1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳቱ ጉብኝት

ሰኞ፣ መጋቢት 6 2013

የዘመኑ ዴሞክራሲያዊት፣ ልዕለ ኃያል ሐገር ዩናይትድ ስቴትስ ከወረረቻት ከ2003 ወዲሕ የኢራቅ መዋዕለ ዜናም ታሪኳም በጦርነት፣ ሽብር፣ ግጭት የተሞላ ነዉ።ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ባለፉት 17 ዓመታት ስም-መልኩን እየለዋወጠ በቀጠለዉ ጦርነትና ሽብር ከ280 ሺሕ በላይ ሕዝብ አልቋል።ሚሊዮኖች ተሰደዋል ወይም ተፈናቅለዉባታል።

https://p.dw.com/p/3qMc3
Irak Najaf | Besuch Papst Franziskus | Großajatollah Ali al-Sistani
ምስል Ayatollah Sistani's Media Office/AFP

የሠላም ጥሪ፣ ፀሎትና ዱዓ


የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ከሮም ድረስ የተከተሉት የቫቲካን ባለስልጣናት፣ የኢራቅ አቻዎቻቸዉ፣ አስተናጋጅ አጃቢዎቻቸዉም የሉም።የርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳቱን ጉብኝት ደቂቃ በደቂቃ ከሚዘግቡት በመቶ ከሚቆጠሩ የመገናኛ ዘዴ ባለሙያዎች መሐል የነበሩት 5 አይሙሉም።አንድ አስተርጓሚ፣ጥቂት ረዳቶቻቸዉ እና ሁለቱ ብቻ።እንግዳዉ ከትንሺቱ አረጌ ግን ንፁሕ ቤት ደጃፍ ሲደርሱ ጫማቸዉን አወለቁ።ለወትሮዉ ከመቀመጫቸዉ የማይነሱት የ90 ዓመቱ አዛዉንት እንግዳቸዉን ቆመዉ ተቀበሏቸዉ።በሁለት እጆቻቸዉ ተጨባበጡ።ለ45 ደቂቃ ተነጋገሩም።ካቶሊክ እንደ ክርስቲያን  ሺዓ እንደ ሙስሊም ሐራጥቃዎች ዓለም ካወቃቸዉ ወዲሕ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስና ታላቁ አያቶላሕ አል ሲስታኒ ቅዳሜ ያደረጉት ዉይይት የመጀመሪያዉ ነዉ።ታሪካዊ። ጉብኝት ወይይቱ ለኢራቅ በዉጤቱም ለዓለም ሠላም ይፈይድ ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።
ዮሴፍ ማቲ ክርስቲያን ናቸዉ።ኢራቃዊ።በሚሊዮን እንደሚቆጠሩ ኢራቃዉያን ሁሉ በገዛ ሐገራቸዉ በገዛ ቀያቸዉ መኖር ሞት-ስቃይ-ሰቆቃ ሆኖባቸዉ መጠለያ ጣቢያ ሠፍረዋል።ባግዳድ።ዩናይትድ ስቴትስ መራሹ ጦር ኢራቅን ከወረረ ከ2003 ወዲሕ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ)  ከጦርነት-ሽብር፣ ከእልቂት-ስደት ሌላ ሌላ የማታዉቀዉን ሐገር፣የሮማ ካቶሊካዊት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ፣ መጎብኘታቸዉ አስደስቷቸዋል።«ግን» አሉ ዮሴፍ በጉብኝቱ ዋዜማ---ቀጠሉም።
«ጥሩ እንዲሆን እንመኛለን።ግን የባግዳድን ንፁሕ አዉራ ጎዳኖች ወይም ለጉብኝቱ ሲባል ያሸበረቁ አካባቢዎችን ብቻ መጎብኘት የለባቸዉም።እዚሕ መጥተዉ እዉነታዉን በተጨባጭ እንዲያዩት እንፈልጋለን።ክርስቲያኖች የሚኖሩበትን ሁኔታ፣ ያለንበትን ሁኔታ ይመልከቱ።የሠላም ሰዉ ነዎት፣ ኑሯችንን እዚሕ መጥተዉ ይኑሩ።»
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ኢራቃዊዉ ተፈናቃይ የተመኙትን አላደረጉም።ማድረግም አይችሉም።ኢራቅን ሲለዩ ግን ለኢራቆች ቃል ገቡ።«አልረሳችሁም።»
*«ወደ ሮም የምመለስበት ጊዜ ተቃርቧል።ይሁንና ኢራቅ ምንግዜም ከኔጋር ትኖራለች።ከልቤ አትጠፋም።»
የሁዲዉ አቭራም፣ ክርስቲያኑ አብረሐም፣ ሙስሊሙ ኢብራሒም ይሉታል።ሁሉም ግን እኩል ያምኑበታል።ትዉልዱም እዚያች ምድር ነዉ።ዑር-ኢራቅ።ርብቃ የተሞሸረችበት፣ ሐዋሪያዉ ቶማስ የሰበከባት፣ አቡ ሐኒፋ የተወለዱ ያስተማሩባት፣ አሊ የሚከበሩባት ያቺ ሐገር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በቀደም እንዳሉት በርግጥ «ዕምነቶች የተወለዱባት ምድር ናት።» ሥልጣኔም።
የኒያንደርታል፣ የካዉካሶይድ ኒሎቲክ፣ የኡሩክ ባሕል የዳበረባት።የሱሜሪያ፣ የሞሶፖታሚዎች ሥልጣኔ ያበባት፣ ሰዉ ሐሳቡን በፊደል መቅረፅ የጀመረባት ጥንታዊዉቱ ሐገር፤ ከአሰልጣኞችዋ- እኩል አሰይጣኞችዋ፣እንደ አዳኞችዋ ሁሉ አጥፊዎች፣ እንደ አልሚዎችዋ ሁሉ አፍራሾች ተለይተዋት አያዉቁም።
የሁዲ፣ክርስትና እስላም ሲፈራረቅባት፣ ግሪኮች፣ሮሞች፣ መንጎሎች፣ ኩርዶች፣ ፋርሶች፣ አረቦች፣ ቱርኮች፣ አዉሮጶች ሲሻሙ፣ሲጠፋፉ ሲጋደሉባት ዘመነ-አመናት አስቆጥራለች።ጥንታዊ ናት-ሐብታም።የቅይጦች ምድርናት ለም። ዓለም ሰላም-ፍትሕ፣ እኩልነት በሚሰበክበት በዚሕ ዘመንም ዕልቂት-ፍጅት፣ ጥፋት ዉድመቷ እንጂ ልማት፣ፍትሕ፣ሰላሟ አለመታወቁ ነዉ ቀቢፀ ተስፋዉ።
የዘመኑ ዴሞክራሲያዊት፣ ልዕለ ኃያል ሐገር ዩናይትድ ስቴትስ ከወረረቻት ከ2003 ወዲሕ የኢራቅ መዋዕለ ዜናም ታሪኳም በጦርነት፣ ሽብር፣ ግጭት የተሞላ ነዉ።ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ባለፉት 17 ዓመታት ስም-መልኩን እየለዋወጠ በቀጠለዉ ጦርነትና ሽብር ከ280 ሺሕ በላይ ሕዝብ አልቋል።ሚሊዮኖች ተሰደዋል ወይም ተፈናቅለዉባታል።ከዓለም የነዳጅ ሐብት ሶስተኛዉ ክምችት የሚዛቅባት ሐገር ከድሆች ድሐ ጠገግ ተንከባላለች።ከአንድነቷ ይበልጥ ክፍፍሏም ጎልቷል። 

Irak Besuch des Papst Franziskus
ምስል Andrew Medichini/AP Photo/picture alliance

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ኢራቃዊዉ ተፈናቃይ እንደተመኘዉ የተራዉን ኢራቃዊ ኑሮ-ኖረዉ ለማየት በርግጥ አይችሉም።እንደ መንፈሳዊ መሪ ግን መከሩ-ፀለዩም።
«የጠመጃ ግጭት ልሳኑ ይዘጋ።በየአካባቢዉ መስፋፋቱ ይገደብ።እዚሕም የትም ቦታ።የየተፋላሚ ወገኖች ጥቅም፣ የሐገሬዉን ሕዝብ ፍላጎት ያላካተተዉ የዉጪ ኃይላት ጥቅም ይወገድ።የሐገር ገንቢዎችና የሠላም ኃይላት ድምፅ ሰሚ ጆሮ ያግኝ።በሠላም መኖር፣ መስራትና ለፈጣሪዉ መገዛት የሚመኘዉ የተራዉ፣ የድሐዉ፣ ወንድና ሴት ድምፅ ሰሚ ያግኝ።»
ሰሚ ያገኝ ይሆን? አናዉቅም።የምናዉቀዉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለተመኙ፣ለፀለዩ፣ ከኢራቅ ለኢራቆችና በኢራቆች በኩል ለድፍን ዓለም ላስተላለፉት መልዕክት ገቢራዊነት የሺዐዎቹን መንፈሳዊ መሪ የታላቁ አያቱላሕ አል ሲስታኒን ድጋፍ ማግኘቱ ነዉ።
የነጃፉ የሺዓ አስተምሕሮ የበላይ መሪ አል ሲስታኒ እንደ ቁም-ኢራን ሺዓ መንፈሳዊ መሪዎች ኃይማኖትን ከፖለቲካ አይቀይጥሙ።ብዙ አይናገሩምም።ከተናገሩ ግን ቃላቸዉ የባግዳድ፣ ባስራ፣ሞስል አዉራ ጎዳኖችን እንቅስቃሴ የመግዛት አቅሙ ከፍተኛ ነዉ።
ዩናይትድ ስቴትስ ኢራቅን በወረረች በ2ኛ ዓመቱ ለአሜሪካ ወራሪ ጦር ያደሩ የኢራቅ ፖለቲከኞች የጠሩትን ምርጫ ኢራቃዉያን አንቀበልም ብለዉ ነበር።አል ሲስታኒ ለሰላም ስትሉ ምረጡ አሉ።ኢራቅ ባይፍቅም መረጠ።በ2014 የኢራቅና የሌቬንት (ሶሪያ) እስላማዊ መንግስት (ISIL) የተባለዉ አክራሪ ቡድን ገሚስ ኢራቅን መቆጣጠሩ ያሰጋቸዉ አል-ሲስታኒ አቅም ያለዉ ኢራቃዊ ቡድኑን እንዲዋጋ ፈትዋ ሰጡ።
ኢራቃዊ ወጣት እየተግተለተለ የኢራቅ መንግስት የሚያደራጀዉ ሚሊሺያ አባል ሆነ።እኒያ ጥቁር ጥምጣም፣ ጥቁር ጀላቢያ የሚያዘወትሩት የዘጠና ዓመት አዛዉንት የሚኖሩት ከብዙ ዓመታት በፊት በተከራይዋት አነስተኛ ቤት ነዉ።ባለፈዉ ቅዳሜ ትልቅ እንግዳቸዉን የተቀበሉትም እዚያችዉ ቤት ዉስጥ ነዉ።
ስለ ሁለቱ ዉይይት በፅሁፉ ከተሰጠዉ መግለጫ ሌላ እስካሁን በድምፅና ፊልም የቀረበ የለም።የሁለቱ መንፈሳዊ መሪዎች ቢሮዎች ከቫቲካንና ነጃፍ በየፊናቸዉ ባወጡት መግለጫ እንዳሉት ግን ዉይይቱ አግባቢና ገንቢ ነበር።የአል ሲስታኒ ቢሮ እንዳስታወቀዉ «ኢራቃዉያን ክርስቲያኖች እንደማንኛዉ ኢራቃዊ በሐገራቸዉ የመኖር መብታቸዉ እንዲከበር አልሲስታኒ አሳስበዋል።ኢራቅ ዉስጥ ባሁኑ ወቅት ከ25000 እስከ 300,000 የሚገመት ክርስቲያን ይኖራል።ከአሜሪካ ወረራ በፊት የክርስቲያኑ ቁጥር ከ1.2 ሚሊዮን ይበልጥ እንደነበር ይገመታል።
«ባለፉት ዓመታ በተወሰደዉ ጎጂና  ኢፍትሐዊ እርምጃ የተሰቃዩ በሙሉ ከለላ እንዲያገኙ» ይላል የአል ሲስታኒ ቢሮ መግለጫ« የኃይማኖት መሪዎች መጣር አለባቸዉ።»
የኢራቁ ፕሬዝደንት ባርሐም ሳሊሕም የሁለቱን መንፈሳዊ መሪዎች ጥሪና መልዕክት ተጋርተዋል።ይሁንና ፕሬዝደንቱ እንዳሉት የኢራቆች ችግር ከኢራቅ የመነጨ ብቻ አይደለም።
«ከዚሕ የጨለማ ሁከት አትራፊ አይኖርም።ከድርድር፣ ከጋራ ፀጥታ ከትብብርና የዜጎቻችንን መብት ከማስከበር በስተቀር መፍትሔ አይኖርም።የኢራቅን ጥልቅ ቁስል ለማዳን ኢራቅን የመግባቢያ፣ የሐሳብ መለዋወጪያ፣ የአካባቢዉ ሐገራት መገናኛ ድልድይ ማድረግ እንጂ  የዉዝግብና ግጭት ምድር ማድረግ አይደለም።»
ኢራቅ፣ ከ2003 ጀምሮ የሚያወድማት ወረራ፣ ዉስጣዊ ጠብና ቁርቁስ አልበቃ ያላት ይመስል የሶሪያ መንግስት፣ የተቃዋሚዎቹና የየደጋፊዎቻቸዉ ጦርነትና ግጭት ይጠብሳታል።የአይሁድና የአረቦች፣ የኩሮዶችና የቱርኮች ጠብ ይለመጥጣታል።ከሁሉም በላይ የኢራንና የዩናይትድ ስቴትስ፣ የኢራንና የሳዑዲ አረቢያዎች ግጭት፣ቁርቁስ የዜጎችዋን ሕይወት ሳይቀር ዕለት በዕለት ይቀጥፋል።ሐብት ንብረታቸዉን  ያወድማታልም።
ኢራቃዊዉ የፖለቲካ ተንታኝ አሕመድ ሩሺድ እንደሚሉት የርዕሰ-ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስና የታላቁ አያቶላሁ የአል ሲስታኒ መልዕክት በኢራቅ ዉሳኔ ሰጪ ኃይላት ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉ አይቅርም።
«ችግሮቹ በሙሉ፣ ሙስና፣ ሥራ አጥነት፣የአገልግሎት ማጣት፣ እነዚሕ ዋና ዋና ችግሮችን ለማስወገድ ባለፉት 17 ዓመታት ምንም የተደረገ ነገር የለም።የርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳቱ ጉብኝት ታሪካዊ ነዉ ግን፣ የዚያኑ ያክል በነዚያ በተጠቀሱት መስኮች ላይ ዉሳኔ የመስጠት ስልጣን ባላቸዉ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀሩም።»
የርዕሰ ሊቃነ-ጳጳሳቱ ጉብኝት፣ ዉይይትና መልዕክት ከኢራቆች አልፎ ኢራቅን የሚያወድም-የሚያጠፋዉን የዉጪ ኃይላትን ግጭትና ሽኩቻ ካላስቀረ ግን ዉጤቱ በርግጥ ግማሽ ነዉ የሚሆን።የፕሬዝደንት ባርሐም ሳሊሕ ስጋትም ይሆነዉ።
«ዓለማችን የክፍፍልና የፅንፈኝነት ዘመን ዉስጥ ትገኛለች።አብዛኛዉ የዓለም ክፍል በተለይ ምሥራቁ ልዩነትንና ብዙሐነትን ማስተናገድ እየተሳነዉ ነዉ።ይሕ መንገድ አሸባሪዎች እንዲጠናከሩ፣ ሁከትን እንዲጭሩ፣ የጥላቻ ንግግርን እንዲያሰራጩ፣በኃይማኖት ስም፣ በየትኛዉም  ዕምነት ተቀባይነት የሌለዉን መልዕክት እያስፋፉ ግፍና በደል እንዲያደርሱም ምክንያት ሆኗል።ይሕ መጪዉን ጊዜ አስጊ ያደርገዋል።ስለዚሕ የፅንፈኞችን አስተዳደብ ለማስወገድ፣ አሸባሪነትን አስወግደን ሐገራችን ያላት በጋራ አብሮ የመኖር ፅንሰ ሐሳብ  አሸናፊ እንዲሆን  የምናደርገዉ ጥረት መቀጠል አለበት።»
አዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳቱ ኢራቅን በመጎብኘታቸዉና ከኢራቅ የፖለቲካና የኃይማኖት መሪዎች ጋር በመወያየታቸዉ መደሰታቸዉን አስታዉቀዋል።ብሊከን ባለፈዉ ቅዳሜ በትዊተር ገፅ ባስተላለፉት መልዕክት ጉብኝቱ ኢራቅ ብቻ ሳይሆን በመላዉ ዓለም በሚገኙ የተለያዩ ኃይማኖት ተከታዮች ዘንድ መከባበርና መግባባትን ለማበረታት ጠቃሚ ነዉ።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ኢራቅን የጎበኙት የዩናይትድ ስቴትስ ጦር በኢራንና በኢራቅ መንግሥታት ይደገፋሉ የተባሉ የሁለት የኢራቅ ሚሊሺያ ቡድናት አባላትን ኢራቅ ድንበር ሶሪያ ዉስጥ በጦር ጄት በገደለ በሁለተኛዉ ሳምንት ነዉ።
ሁለቱ ሚሊሺያዎች ኢራቅና ሶሪያ የሸመቁ የISIL አሸባሪዎችን ይዋጋሉ የሚባሉ ናቸዉ።በጦር ጄቶቹ ድብደባ ከ20 የሚበልጡ ሚሊሺያዎች ተገድለዋል።በርካታ የጦር መሳሪያ ወድሟል።ሁለቱ ቡድናት የባልደረቦቻቸዉን ደም ለመበቀል ኢራቅ የሚገኝ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮችን መደብደባቸዉም ተሰምቷል።በርግጥ የኢራቅ ወይም የሌላዉ የዓለም ግጭት ዉዝግብ መሰረታዊ ምክንያት የአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር እንዳሉት የኃይማኖት ልዩነት ይሆን? ሌላ ጥያቄ።

Irak Besuch des Papst Franziskus in Ur
ምስል Vatican Media/REUTERS
Irak Mosul | Besuch Papst Franziskus
ምስል Andrew Medichini/AP/picture alliance

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ