1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሮኬት ፍንዳታ በባሕር ዳርና ጎንደር

ቅዳሜ፣ ኅዳር 5 2013

በባህርዳር እና ጎንደር ከተማ ትናንት ምሽት ለተፈጸሙ የሮኬት ጥቃቶች ሕወሃት ኃላፊነቱን መውሰዱን ዐስታወቀ። ከምሽቱ 4፡45 የተሰሙት ፍንዳታዎች ብርቱ ከመሆናቸው የተነሳ ርእደ-መሬት የተከሰተ ይመስል እንደነበር፤ የባሕር ዳሩ ወኪላችን ዓለምነው መኮንን የላከልን ዘገባ ይጠቁማል።

https://p.dw.com/p/3lI8F
Äthiopien Notstände in Amhara
ምስል DW/J. Jeffrey

በባህርዳር እና ጎንደር ከተማ ትናንት ምሽት ለተፈጸሙ የሮኬት ጥቃቶች ሕወሃት ኃላፊነቱን መውሰዱን ዐስታወቀ።  በባህር ዳር ከተማ ፍንዳታዎቹን ተከትሎ  የጦር መሣሪያ ተኩስ ለ15 ደቂቃ ያህል  ሲሰማ መቆየቱን የባህር ዳሩ ወኪላችን ዓለምነው መኮንን ያነጋገራቸው የዐይን እማኞች ዛሬ ለዶይቸ ቬለ ገልፀዋል። 

ትናንት ምሽት በባህርዳር ከተማ ሁለት ከባድ ፍንዳታዎች ተሰምተዋል፡፡ ከምሽቱ 4፡45 የተሰሙት ፍንዳታዎች ብርቱ ከመሆናቸው የተነሳ ርእደ-መሬት የተከሰተ ይመስል እንደነበር፤  የባሕር ዳሩ ወኪላችን ዓለምነው መኮንን የላከልን ዘገባ ይጠቁማል። ፍንዳታዎቹን ተከትሎም  የጦር መሣሪያ ተኩስ ለ15 ደቂቃ ያህል  ሲሰማ መቆየቱን ገልፆልናል። ዘጋቢያችን ስለደረሰው ጉዳትና አጠቃላይ ሁኔታ ከቦታው ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ሙከራ እያደረግን ነው። በጎንደርም ፍንዳታው መከሰቱ ተዘግቧል።

የሕወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት፦ ስለ ትናንቱ ጥቃት የሚያውቊት ነገር እንደሌለ ገልጠዋል። ኾኖም የሕወሓት መሪዎች «ትግራይን የሚያጠቃ ማንኛውም አየር ማረፊያ ዒላማ ይኾናል» ማለታቸውንም አክሏል። የትግራይ ክልል የመንግሥት ቴሌቪዥን «እኛ ላይ የሚደርሰው ጥቃት እስካልቆመ ድረስ መሰል ጥቃቶች ይቀጥላሉ» ማለቱን ደግሞ አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል። «በባህር ዳር እና ጎንደር የሚገኙ የወታደራዊ ዒላማዎችን መትተናል» ሲሉ የሕወሓት ሥራ አስፈፃሚ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ መናገራቸውንም አክሎ ዘግቧል።

ይኽ በእንዲህ እንዳለ፦ «የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ» የተሰኘው መንግሥታዊ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር በገጹ ላይ ይፋ እንዳደረገው፦ «ትናንት ምሽት ወደ ባሕርዳር እና ጎንደር ሮኬት ተተኩሷል።» በሮኬት ተኩሱም በአውሮፕላን ጣቢያው ላይ መጠነኛ ጉዳት መድረሱን አትቷል። የጉዳት መጠኑ ምን ያኽል እንደኾነ ግን አልዘረዘረም። «ስግብግቡ ጁንታ በእጁ ያሉትን የመጨረሻዎቹን መሣሪያዎች ጠጋግኖ ሞክሯል» ሲልም አክሏል። ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት «መርማሪ ቡድን ተመድቦ እያጣራው» መኾኑን በመግለጥም «በቀጣይ የሚገለጽ ይሆናል» ብሏል።  

Äthiopien Bahirdar Covid19
ምስል DW/A. Mekonnen

የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት በበኩሉ፦ ስማቸውን መናገር ያልፈለጉ አንድ ሐኪም በፍንዳታው «ቢያንስ ኹለት ሰዎች እንደተገደሉ» እንዲሁም «10 ወይንም 15 ሰዎች መቁሰላቸውን»  ከጎንደር ኾነው እንደነገሩት ጽፏል። የአማራ ክልል መንግሥታዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ (አብመድ) ትናንት ምሽት ስለነበረው ፍንዳታ ሲጽፍ፦ «በአሁኑ ሰአት ሁሉም ነገር ሰላም ነው» ብሏል። ትናንት ምሽት ስለተከሰቱት ፍንዳታዎች ቀጣዩን በፌስቡክ ገጹ አስፍሯል።  «ዛሬ ምሽት 5:00 ሰዓት ገደማ በባህር ዳር መኮድ እና በጎንደር አዘዞ አካባቢ በተቀራራቢ ሰአት መለስተኛ  ፍንዳታ እንደተፈፀመ የክልሉ መንግስት ዐስታውቋል» ሲል ትናንት ማምሻውን ያሰፈረው ጽሑፍ ይነበባል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ልደት አበበ