1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ አራት ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ 

ሐሙስ፣ መጋቢት 16 2013

ዓለም አቀፉ ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን በትግራይ አራት ሰላማዊ  ሰዎች መገደላቸውን ገለፀ። ቡድኑ በአባላቶቼ ላይም ጥቃት ድሶባቸዋል ብሏል።

https://p.dw.com/p/3rC0l
Logo Ärzte ohne Grenzen Doctors without borders medicins sans frontieres


ድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን በመባል የሚታወቀው ዓለም አቀፍ  የህክምና ዕርዳታ ቡድን ዛሬ ባወጣው መግለጫ በትግራይ አራት ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ  ተመልክቻለሁ፤ በቡድኑ ዓባላቴ ላይም ጥቃት ደርሷል ሲል አመልክቷል።
የዕርዳታ ቡድኑ ይህንን ድርጊት ተመለከትኩ ያለው  በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ለዕርዳታ ስራ በተጓዘበት  ወቅት ሲሆን፤ ጥቃቱ የተፈፀመውም በመቐለና አዲግራት ከተማ መካከል  ነው።ይህ ድርጊት እንደተፈፀመ  ብዙም ሳይቆይ በራሱ ቡድን አባላት ላይ ጥቃት መድረሱንም  አመልክቷል። 
የእርዳታ ቡድኑ የድንገተኛ አደጋ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ካርሊን ክሊይጀር እንደገለጹት፤ ቡድኑ ግልጽ ምልክት በተደረገበት መኪና ውስጥ ይጓዙ የነበረ ቢሆንም ፤መንገድ ላይ አንድ የታጠቀ ቡድን አድብቶ በኢትዮጵያ የጦር ኮንቮይ ላይ ጥቃት ማድረሱንና በርከት ያሉ ተሽከርካሪዎችም በእሳት ሲጋዩ በቅርብ ርቀት መመልከታቸውን ገልፀዋል። 
በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ወታደሮች የድንበር የለሹ የሀኪሞች ቡድን መኪናና እና ከኋላ የሚጓዙ ሁለት መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ መኪናዎችን በማስቆም  ተሳፋሪዎቹ  እንዲወርዱ ካደረጉ በኋላ ከተሳፋሪዎቹ መካከል ሴቶቹ እንዲሄዱ ሲፈቀድላቸው ወንዶቹ ተለይተው ተገድለዋል ብለዋል ሀላፊዋ።
ከዚያ በኋላ የሀክምና እርዳታ ቡድኑ መንገዱን እንዲቀጥል የተፈቀደለት ቢሆንም፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የድንበር የለሽ ሐኪሞች መኪና እንደገና በወታደሮች እንዲቆም ተደርጓል ሲል መግለጫው አመልክቷል። ከዚያም ሾፌሩን በማስፈራራት ከመኪናው እንዲወርድ የተደረገ ሲሆን፤ በመጨረሻም ተፈቅዶለት ቡድኑ ወደ መቀሌ መመለሱን መግለጫው አብራርቷል። 
ቡድኑ በትግራይ እየተካሄደ ባለው ግጭትና ባጋጠመው ክስተት  ባጣም መደንገጡን ገልጾ ፤በዚህ ግጭት ውስጥ ሰላማዋዊ ሰዎችን  በተሻለ ሁኔታ መጠበቅ አስፈላጊነ ነው ብሏል፡፡ የታጠቁ ሀይሎችም  ሰብአዊ እና የህክምና እርዳታን ማክበር አለባቸው ሲል ድርጅቱ  አሳስቧል፡፡ላለፉት አምስት  ወራት በኢትዮጵያ መንግስትና በህዝባዊ ወያነ ሀርነት ትግራይ መካከል የዘለቀውን ግጭትና ጥቃትም ኮንኗል።
በጉዳዩ ላይ ዶቼ ቬለ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በርሊን የሚገኙትን የድርጅቱን የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ሀይከ ዲርባህ ለማነጋገር ጥረት ቢያደርግም በደህንነት ስጋት የተነሳ ቃለመጠይቅ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልፀዋል።

BG Tigray | Mekele
ምስል Maria Gerth-Niculescu/DW

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ