓለሙ አወቀ በቀበሌያቸው የተጠቀሱት ታጣቂዎች ባለፈው እሁድና ከትናንት በስትያ ጥቃት ማድረሳቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ታጣቂዎቹ ሱዳናውያንና በሱዳን ኃይሎች የሚደገፉአንዳንድ ተቃዋሚ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ ዓላማቸውም የኢትዮጵያን መንግስትና ህዝብ በጉልበት እናንበረክካለን የሚል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የምዕራብ ጎንደር ዞን የስራ ኃላፊዎች ተጨማሪ አስተያየት እንዲሰጡኝ በተደጋጋሚ ብደውልም ስልካቸውን ማንሳት አልቻሉም፤ አንዳንዶቹ ደግሞ መረጃ በስልክ መስጠት አፈልጉም፡፡

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዓለምነው መኮንን