1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰሜን ሸዋ ግጭትና የሚነደው ፓርክ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 4 2011

ኢትዮጵያ በስተሰሜን ሰላም አጥታ ሰንብታለች። በተራራ፥ ጉድባዎቿ ጥይት ሲጮኽ፤ ከባድ መሣሪያ ሲያጓራ መክረሙ ተነግሯል። በርካታ ሰዎቿ ለሞት ተዳርገዋል። ቦንብ እየተወረወረ የቤተ ክርስትያን ጣራ መነደሉን የሚያሳዩ የቪዲዮ ምስሎች ተሰራጭተዋል። በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የሰሜን ተራራ ብሔራዊ ፓርክ በእሳት እየተንቀለቀለ ነው።

https://p.dw.com/p/3GdZq
Blutbrust-Paviane
ምስል picture-alliance/blickwinkel/C. Lundqvist

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ኢትዮጵያ በስተሰሜን ሰላም አጥታ ሰንብታለች። በተራራ፥ ጉድባዎቿ ጥይት ሲጮኽ፤ ከባድ መሣሪያ ሲያጓራ መክረሙ ተነግሯል። በርካታ ሰዎቿ ለሞት ተዳርገዋል። ቦንብ እየተወረወረ የቤተ ክርስትያን ጣራ መነደሉን የሚያሳዩ የቪዲዮ ምስሎች በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ተሰራጭተዋል። የሰሜን ሸዋ ነዋሪዎች ከአቅማቸው በላይ የኾነ ታጣቂ ከባድ ጉዳት እንዳደረሰባቸው ገልጠዋል። የመንግሥት ታጣቂዎች አድልዎ ፈጽመውብናል ሲሉም ተደምጠዋል። በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የሰሜን ተራራ ብሔራዊ ፓርክ በእሳት እየተንቀለቀለ ነው። ብርቅዬ አራዊቱ ለከፋ ጉዳት ተዳርገዋል። ይኽንኑ የሚያሳዩ ምስሎች እና መልእክቶች በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ተሰራጭተዋል። መንግሥት የጥላቻ ንግግር ላይ ረቂቅ አዋጅ ማዘጋጀቱን ዐስታውቋል።

ሰሞኑን በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በጦር መሣሪያ በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እና የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች ገልጠዋል። የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድማገኘሁ በበኩላቸው ለዶይቸ ቬለ(DW) በዚህ ሳምንት ረቡዕ በሰጡት ቃለ መጠይቅ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 27 መድረሱን፤ ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊጨምር እንደሚችል ስጋታቸውን አካፍለዋል።

Karte Äthiopien englisch

ሌሎች የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች ግን ቊጥሩ ከዚህም በላይ ነው ይላሉ። ከመካከላቸው አንዱ ቢኒ ቢኒ የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «አጣዬና ማጀቴ ብቻ ከ35 በላይ ነው። አጣዬ እስካሁን እኔ የማቀው 18 ሰዎች ሞተዋል። ማጀቴ ደግሞ 17 ሰዎች ነው የሞቱት። ካራቆሪና ቆሪሜዳ ያለቀስ ሰው» በማለት የሟቾች ቊጥር በርካታ መኾኑን ጠቅሰዋል።

«ቁርጥ ነው ዘንድሮ» የተባሉ ሌላ የፌስ ቡክ ተጠቃሚም የሟቾቹ ቊጥር ከፍተኛ እንደኾነ ጽፈዋል። «እስኪ ትክክለኛውን ቁጥር ተናገሩ። ማጀቴ ብቻ በአንድ ቀን 17 ሰው ተቀብሯል። በጥቅሉ በቆሪሜዳ፣ ካራቆሪ፣አጣዬ እና ማጀቴ 45 ሰው በላይ ሞቷል» ብለዋል። አስተያየት ሰጪ የፌስቡክ ተጠቃሚዎቹ የአካባቢው ነዋሪ መኾን አለመMኾናቸውን አልገለጡም።

የጠቅላይ ሚንሥትር ጽ/ቤት በማኅበራዊ መገናኛ አውታር ገጾቹ ባሰራጨው የብሔራዊ ፀጥታ ምክር ቤት መግለጫ ላይ፦ «በግጭቱ ሕይወታቸውን ላጡ» የሚል ሐረግ ይነበባል።

«በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ውስጥ ግጭት የለም፤ እየተፈፀመ ያለው ጥቃት ነው!» ሲል የቴዲ አየለ‏ በትዊተር አስተያየት ሰጥቷል። «በእሳት መጫወት ይቁም መንግስት ኦነግን በግልጽ ያውግዝ። ኦነግን ከመንግስት መዋቅር ያጽዳ! በወሎ እና በሰሜን ሸዋ ኦነግ የሽብር ጥቃት ፈጽሟል» ሲል አዲስ ኅብስት የተባለ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚ ጽፏል። ወርቊ ፈረደ ደግሞ፦ «አብይ አህመድ ኦነግ እስከሙሉ ትጥቁ እንዲገባ አደረገ። ሌሎች ታጣቂ ኃይሎች ትጥቅ ፈትተዉ ገቡ። ለምን ኦነግ ከነትጠቁ ገባ?» የሚል አስተያየት አስነብቧል። 

መንግሥቱ ዲ አሰፋ በትዊተር ባሰፈረው ጽሑፍ፦ «በወሎ እና ሰሜን ሸዋ እየደረሰ ያለው ሕይወት መጥፋት እና ንብረት ውድመት አስቸኳይ መፍትሔ የሚሻ አደገኛ ሁኔታ ነው። ኢትዮጵያ ሁላችንንም ለማቀፍ ምንም አያንሳትም፤ ጠባቦች እና የግጭት ነጋዴዎች አበሳችንን እያበዙት ሁነው እንጂ» ብሏል።

የሰሜን ተራራ ብሔራዊ ፓርክ ቃጠሎ

በተባበሩት መንግሥታት የትምሕርት፤ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (UNESCO) በቅርስነት የተመዘገበ የሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ካለፈው ሳምንት አንስቶ በእሳት እየነደደ መኾኑ በርካቶችን ያሳሰበ ጉዳይ ነው። አያሌው መንበር በትዊተር ገጹ፦ የአካባቢው ነዋሪዎች እሳቱን ለማጥፋት እየተረባረቡ መኾናቸውን ጽፏል። ባያያዘው የቪዲዮ ምስል ላይም፦ ደረቊን ሳር በፍጥነት እየለበለበለ የሚገሰግሰውን የእሳት ነበልባል ለማጥፋት የሚረባረቡ በርካታ ሰዎች ይታዩበታል።

«ትኩረት ለሰሜን ተራራ» በሚል የሚንደረደረው የትዊተር ጽሑፍ የፍሬ ስቴይን አላይቭ ነው። «ባህልህ ቅርስህ ታሪክህ መንፈሳዊ እሴቶችህን አጥተህ አገርም ሆነ ብሔር አለኝ ልትል አትችልም። በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ቅርሶቻችንን መጠበቅ መቻል አለብን» ይላል ጽሑፉ።

Bildergalerie Rote Liste des gefährdeten Welterbes (Nationalpark Simien)
ምስል picture alliance/Robert Harding

«በልጅነታችን እየተማርን ያደግነው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፖርክ ዳግሞ በእሳት እየተቃጠለ ነው። ከጎረቤት ሀገርም ቢሆን የእሳት አደጋ ማጥፊያ ትብብር ጠይቆ እሳቱ ቢጠፋ እንስሳቶቹም ይትረፋ ያሳዝናል በጣም» ሲል ቊጭቱን ትዊተር ላይ የገለጠው አብዱረሂም መድረሳ ነው።

ይርጋ ገላው፦«በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የሰሜን ተራራ እየነደደ ነው። እሳቱን ለማጥፋት መንግሥት ምን እየሠራ እንዳለ የሚያውቅ ይኖርን?» ሲል ጠይቋል በትዊተር ጽሑፉ። በባሕልና ቱሪዝም ሚንስቴር የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ አባተ ለዶይቸ ቬለ (DW) ሲናገሩ፦«የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በሳምንት ጊዜ ውስጥ በጣም ከፍተኛ በኾነ ደረጃ ቃጠሎው የተስፋፋበት ኹኔታ ስላለ ከኬንያ ሔሊኮፕተሮች ለማምጣት ጥረት እየተደረገ ነው» ብለዋል።

ኾኖም ሐሙስ ምሽት የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከኾነ፦ ኬኒያ በገዛ ፓርኳ ላይ በተነሳ እሳት ምክንያት በአፋጣኝ ሔሊኮፕተር ለኢትዮጵያ መላክ አለመቻሏን ጠቁማለች። ደቡብ አፍሪቃ እና ፈረንሳይ እሳት ማጥፊያ ሄሊኮፕተር ለመላክ መዘጋጀታቸው ተሰምቷል።

በፌስቡክ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል ደግሞ ረመሳን መሐመድ፦ «በጣም ነው ሚያሳዝነው። ማንም ሳይንከባከበው፤ ይህን የመሰለ ተፈጥሮ፤ በእሳት ሲጋይ ማየት፤ ልብ ይሰብራል። እባካችሁ የሚመለከተው ሁሉ ታደጉልን» ብሏል።

በረከት ጃጄ ደግሞ፦ «የሰሜን ብሔራዊ ፓርክ እየተቃጠለ ነው!!! ከፖለቲካም፣ከዘርም ከምንም በፊት ሰባዊነት ይቀድማል። እንሳሳት እየተቃጠሉ ነው እባካችሁ ሁላችንም ለሚመለከተው እናሳውቅ። መንግስት ለፖለቲካ ብቻ ነው መግለጫ የሚያወጣው?እንስሳት ይጣራሉ!! እኔም ይመለከተኛል እንበል!!» ይላል። 

Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

የጥላቻ ንግግርን በተመለከተ ሰሞኑን በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች የወጣው ረቂቅ አዋጅ የበርካቶች መነጋገሪያ ለመኾን አፍታም አልወሰደበትም። ረቂቊን በትዊተር የመገናኛ አውታር ገጻቸው ለንባብ ያበቊት የኢትዮጵያ ፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የኮሙኒኬሼን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ዝናቡ ቱኑ ናቸው።

ረቂቊን በተመለከተ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል ኢትዮጵያ ሞመንት በሚል የትዊተር ስም የቀረበ ጽሑፍ፦ «አዲዮስ ዲሞክራሲ! የጥላቻ ንግግር ሕግ ረቂቅ ቀረበ፤ ኦዴፓ ሕዝብ ለማፈን ዝግጅቱን አጠናቀቀ ማለት ነው!» በሚል ይነበባል። ያህኮል በተባለ የትዊተር ስም ተጠቃሚ ደግሞ፦ «የጥላቻ ንግግር ሕግ የሚያስፈራው በጥላቻና በሐሰት ዜና ለተጠመዱት ብቻ ነው» ይላል።

«ከጥላቻ ሐውልትና ከጥላቻ ንግግር?» ሲል በጥያቄ የጀመረው ቴዲ ነው፤ በትዊተር ጽሑፉ።  «ጡት ያለው የጥላቻ ሐውልት ይሻለኛል ያለ ይመስላል መንግስት» ብሏል ቴዲ። እጅ ላይ የተቀመጠ ጡት የሚታይበት ግዙፍ ሐውልት ፎቶግራፍ አያይዟል። «የጥላቻ ንግግር ሕግ ከማፅደቃችሁ በፊት በኩራት ያቆማችሁትን የጥላቻ ሐውልት አፍርሱ። ፌስቡክ ሰፈር የተገኘ» በሚል ያስነበበችው እሙዬ ፎኒክስ ናት።

«የጥላቻ ንግግርን ከመቆጣጠራችሁ በፊት ራሳችሁን መቆጣጠር ያሻችኋል» በማለት በእንግሊዝኛ ቋንቋ የጻፈው ዳዊት  ኤም በዛብህ ነው። «ጥላቻን መቆጣጠር ካልቻላችሁ ከጥላቻ ንግግር በባሰ መልኩ ይበልጥ በተለያየ  መንገድ ሊገለጥ ይችላል» ሲል አክሏል። «ከጥላቻ ንግግር በፊት የጥላቻ ሐውልት ይፍረስ!» ዮሐንስ በተባለ ግለሰብ በትዊተር የተሰጠ አስተያየት ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ