1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱማሊያ ነፃነት 60ኛ ዓመት

ቅዳሜ፣ ሰኔ 27 2012

ሶማሊያ ረቡዕ ሰኔ 24 ቀን፣ 2012 ዓ.ም 60ኛ ዓመት የነፃነት በዓሏን አክብራለች። ሰኔ 24 ቀን፣ 1952 ዓ.ም በጣሊያን እና ብሪታንያ ቅኝ ግዛት ውስጥ ለአንድ ምእተ ዓመት ግድም ሲማቅቊ የቆዩ የሶማሊያ ግዛቶች ተዋሕደው ሶማሊያ ነጻነቷን ያወጀችበት ቀን ነበር።

https://p.dw.com/p/3emJN
Somalia Luftansicht von Mogadischu
ምስል Getty Images/AFP/T. Smole

በነፃነት ማግስት ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ተዘፍቃለች

ሶማሊያ ከጣሊያን እና ብሪታንያ ቅኝግ ግዛት የተላቀቀችበትን 60ኛ ዓመት የነፃነት በዓሏን ረቡዕ ሰኔ 24 ቀን፣ 2012 ዓ.ም አክብራለች። ብሪታንያ የሶማሊያ ከፊል አካልን በቅኝ ግዛቷ የያዘችው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1884 ነበር። አምስት ዓመት ቆየት ብሎ ደግሞ ጣሊያን ከፊል የሶማሊያ አካባቢዎችን ቅኝ ገዝታለች። ኹለቱ የሶማሊያ ግዛቶች የዛሬ 60 ዓመት ከተዋኻዱ አፍታም ሳይቆይ ነበር ሶማሊያ ወደጎሳ እና መንደር በወረደ የእርስ በእርስ ግጭት የተዘፈቀችው።

ሶማሊያን የእርስ በእርስ ጦርነት ሲያምሳት ከሦስት ዐስርተ ዓመታት በላይ ተቆጥሯል። አለመረጋጋት እና ሽብር ሶማሊያ ከኹለቱ የአውሮጳ ቅኝ ገዢዎች ነፃ ከወጣችበት ጊዜ አንስቶ ቀፍድዶ ይዟታል። አድብቶ ገዳዮች እና የመንገድ ዳር ቦንብ ፍንዳታዎች በሶማሊያ የተለመደ ክስተት ከኾነ ዓመታት ተቆጥሯል። ወደ 15 ሚሊዮን  አካባቢ የሚጠጋው የሶማሊያ ነዋሪ በእርስ በእርስ ግጭት በዋናነት በአልሸባብ ጥቃት ሕይወቱ በስጋት የተዋጠ ነው።

በሶማሊያ እስላማዊ መንግስትን ለማቋቋም የሚታገለው አልሸባብ የተባለው ታጣቂ ቡድን ሀገሪቱ ውስጥ ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶችን ይሰነዝራል። ቡድኑ እስከአኹን ሶማሊያ ውስጥ አደረሳቸው ከተባሉት ጥቃቶች ከሦስት ዓመት ግድም በፊት ሞቃዲሾ ውስጥ ፈንጂ በታጠቊ ከባድ ተሽከርካሪዎች የተፈጸመው እልቂት ይጠቀሳል። በወቅቱ ዋና ከተማዪቱ ሞቃዲሾ ውስጥ በተከታታይ የደረሱ የተሽከርካሪ ፍንዳታዎች ቢያንስ 512 ሰዎችን ገድለዋል። 312 ሰዎችን ለከባድ እና ቀላል የመቊሰል አደጋ ዳርገዋል። ከዓመታት በፊት ለተፈጸመው ከባድ ፍንዳታ አልሸባብ ኃላፊነቱን ባይወስድም የሶማሊያ መንግስት ግን ቡድኑን ተጠያቂ አድርጓል።

የሶማሊያ ፕሬዚደንት ሞሐመድ አብዱላሂ ሞሀመድ  ወይንም ፋርማጆ
የሶማሊያ ፕሬዚደንት ሞሐመድ አብዱላሂ ሞሀመድ  ወይንም ፋርማጆ ምስል Getty Images/AFP/M. Haji Abdinur

የዛሬ 60 ዓመት ሶማሊያ ነፃነቷን እንዳወጀች ቀውስ ውስጥ ለመዘፈቅ ብዙም አልቆየች። ከነጻነት በኋላ በ9ኛው ዓመት የሀገሪቱ ፕሬዚደንት አብዲራሺድ ዓሊ ሼርማርኬ በግል ጠባቂያቸው ላሳኖች የተባለችው ከተማ ውስጥ ሲገደሉ ዚያድ ባሬ የጦር ሰራዊቱ አዛዥ ነበሩ።

ከቅኝ ግዛት ነፃነት በኋላ የሶማሊያ ኹለተኛ ፕሬዚደንት የነበሩት ሼርማርኬ በተገደሉ በስድስተኛው ቀን የጦሩ አዛዥ ሜጄር ጀኔራል ጃሊ ሞሐመድ ዚያድ ባሬ አብዮታዊ ጠቅላይ ምክር ቤቱን እየመሩ መፈንቅለ መንግስት ፈጸሙ። ሶማሊያዊው ጋዜጠኛ ሞሐመድ ኦዶዋ መፈንቅለ መንግሥቱ የተመረጠ የሲቪል መንግሥትን አስወግዶ የጭቆና አገዛዝ በር ከፋች እንደነበር ለዶይቸ ቬሌ እንዲህ ይናገራል።

«መፈንቅለ መንግስቱ ዚያድ ባሬ በጦር አበጋዞች እና የተለያዩ ጎሣዎች አማጺ ቡድኖች እስኪባረሩ ድረስ የጭቆና ስርዓታቸው እና አምባገነንነት ዘመናቸው መንደርደሪያ ነበር።»

የሶማሊያ ፖለቲካ ተንታኝ ሞሀመድ ሀጂ ሑሴን በበኩላቸው ሶማሊያን ወደ እርስ በእርስ የተራዘመጦርነት የዶላት የጎሳ ፖለቲካ መኾኑን ይናገራሉ።

የሶማሊያ ፕሬዚደንት የነበሩት ሜጄር ጀኔራል ጃሊ ሞሐመድ ዚያድ ባሬ ከ20 ዓመት በፊት ግድም በሪያድ
የሶማሊያ ፕሬዚደንት የነበሩት ሜጄር ጀኔራል ጃሊ ሞሐመድ ዚያድ ባሬ ከ20 ዓመት በፊት ግድም በሪያድምስል picture-alliance/dpa

«ጎሳና ጎጥን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ መጠነ ሰፊ የፍትኅ እጦት፤ ሰቆቃ፤ የውስጥ ሽኩቻ፤  በጦሩ አፈንጋጭነት እና በኋላ ላይም ምንም አጀንዳ የሌላቸው የጎሣ ቡድኖች መፈልፈልን አስከትሏል።»

እነዚህ ጉዳዮች ሶማሊያን በቀጣይ እጅግ ከባድ ዋጋ አስከፍሏታል። ዚያድ ባሬም ቢኾኑ በአብዛኛው ለዘብተኛ ያልኾኑ ሙሊሞች በሚበዙባት ሶማሊያ «ሳይንሳዊ ሶሻሊዝም» ፖለቲካን እከተላለሁ ማለታቸው ውድቀታቸውንካፋጠኑ ጉዳዮች እንደ አንዱ ይጠቀሳል። ኢትዮጵያ ላይ ወረራ ለማካኼድ ደፍረው በኢትዮጵያውያን ሀገር ወዳዶች የደረሰባቸው ብርቱ ምት ውድቀታቸውን አጣድፎታል።

የጦር አበጋዞች እና የጎሳ መሪዎች ሶማሊያን ወደ ሽብር እና የትርምስ ሀገር መርተዋት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲያልቊ ሰበብ ኾነዋል። ሚሊዮኖችም ከቀዬያቸው በእርስ በእርስ ግጭቱ ተፈናቅለዋል። ዋና ከተማዪቱ ሞቃዲሾ ውስጥ እዚህ እዚያም የተወታተፉ መጠለያዎች እንደሚበዙ ይነገራል። ሶማሊያ የተንኮታኮተች ሀገር ተብላ ቆይታም ጊዜያዊ የፌዴራል መንግስቱ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2004 መሰረት እስኪይዝ ድረስ ከ1991 እስከ 200 ባሉት ጊዜያት ተደጋጋሚ ጊዜያዊ መንግስት ለማቆም ተሞክሯል። 

Karte Infografik Somalia Al-Shabab EN

በ2006ም አኹን በሶማሊያ ጥቂት ቦታዎች የተወሰነው አልሸባብ ወጣት ክንፍ የነበረበት እስላማዊ የሸሪዓ ፍርድ ቤት ኅብረት (ICU) የተባለው ቡድን ሞቃዲሾን እና በርካታ ግዛቶችን ተቆጣጥሮ ነበር። የኢትዮጵያ ጦር እና የአፍሪቃ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ቡድን ለሶማሊያ የሽግግር መንግስት ምስረታ ብርቱ አስተዋጽዖ ማበርከታቸው ይነገራል።

ዛሬም ድረስ ግን ከእስላማዊ የሸሪዓ ፍርድ ቤት ኅብረት የወጣው እና በአረቢኛ «ወጣቶቹ» የሚል ትርጉም ያለው አልሸባብ የተባለው ቡድን በተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶችን በመሰንዘር ላይ ይገኛል። ሞሐመድ አብዱላሂ ሞሀመድ  ወይንም ፋርማጆ በመባል የሚታወቊት ፖለቲከኛ የሶማሊያ ዘጠነኛ ፕሬዚደንት ኾነው ያገለግላሉ። ዛሬም ድረስ ግን የሶማሊያ መንግስት በአፍሪቃ ኅብረት እና ዓለም አቀፍ ለጋሾች ድጋፍ ቆሞ ይገኛል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ