1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የርዳታ አቅርቦትና የርሃብ ወሬ በትግራይ ፤ አየር መንገድ እና የዓለማየሁ እሸቴ ሽኝት

ዓርብ፣ ጳጉሜን 5 2013

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች  በውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ያልተገደበ አስተያየት ሃሳባቸውን የሚያንሸራሽሩባቸው መድረኮች ከሆኑ ሰነባብተዋል። ሃሳብን በነጻነት ለሌሎች የማዳረሻ መንገድነቱ በበጎ ቢታይም፤ የፖለቲካ አቋምም ሆነ የተለያዩ አመለካከቶችን ከማንጸባረቂያነት አልፎ የጸብ አውድማ የሚሆንበት አጋጣሚ እየባሰበት መሄዱ ይታያል።

https://p.dw.com/p/407Cw
Äthiopien Addis Abeba | Muferiat Kamil - Friedensministerin
ምስል Solomon Muchie/DW

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

 ሳምንቱን ጠብቆ ሳይሆን በየዕለቱ አዳዲስ የመወያያ ጉዳዮች የመኖራቸውን ያህል የሚሰነዘሩት አስተያየቶች በአብዛኛው ለመደበኛው መገናኛ ዘዴ የማይመጥኑ የሚሆኑበት አጋጣሚ እንደሚያመዝን ግን መነገር አለበት። ለዛሬ ትግራይ ክልል የረሃብ አደጋ አንዣቧል ጥቂት የማይባሉትን ሕይወት ቀጥፏል እንዲሁም  መንግሥት የሰብዓዊ ርዳታ አቅርቦት ያስተጓጉላል ለሚለው የሰጠውን ምላሽ በሚመለከት ከተሰነዙ አስተያየቶች የተሻሉትን፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሱዳን የጦር መሣሪያ አጓጉዟል በሚል የቀረበበት ክስና አየር መንገዱ የሰጠውን መግለጫ፤ እንዲሁም ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በኢትዮጵያ የሙዚቃው ዓለም የማይደበዝዝ አሻራውን በማሳረፍ በብዙዎች ከሚወደደው ከዓለማየሁ እሸቴ የመጨረሻ ሽኝት ጋር በተገናኘ የተሰጡ አስተያየቶችን በመጠኑ መራርጠናል።

Twitter Logo
ምስል picture-alliance/Zuma/Soma/O. Marques

የተመድ የሰብዓዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ኦቻ ባለፈው ሳምንት እስካሁን ወደ ትግራይ የገባው ከሚፈለገው የሰብዓዊ ርዳታ ከ10 በመቶ ያነሰ፤ ለሥራ ማስኬጂያ ከታሰበው ጥሬ ገንዘብ 2,2 በመቶ ብቻ እንዲሁም ነዳጅ ዘይትም እንዲሁ 28 በመቶው ብቻ ነው ማለቱን የጠቀሱት ሄኖክ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ፤ የነዳጅ እጥረት ወደ ትግራይ የገቡ ትላልቅ ተሽከርካሪዎች እንዳይመለሱ እንቅፋት ሆኗል ካሉ በኋላ፤ በርሃብም በጥይትም የሚያልቁት ወንድም እና እህቶቻችን ናቸው። ከዚህ አዙሪት የምንወጣው በንግግር እና በድርድር ብቻ ነው። ሲሉ፤ መድህኔ የተባሉ ሌላው አስተያየት ሰጪም በዚሁ በትዊተር፤ በከፋ የርሃብ አፋፍ ላይ ናቸው የተባሉት ሰዎች በቃ ሕይወታቸው አልፏል። ጥቂት የሚቀምሱት ያላቸው ደግሞ አሁን በከፋው የረሃብ አደጋ ላይ ናቸው። በማለት ለዓለም የምግብ ድርጅት፣ ለተመድ የሕጻናት መርጃ እንዲሁም ለየተመድ የርዳታ ጉዳይ ኃላፊ ጉዳዩ እንዲደርስላቸው ጠቁመው በትግራይ የከፋ ረሃብ እንዳለ ለመግለጽ ሞክረዋል።

ኢቡፍ ሀቹ የሚል የፌስቡክ ስም ያላቸው ሌላቸው አስተያየት ሰጪም «አዎ መንግሥት የትግራይ ሕዝብ በጦርነት እና በረሃብ እንዲያልቅ እየሠራ ነው።» ይኽንኑ ያስተጋባሉ፤ እያቸው ምናለ በበኩላቸው፤ «የርዳታ ቁሳቁስ እንዳይደርስ የሚከለክሉ እኮ ራሳቸው ጁንታዎች ናቸው። በዚያ ላይ ርዳታ ጭነው የገቡ ሹፌሮችን ይገድላሉ፤ መኪኖችንም እዚያው ያስቀራሉ። ችግሩ የአረመኔው ወገኔ ነው ለሚለው ሕዝብ እንኳን የማይራራው ጁንታው ነው።» ሂዝይ ናስርም እንዲሁ፣ «መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ ብዙ ድጋፍን አድርጓል። ነገር ግን ህወሃት/TPLF ለሕዝቡ ምንም ባለማሰብ ይኽንን ሁኔታ በተደጋጋሚ ሲያስተጓጉል ታይቷል ሆኖም መንግሥት ይኼን ሁሉ ነገር በትዕግሥት በማለፍ ለሕዝቡ ከሚጠበቀው በላዩ ርዳታን ሲያደርግ ነበር።» ነው የሚሉት። ሴና ዳዊትም በፌስቡክ ጁንታው ያሉት ኃይል፤ «ያደረሰብን ሰብዓዊ ጉዳት ይኽ ነው የሚባል ባይሆንም የመንግሥት የሥራ አመራሮች እያደረጉ ያለው ሥራ እንደዜጋ የሚያኮራ ነው« ይላሉ፣ አክለውም፤ «ህዝቡን ለመርዳት ቢፈልግ ቢሆን ኖሮ ጁንታው አማራን እና አፋርን ወርሮ መንገዶችን ባላስተጓጎለ ነበር።» ሲሉም ይወቅሳሉ።  የካቤድ ሰሎሞን ደግሞ፤ «ከምንግዜውም በላይ ከትግራይ ሕዝብ ጎን መቆም ያለብን ወቅት ላይ ነው ያለነው። የትግራይ ሕዝብ በአሸባሪው ቡድን ምክንያት መቸገር የለበትም የሚል እምነት አለኝ። ይኽ ርዳታ ግን ህዝቡ ጋር ሳይደርስ የጁንታው ስንቅ እንዳይሆን መንግሥት አስፈላጊውን ነገር ማድረግ አለበት።» ብለዋል።

Symbolbild Twitter Konto
ምስል picture-alliance/dpa/A. Gombert
Facebook Logo Schritftzug
ምስል picture-alliance/AP Photo/R. Drew

መንግሥት በትግራይ ከሚካሄደውን ውጊያ በተናጠል የተኩስ አቁም ወስኖ ከወጣ በኋላ ወደ ክልሉ የሰብዓዊ ርዳታ እንዳይደርስ ክልከላ ያደርጋል የሚለው ክስ ተቀባይነት የለውም ብሏል። በሳምንቱ መጀመሪያ  የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በሰጡት መግለጫ ትግራይ ውስጥ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ አስተዳደራዊ መዋቅር ባይኖረውም ለትግራይ ሕዝብ ከተለያዩ ረጂ ድርጅቶች ከአንድ መቶ ሚሊየን በላይ ብር ፤ እንዲሁም ከ700 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ዘይት መጓጓዙን ገልጸዋል። ከመንግሥትም ሆነ ከረጂ ድርጅቶች የተገኘ ለሁለት ወራት የሚሆን ምግብ ነክ ርዳታም ትቶ መውጣቱን ነው የገለጹት። ከዚህም ሌላ ከአራት ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ መድኃኒቶችን ጨምሮ ሌሎች ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችም በዚህ ጊዜ ውስጥ መጓጓዛቸውንም ዘርዝረዋል። ሆኖም ርዳታውን ጭነው ወደ ትግራይ ከተጓዙ ተሽከርካሪዎች 72 በመቶው አለመመለሳቸውንም አክለዋል።  ሰሚራ ሙራድ ተስፋ ሰጪ አስተያየት ነው በፌስቡክ ያካፈሉት፤ «የጨለማው ድቅድቅነት የነገን ብሩህነት ያሳያል! ሀገሬ ተስፋ አላት!» ይላሉ። ኢ-ወገንተኛ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ደግሞ፤ «በጣም እውነት ነው። የእኛ ትውልድ ይኽንን የትዕቢት እና የሰቆቃ ሰንሰለት መበጠስ አለበት። ይኽ የሚሆነው «በለው» እና «በሎም» ኋላ ቀር መንደቾe መሆናቸውን የተረዳን ጊዜ ነው።» ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።

Fluggesellschaft Ethiopian Airlines | Frachtflugzeug Boeing 777F
ምስል Nicolas Economou/ZUMA/imago images

በሳምንቱ መጀመሪያ ከወደ ሱዳን የተሰማው ዜና በኢትዮጵያ አየር መንገድ የተጓጓዘ 72 ሣጥን የጦር መሣሪያ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑን አመልክቷል። የኢትዮጵያ አየር መንገድም ወደ ሱዳን ያጓጓዘው የጦር መሣሪያ ሕጋዊ ፈቃድ ያለው ለአደን የሚውል መሆኑን ገልጿል። ይኽን ዜና ካነበቡት አንዱ የሱነህ ወልዴ በፌስቡክ፤ «ታላቅ ስም ያለው አየር መንገዳችንን ለማጥላላት የሚደረግ አካሄድ መሆኑ አይጠፋንም።» ሲሉ፤ እልዬ ተመስገን ደግሞ ጭራሽ አየር መንገዱ ምላሽ የሰጠበትን ዜና ያመኑ አይመስሉም፤ «ይኽ የውሸት ዜና ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድን ስም ለማጠልሸት ወይም ለማበላሸት ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ አያደርገውም።» ነው ያሉት። ለምኑ ፈቃደ መስፍን ደግሞ፤ «አይ አየር መንገድ ከጥቂት ወራት በፊት መሣሪያ እያጓጓዘ ነው ሲባል ከእውነት የራቀ የሀሰት ወሬ ነው ብሎን ነበር፤ አሁን ደግሞ ለአደን የሚውል ነው አለን። ይኹን እስቲ።» ብለዋል። አለማየሁ አሰፋ ደግሞ እንዲህ ይጠይቃሉ፤ «ችግር እያለብን በሱዳን በኩል ማን አጓጉዙ አላችሁ?» ጋዲሳ ተፈሪ በበኩላቸው፤ «ለአየር መንገዳችን ማን ነው ጦር መሣሪያው አደን ቦታ እንጂ ከተማ ውስጥ አይተኮስም ወይም አይሠራም ብሎ የነገረው? መሣሪያውን የሠራው ኩባንያ ወይስ ጠብመንጃው እኔ የአደን ብቻ ነኝ ብሎ ነገራቸው? ምን የሚሉት ማደናገሪያ ይሆን?» ነው ያሉት። ሱዳን የጦር መሣሪያው ወደ ሀገሯ መግባት ለውስጥ ሰላሜ ያሰጋኛል ማለቷን አስመልክተው ሰላም ላለም የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ «እኔ እንደውም ከሱዳን ይልቅ ለኢትዮጵያ ሰላም የሚያሰጋ ይመስለኛል። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ጠላቶች ኻርቱምን መሣሪያ እያደረጉ ስለሆነ።» ብለዋል። ነገሩ ግራ የገባቸው መሆኑን ለመግለጽ የሞከሩት ደግሞ ስማቸውን በአረቢኛ የጻፉ አንድ የፌስቡክ ተጠቃሚ ናቸው፤ እንዲህ ነው ያሉት። «ችግር አስቸጋሪነቱ ቢያስቸግርም ግን እንደ ችግር አስቸጋሪ ነገር የለም፤ ማለቴ አልገባኝም ለማለት ነው።» ቢኒያም አበራ ደግሞ፤ «ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም አሉ አበው።» በማለት አግራሞታቸውን ገልጸዋል።

Äthiopien Beerdigung Sänger Alemayehu Eshete
ምስል Seyoum Getu/DW

ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በኢትዮጵያ የሙዚያ ዓለም የማይጠፋ አሻራውን ያሳረፈው  ድምጻዊ ዓለማየሁ እሸቴ ባለፈው ሳምንት ነበር ድንገት ማረፉ የተሰማው። የ80 ዓመቱ ተወዳጁ የሙዚቃ ሰው በዚህ ሳምንት ብዙዎች አድናቂዎቹ እና ወዳጅ ዘመዶቹ በተገኙበት በደማቅ ስንብት እና ሽኝት ስርዓተ ቀብሩ ተፈጽሟል። በመስቀል አደባባይ የተከናወነውን ስንብት በማኅበራዊ መገናኛው የተመለከቱ አብዛኞቹ በሰላም እረፍ የሚሉ የስንብት አስተያየቶችን በተለያዩ ቋንቋዎች አስተላልፈዋል። ከእነሱ መካከል ቲጂ አድማሱ በፌስቡክ፤ «በሰላም እረፍ፤ የእኛ ዘመን ድንቅ ዘፋኝ።» ሲሉ፤ ፍሰሃ ሙሉጌታ ደግሞ« አሌክስ ይገባሀል ለፍቅር የተፈጥርክ ነህ እንላለን።» ብለዋል። አንዷለም ገዛኸኝ ሀቢቦ በበኩላቸው፤ «ነፍስህን ይማርልን አሌክስ፤ ማን ይሁን ትልቅ ሰው፣ ማሪኝ ብዬሻለሁ እሞትብሻለሁ፣ ወዘተረፈ ዘፈኖችን እየሰማን እንኖራለን፤ አንረሳህም መቼም።» ነው ያሉት። ሱራፌል ታሪኩ ወልደ ኪዳንም፤ «እግዚአብሔር ነፍስህን በገነት ያሳርፋት፣ ለቤተሰቦችህ ለወዳጅ አድናቂዎችህ መጽናናትን እመኛለሁ! አንተ ብታልፍም ተወዳጅ ሥራዎችህ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ ይኖራሉ።» ሲሉ ተሰናብተዋል። ሳምራዊት ኤች ሰመረ ደግሞ፤ «ጨዋ፣ ትዳሩን አክባሪ፣ ፈሪሀ እግዚአብሔር በውስጡ ያለ፤ ታላቅ ሰው፤ ነፍስን በገነት ያኑራት።» ብለዋል። ሚጣ ሚጣ የተባሉ ሌላዋ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ፤ «አይሰው ከንቱ በቃ መጨረሻችን ይኽ ነው!» ሲሉ፤ እውነት ያሸንፋል በበኩላቸው« በስሙ መንገድ ሰይሙለት እባካችሁ!» የሚል ሃሳብ ሰጥተዋል። 

Der äthiopische Sänger und Songwriter Alemayehu Eshete
ምስል Pablo Ruiz Holst

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋኅ መሐመድ