1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰርገኞች ወር

እሑድ፣ የካቲት 10 2011

በኢትዮጵያ የጋብቻ ሥነ-ስርአት እንደ ማህበረሰቡ የኑሮ ሁኔታ ሃይማኖታዊና ልማድን ተከትሎ ይከናዉናል። በተለይ በጥር ወርና በየካቲት ወር መጀመርያ የትዳር መስራቾች ቁጥር ከወትሮው ጨምሮ በመታየቱ፤ ጊዜዉ በሰርግ ወቅትነት ይታወቃል።

https://p.dw.com/p/3DTi4
Äthiopien Hochzeitszeremonie
ምስል DW/Yohannes Gegziabher

መዝናኛ፦ የሰርገኞች ወር

ከ 80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች በሚኖሩባት በኢትዮጵያ የጋብቻ ሥነ ስርዓቱ እንደ  ማኅበረሰቡ ባህልና ልማድ የተለያየ ነዉ። ያም ሆኖ በባህልም ይሁን በዘመናዊዉ ሥርዓት ጋብቻ ሕጋዊ የአንድነት  ስምምነት ነዉ። በአብዛኛዉ ሰው በኑሮ ይስማማኛል ያለዉን ሐሳቡን እና  ችግሩን የሚጋራው፤ የሕይወት አጋሩን መርጦ ጋብቻ ይመሠርታል። ጋብቻው ማኅበራዊ ዝግጅት ከመሆን የበለጠም ትርጉም አለው።

በኢትዮጵያ በተለይ በጥር ወርና በየካቲት ወር መጀመርያ የትዳር መስራቾች ቁጥር ከወትሮው ጨምሮ በመታየቱ፤ ጊዜዉ በሰርግ ወቅትነት ይታወቃል። በቅርቡ ልትሞሸር ዝግጅት ላይ የምትገኘዉ ሳምራዊት ተገኝወርቅ ትባላለች። ሳምራዊት ለ«DW» ቃለ መጠይቅ ልትሰጥ ስትዘጋጅ ልትዳር የቀራት 10 ቀናት ነበር። ሳምራዊት ለሰርጓ ለ6 ወታት ተዘጋጅታለች። «ዝግጅቱ እንዴት ነው የሚሆነው የሚለው ያስጨንቃል። ደስታ አለው። ያገኘሽ ሰው ሁሉ ይደሰታል።»

ሌላዉ ሰርገኛ ፈይሰል ኡስማን ይባላል። እሱም እንዲሁ ለሰርጉ ሦስት ቀናት ሲቀሩት ነበር ቃለ ምልልስ የሰጠን። ፈይሰል እንደሚለዉ ከሆነ ቀለል ባለ ድግስ ነዉ የጋብቻ ሥነ ስርዓቱን መፈፀም የሚፈልገዉ። ለዚህ ምክንያት ፈይሰል የሚሰጠዉ ምክንያት ካለዉ የኢኮኖሚ አቅም እንደሆን ተናግሮአል። «የአቅም ጉዳይ ስለሆነ ሰርጌን ዝግጅት በቀላሉ ነው የማደርገው። አብዛኛው ሰዎች ሰርግን ሲያስቡ ወጭውን ፈርተው ለማግባት ይቸገራሉ» አሁን አሁን እየተለመደ የመጣው የሰርግ ዝግጅት እቅድ አውጭ በተለምዶ «wedding Planner» ይባላል።

Äthiopien Unternehmer Preis 2016 - Mihret Mitiku
ምስል Mercy Décor

አብርሃም በቀለ «wedding Planner»  ወይም የሰርግ እቅድ አዉጭ ነዉ። አብርሃም በሞያዉ ለሰርጉ የሚያስፈልጉ ነገሮችን የት ማግኘት እንደሚቻል ምክር ይሰጣል። አብርሃም የሰርጉን አዳራሽ ከማስዋብ እስከ ሰርጉ ዝግጅት ፍጻሜ ያሉትን ሁሉ ክንዉኖች እንደሚሰራ ገልጾልናል። በአጠቃላይ የሰርገኞችን ሀሳብ ቀለል በማድረግ፤ ሰርጉም የተቃና ሆኖ እንዲያልፍ እናደርጋለን ይላል አብርሃም በመቀጠል። «ሰርጉ የተቃናና መልካም ሆኖ እንዲያልፍ ማድረግ ነው። አብዛኛው ሰው ለሰርጉ የሚያስፈልገውን የት ማግኘት እንደሚችል አያቅም። የተጋቢዎቹን የሰርግ ወጭ እቅዳቸውን ካወቅን በሃላ አገልግሎቱን በዛ ሁኔታ ማግኘት እንዲችሉ እናስተካክላለን።»

በውቀቱ ሰው መሆን የባህልና የሰርግ ዘፋኝ ነው። የሰርግ ዝግጅት ከሙሉ ባንድ ጋር ይሰራል። በሰርግ ዝግጅት የሰርግ ዘፋኝ መሆን ትልቅ ሀላፊነት መሆኑንም ይናገራል። የተሰጠውን ሀላፊነት ለመወጣት፤ ሰርገኞቹም ደስተኛ ሆነው እንዲያሳልፉ ተጠንቅቆም እንደሚሰራ ነዉ የሚናገረዉ። «ሰርግ ፕሮግራም ስይዝ ከአንድ ዓመት በፊት ነው የምዘጋጀው። ትልቅ ሃላፊነት ነው። ሰርግ ማለት ሀላፊነት የምወስድበት ያቺ አንድ ቀን ከተበላሽች ስንት ዓመት ያሰብነው ከንቱ የሚሆንበት ነው። ስለዚህ ተጠንቅቀን ነው የምንሰራው።»

እንደባለሙያዎቹ አስተያየት የአዲስ ትዳር መስራቾቹ ፍቅር የፈካ እና የደመቀ፣ ዘመናትን የተሻገረ መሆን የሚችለው ያለመጠባበቅ ኃላፊነት ወስደዉ መስራት ሲችሉ ነው፡፡ ደስተኛ ትዳር በቀን ውስጥ በትናንሽ ንግግሮች እና የጥሩ ሃሳብ ልውውጦች የተሞላ ነውም ይላሉ።  

ነጃት ኢብራሂም
አዜብ ታደሰ