1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስአፍሪቃ

የሰው ልጅ አይኖች በቴሌስኮፗ አይኖች ላይ ተስፋ ሰንቀዋል

ረቡዕ፣ ጥር 11 2014

ለፈው የጎርጎርሳዊው ታኅሣስ 25 ቀን 2021 የአጽናፈ ዓለሙን ያለፈ ታሪክ ለምድራችን ቀረብ ብለው በሚገኙ ኮከቦች ላይ ምርምር የማካሄድ ተልዕኮ የተሰጣት የናሳዋ ጄምስ ዌብ ቴሌስኮፕ ተልዕኮዋን በተሳካ ሁኔታ ጀምራለች ። የዓለማችን ግዙፏ ቴሌስኮፕ በእርግጥ እስከ ዛሬ ከተሠሩ ቴሌስኮፖች ሁሉ ለየት  ተደርጋ ነው የተሠራችው ።

https://p.dw.com/p/45iSi
Weltraumteleskop James Webb
ምስል NASA GSFC/CIL/dpa/picture alliance

የናሳዋ ጄምስ ዌብ ቴሌስኮፕ ተልዕኮ እና የተጣለባት ተስፋ

የማያውቁት ሀገር አይናፍቅም ከሚለው ብሂል የወጣው እና እየረቀቀ የሄደው የሰው ልጅ አዕምሮ  ከማያውቀው ዓለም የማያውቀውን ነገር ማሰስ ከጀመረ ዉሎ አደረ ። ከምድር ማህጸን እስከ ቅርብ ህዋ ነገር ዓለሙን በሩቁ ከመበርበር እስከ በአካል ተገኝቶ ዳስሶ እና ጨብጦ መረዳትም ተራምዷል። የሰው ልጅ ህልሙ ሩቅ ነው ፤ ጥያቄውም ብዙ ። በአጽናፈ ዓለም ውስጥ መሬት በተባለች ፕላኔት ላይ እርሱ ብቻውን እየኖረ ይሆን ? ለሰው ልጅ መኖርያነት የሚበጅ ሌላስ ምድር ይኖር ይሆን ? ከሰው ልጅ ውጭስ በሌሎች ዓለማት እርሱ (የሰው ልጅ ) ያላወቃቸው ወይም ያልደረሰባቸው ሌሎች ፍጥረታት ይኖሩ ይሆን ? ጥያቄው ብዙ ነው ። መልሱ ግን እንዲሁ አይመለስም ፤ቀላልም አይደለም ፤ አጽናፈ ሰማያትን መፈተሽ ፤ የፍጥረተ ዓለማትን የኋላ ታሪክ መለስ ብሎ ማየት ብዙ ብዜ ይጠይቃል። ጤና ይስጥልን አድማጮቻችን በዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዝግጅታችን በቅርቡ ወደ ህዋ በመጠቀችው እና በሰው ልጅ የህዋ የምርምር ታሪክ አንድ እርምጃ ታራምዳለች ተብሎ ተስፋ በተጣለባት የናሳዋ ጀምስ ቴሌስኮፕ ተልዕኮ መጀመርዋን በተመለከተ ከብዙ በጥቂቱ እንመለከታለን ፤ መልካም ቆይታ

NASA James Webb Space Teleskop
ምስል NASA/abaca/picture alliance

ባለፈው የጎርጎርሳዊው ታኅሣስ 25 ቀን 2021 የአጽናፈ ዓለሙን ያለፈ ታሪክ ለምድራችን ቀረብ ብለው በሚገኙ ኮከቦች ላይ ምርምር የማካሄድ ተልዕኮ የተሰጣት የናሳዋ ጄምስ ዌብ ቴሌስኮፕ ወደ ጠፈር ከተላከች በኋላ ተልዕኮዋን በተሳካ ሁኔታ ጀምራለች ። 10 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገባት የዓለማችን ግዙፏ ቴሌስኮፕ በእርግጥ እስከ ዛሬ ከተሠሩ ቴሌስኮፖች ሁሉ ለየት  ተደርጋ ነው የተሠራችው ። በተልዕኮዋም በቀጣዮቹ አስር ዓመታት ውስጥ በህዋ የምርምር ታሪክ ምናልባትም አዳዲስ የምርምር ሥራዎችን በማከናወን የሰው ልጅ ስለ አጥናፈ ዓለም ያለውን ዕውቀት ከፍ ታደርጋለች  ተብሎ ተስፋ ተጥሎባታል።

USA Das neue Weltraum-Teleskop James Webb Space Telescope
ምስል NASA/ZUMAPRESS.com/picture alliance

ለመሆኑ የጄምስ ዌብ ቴሌስኮፕ ዋናው ተልዕኮዋ ምንድነው ? መድረሻዋስ የት ነው ? ተመራማሪዎችስ እንዴት ይሆን የሚቆጣጠሯት ? ለጥያቄዎቹ ምላሽ ይሆኑ ዘንድ ከቴሌስኮፑ ሥራ ጀምሮ ያለውን ለአፍታ እንመልከት።

ጄምስ ቦንድ ቴሌስኮፕ ምንም እንኳ የአሜሪካው ግዙፉ የህዋ ምርምር ማዕከል ናሳ ባለቤትነት በሚከናወን ግዙፍ ፕሮጀክት አማካኝነት የተሠራች ቢሆንም በዓለም ዙርያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እና በርካታ ተቋማት ተሳታፊ ሆነውበት ከሦስት አስርት ዓመታት ከተሻገረ ምርምር እና ሥራ በኋላ ለተልዕኮ ዝግጁ ሆናለች።

ከአሜሪካ ውጭ የካናዳ እና የአውሮጳ የጠፈር ተመራማሪ ተቋማት መሐንዲሶች የተሳተፉበት ይኸው ግዙፍ የምርምር ፕሮጀክት አዲሱን ቴሌስኮፕ ቀደም ሲል በሥራ ላይ ከነበረው ሐብል ቴሌስኮፕ በ100 እጅ ነገሮችን አጉልታ እንድታሳይ እና ተጨማሪ የምርምር ግብዓቶችን እንድታቀርብ ተደርጋ ተፈብርካለች።

Illustration | James Webb Space Telescope
ምስል D. Ducros/ESA/dpa/picture alliance

በማር እንጀራ ቅርጽ በወፍራም ቢጫ አንጸባራቂ መስታወት የተሠራችው ቴሌስኮፗ ከምድር 1.5 ሚሊዮን ኪሎ ሜትሮችን ርቆ ወደ ተዘጋጀላት የመዳረሻ ጣቢያዋ እያመራች ነው። ተልዕኮው ከወሰደው የዝግጅት ዓመታት ፤ የተመራማሪዎች የሰላ አዕምሮ እንዲሁም ከፈሰሰበት መዋዕለ ነዋይ አንጻር ስኬታማነቱን በስጋት እና በጉጉት የሚጠባበቁት ጥቂቶች አይደሉም  ።

የቴሌስኮፗ ተልዕኮ በሰው ልጅ የምርምር ታሪክ በከፍተና ደረጃ የሚጠበቅ መሆኑን የሚገልጹት በአሜሪካ ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ መምህር የሆኑት  ፕሮፌሰር አብረሃም ሎኤብ የጀምስ ዌብ ቴሌስኮፗን ተልዕኮ በከፍተኛ ደረጃ ተጠባቂ እንዲሆን በርካታ ምክንያቶች ሊጠቀሱ እንደሚችሉ ያስረዳሉ።

« በብዙ ምክንያቶች ተልዕኮው ተጠባቂ እንዲሆኑ አድጓል። ከእነዚህ ውስጥ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል የምርምር ማዕከሉ እንዲሆን የታቀደለት ስፍራ ከምድር ከ1.5 ሚሊዮን ኪሎ ሜትሮች በላይ ርቆ መገኘቱ ነው።  ይህ ደግሞ የቀድሞው ግዙፉ ሐብል ቴሌስኮፕ ከሚገኝበት የምርምር ማዕከል ከ3,000 እጅ በላይ ርቆ የሚገኝበት ስፍራ መሆኑ ነው። ይህን ማድረጉ የምርጫ ጉዳይ ስለሆነ አይደለም ። እስካሁን በተደረገው ምርምር የተገኘው ውጤት እና የምርምሩ ትክክለኛነት መሳርያውን እዚያ ድረስ አርቆ መላኩ አስፈላጊ ስለሆነም ጭምር ነው። »

Frankreich Kourou | Start der Ariane 5 Rakete mit James Webb Space Telescope
ምስል NASA TV/AFP

የአጽናፈ ዓለም መጀመርያ የት መቼ እና እንዴት ለሚሉ ጥያቄዎችም ቴሌስኮፗ መልስ ለመሻት ቀደምት ከዋክብትን በጥልቀት በመፈተሽ ከአንዳች መደምደሚያ ላይ ለመድረስ ተስፋ የሰነቀች እንደሆነም ጭምር ነው ፕሮፌሰር አብረሃም የሚናገሩት።

« ቴሌስኮፗ ጥልቅ የህዋ ምስሎችን የመስብሰብ ተልዕኮ ተሰጥቶታል። ይህም በመቶ ሚሊዮኖች ዓመታት የሚቆጠር ዕድሜ እንዳለው በሚገመተው ህዋ ውስጥ የመጀመርያውን ኮከብ ፤ የመጀመርያውን ጋላክሲ ፣ እንዲሁም እያደረግን በምንገኘው ሳይንሳዊ ምርምሮች ውስጥ ለቀዳሚው ብርሃን መነሻ የሆነው ክስተት መቼ እና እንዴት ተከሰተ   ለሚሉ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ዕድሉን ያሰፋልናል።»

ጄምስ ዌብ ከማረፊያ ጣቢያዋ ለመድረስ 29 ቀናትን እንደሚወስድባት ይጠበቃል። ዛሬ 24 ቀኗ ላይ ደርሷል። በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ ረዥሙን መንገድ ታገባድዳለች ተብሎም ይታሰባል። በተያዘላት ጊዜ የተላከበት ስፍራ መድረስ ከቻለች ዓመታትን ተሻግሮ ለመጣው የተመራማሪዎች ልፋት ምዕራፍ ሁለት ስኬት ታጎናጽፋለች ማለት ነው።

NASA Weltraumteleskop - James Webb Space Telescope
ምስል NASA/AP/picture alliance

በእርግጥ ሥራው እጅግ አድካሚ፣ ትዕግስት የሚጠይቅ ፣የሰው ልጅ የአዕምሮ ውጤት የላቀ ደረጃ ስለመድረሱ ማሳያ ቢሆንም ቀጣዩ ምዕራፍ የበለጠ ልፋት ፣የበለጠ ትዕግስት የሚጠይቅ ምናልባትም በትውልድ ቅብብሎሽ ዘመን ተሻጋሪ የምርምር ሥራ ሊሆን እንደሚችል ከምርምሩ መነሻ ጀምሮ የታለፉ ሂደቶች ማሳያ ናቸው።

አጽናፈ ዓለም እጅጉን ረቂቅ ፣ ጥልቅ ፣ መጀመርያ እና መጨረሻ የሌለው አልፋ እና ዖሜጋ ነው። የምድርን ግዝፈት ፣ የተፈጥሮ ረቂቅነት እየኖርንባት፣እያየናት፤ እየጨበጥናት ፣ እያሸተትናት እና እየቀመስናት በእርግጥ ገና በቅጡ አላወቅናትም። ይህ በእንዲህ እያለ ታዲያ እንዴት ተደርጎ ከእኛ በብርሃን አመታት ርቀው የሚገኙ ዓለማትን መመርመርስ ይቻለናል፤ ለዚያውም መቶ ሚሊዮን ዓመታትን ወደ ኋላ ተመልሶ ፍጥረተ ዓለምን ለማወቅ በውኑ ይቻላልን ? ጀምስ ዌብ ቴሌስኮፕ በጉዞ ላይ ናት ።

NASA Weltraumteleskop - James Webb Space Telescope
ምስል NASA/AP/picture alliance

 

ጋዜጠኛ እና የስነፈለክ ተመራማሪ የሆነችው ኤልሳቤት ቤርሶን በበኩሏ  በጉዞ ጀምስ ዌብ ላይ ያላትን ምልከታ ስትናገር ፤

«ከአስርት ዓመታት ላላነሰ ጊዜ በህዋ እና ስነ ፈለክ ጉዳዮች ላይ ስዘግብ ቆይቻለሁ። በቆይታዬ የሰው ልጅ በዚህ ረገድ ያሳየውን እመርታ ማየት ችያለሁ። ይህ ደግሞ ሰዎች በዙርያቸው ባለው ሕዋ ውስጥ ምን እየተካሄደ እንዳለ ለማወቅ እየተደረገካለው ጥረት የመነጨ እንደሆነ ነው። ነገር ግን ይህ ታላቅ ተልዕኮ ሲከናወን የሰውልጅ የበለጠ የማወቅ እና በሚከናወኑ ነገሮች ዙርያ ያለው ሂደት ምን እየሆነ እንደሁ የበለጠ ለማወቅ ይጓጓል ፤ ከዚህ የተነሳ ስለስኬቱ ሁሉም ይጨነቃል። » ብላለች። 

በ18 ጠንካራ እና ግዙፍ ወርቃማ መስታወቶች የተሠራችው እና እንደጎርጎርሳዊው አቆጣጠር ከ1961 እስከ 1968 የአፖሎ 11ን የህዋ ጉዞ ተልዕኮ በመራው ጀምስ ኤድዊን ዌብ ስም የተሰየመችው ቴሌስኮፑ ፤በአንድ ነጸብራቀ ምስል ተቀባይ መሳርያ አማካኝነት እጅጉን ርቆ ምናልባትም እስካሁን ከተደረሰባቸው መረጃዎች አንድ እርምጃ የተራመደ መደምደሚያ ላይ ሊያደርሱ የሚችሉ መረጃዎችን ትሰበስባለች ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

በዓለማችን እጅጉን ግዙፍ ከተባሉ መርኃ ግብሮች አንዱ እንደሆነ የተነገረለት የህዋ ምርምር መሳርያው ሥራው ገና ያኔ የዛሬ 26 ዓመታት አካባቢ ሲጀመር ገፍቶ ዛሬ ይደርሳል ብሎ የገመተ ሰው ስለመኖሩ መረጃ የለም። ሥራው ሲጀመርም 500 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነበር ተመድቦለት የነበረው ። በጎርጎርሳዊው 2007 ተጠናቆ ወደ ህዋ እንዲመጥቅም ነበር ዕቅዱ የተዘጋጀው። ሲጠናቀቅ ግን ገንዘቡ በ20 በመቶ አድጎ 10 ቢሊዮን ብር ጨርሶ ፤ ከተያዘለት የማጠናቀቂያ ጊዜ 14 ተጨማሪ ዓመታት ወስዶ፣  ከምርምር ተቋሙ በተጨማሪ የሌሎች ኃያላን ሃገራት ጠበብትን ተሳትፎ ጠይቆ በመጨረሻም በስኬት መጠናቀቅ ችሏል።

NASA Entfaltung zweiter Spiegelflügel James Webb Space Telescope
ምስል Bill Ingalls/NASA/AP/picture alliance

ጀምስ ዌብ በህዋ ውስጥ የሚደርስባትን ሙቀት ቅዝቃዜ ፤ ግጭት ተቋቁማ ሚሊዮን ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጣ ከመዳረሻዋ ለመድረስ ህዋን እየቀዘፈች ነው። የወዲያኛውን አለም አቅርበው ለማየት የቋመጡ የሰው ልጅ ዓይኖች በቴሌስኮፗ ዓይኖች ላይ ተስፋቸውን ጥለዋል። በአጽናፈ ሰማያት መሐል ባለችው ትንሿ መሬት ላይ ብቻችንን ነን ወይስ እና የማናውቃቸው ሰማየ ሰማያትን ተሻግረው ሌሎች ይኖሩ ይሆን ? ጥያቄውን ሸጉጣ ጉዞዋን የተያያዘችው ቴሌስኮፗ ስለመመለሱ ለጊዜው እርግጠኛ አይደለንም ። ቀናት ፤ ወራት ምናልባትም አመታት ልንጠብቅ ግድ ሊለን ይችል ይሆናል። ደግሞስ ማን ያውቃል ፤ይሄ ትውልድ የጠየቀው ጥያቄ ሳይመለስ ትውልድ ሊተካም ይችል ይሆናል። ጥያቄ፤ ምርምር ፤ በምዕራፍ የተከፋፈለ ስኬት ጥረቱ ይቀጥላል። የሰው ልጅ መጀመርያውን እየጠየቀ ወደ መጨረሻው መጓዙ ግን የተፈጥሮ ሕግ ነው እና ይቀጥላል። ለዛሬ በዚሁ ይብቃን ሳምንት በሌላ መሰናዶ እንጠብቃችኋለን፤

ታምራት ዲንሳ 

ሸዋዬ ለገሰ