1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የራይላ ኦዲንጋ አወዛጋቢ በዓለ ሲመት

ማክሰኞ፣ ጥር 22 2010

የኬንያን መንግስት የሚቃወመው «ብሄራዊ ላዕላይ ህብረት» በምህጻሩ (NASA) የተባለው ፓርቲ መሪ በዛሬው ዕለት አወዛጋቢ በዓለ ሲመት ፈጽመዋል፡፡ መሪው ራይላ ኦዴንጋ «የህዝብ መሪ» (people’s president) በሚል ማዕቀፍ የሀገሪቱ ፕሬዘዳንት አሁሩ ኬንያታ ከሦስት ወራት በፊት የፈጸሙትን ቃልኪዳን የሚመስል እሳቸውም ደግመዋል፡፡

https://p.dw.com/p/2rmEC
Kenia "Vereidigung" von Raila Odinga in Uhuru Park in Nairobi
ምስል picture-alliance/AP Photo/B. Curtis

የራይላ ኦዲንጋ አወዛጋቢ በዓለ ሲመት

አሁሩ ኬንታ የኬንያ ፕሬዜዳንትነት በዓለ ሲመታቸው በተፈጸመ በሦስተኛው ወር በዛሬው ዕለት ሀገሪቱ  አወዛጋቢ ፖለቲካዊ ትዕይንት አስተናግዳለች፡፡ የእሳቸው ተቀናቃኝ የሆኑት የተቃዋሚ ፖለቲካ ቡድን መሪ ራይላ ኦዲንጋ ዛሬ «ኡሁሩ ፓርክ» በተሰኘው ቦታ «የኬንያ ህዝብ መሪነት» ቃለ-መሃላ ፈጽመዋል፡፡

«እኔ ራይላ አሞሎ ኦዲንጋ የፈጣሪን ፈቃድ በሙሉ በመመረዳት፣ እንደ ኬንያ ህዝብ ፕሬዘዳንትነቴ ዕምነት የሚጣልበትና እና ለሪፐብሊኩም እውነተኛ አገልጋይ ለመሆን በጽኑ ቃል እገባለሁ፡፡ ለዚህ  የኬንያ ህገ መንግስትንም ተገዢ እሆናለሁ፣ እጠብቃለሁ፣ እከላከላለሁ፣ ተገን እሆናለሁ›› ብለዋል በቃለ-መሃላቸው።  
ስነስርዓቱ የተፈጸመው ኦዲንጋ የሚመሩት «ብሄራዊ ላዕላዊ ህብረት» በምህጻሩ (NASA) ሀገሪቱ በጎርጎሮሳዊው ነሐሴ 2017 ያከናወነችው ምርጫ አሸናፊ ራይላ ኦዲንጋ መሆናቸውን የሚያሳይ አዲስ መረጃ ማግኘቱን ባሳወቀ ማግስት ነው፡፡ ናሳ አሸናፊ መሆኑን ያተተበትን ምርጫ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስነስርዓት ግድፈት አለበት በሚል ከሻረው በኃላ ድጋሚ ምርጫ በጥቅምት 2017 ተደርጓል፡፡ ከዚህ ምርጫ የተቃዋሚዎች መሪ ራይላ ኦዲንጋ ራሳቸውን በማግለላቸው ኬንያን ለ5 ዓመታት ያስተዳዳሩት አሁሩ ኬንያታ ከቀሪ ዕጩዎች ጋር በመወዳዳር ለተጨማሪ አምስት ዓመታት በስልጣን የሚቆዩበትን ድል ተቀዳጅተዋል፡፡

Kenia Nairobi Großdemonstration der Opposition
ምስል Reuters/B. Ratner

በናሳ አመራሮች ዘንድ ድጋሚ ምርጫው እጅግ ቁጥሩ ያነሰ መራጭ የተሳተፈበት፣ ነውና ተቀባይነት የለውም-ህዝቡ ትክክለኛ ድምጹን በአንባገነነት ርምጃ ተነፍጓል፡፡ህዝቡ የመረጠው ራይላ ኦዲንጋን ነውና ህዝብ ፍላጎት የህዝብ ፕሬዘዳንት ሆነው   ቃለ መሃላ ሊፈጽሙ ይገባል በሚል ሲሞገት ሰንብቷል፡፡

የዛሬውን ስነስርዓት ወደ ትክክለኛ ዲሞክራሲ የሚያደርስ ታሪካዊ ርምጃ ሲሉ ኦዲንጋ ገልጸውል፡፡ ‹‹ዛሬ ለኬንያዊያን ታሪካዊ ቀን ነው፡፡በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ በ100ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ የምርጫ ማጭበርበር ተግባር ሊያበቃ ይገባል ሊል ተሰብስቧል፡፡የዛሬው ርምጃ የምርጫ አምባገነናዊነትን የመግቻ እና ትክክለኛ ዲሞክራሲን የማስፈን አንድ ርምጃ ነው፡፡››

Kenia Vereidigung von Raila Odinga in Uhuru Park in Nairobi
ምስል DW/S. Wassilwa

የኬንያ መንግስት ግን የዛሬውን አወዛጋቢ ህዝባዊ በዓለ ሲመት ከጥንስሱ ጀምሮ ተቃውሞታል፡፡በህጋዊ መንገድ የተመረጠ መሪ ባለበት ሁኔታ ሌላ የመሪነት ቃለ መሃላ መፈጸም መፈንቅለ መንግስት ነው፣ህገመንግስታዊ ስርዓትን መጣስ ነው ሲል በተወካዮቹ በኩል ኮንኖታል፡፡

የሀገሪቱ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ጊቱ ሙጋይ ደግሞ ድርጊቱ የሞት ቅጣት የሚያስከትል ከባድ ወንጀል መሆኑን ቀደም ባሉት ሳምንታት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከፍተኛ የሀገር ክህደት ነው፡፡ በፈጸመው ሰውም ሆነ ስነስርዓቱን ባመቻቸው ሰው ዘንድ ይሄ የሀገር ክህደት ነው፡፡ለከፍተኛ የሀገር ክህደት ቅጣቱ ምንድነው ? ሞት ነው! ››

ሀብታሙ ስዩም 

ኂሩት መለሰ