1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሪየክ ማቻርና ወታደራዊ ክንፉ ውዝግብ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 1 2013

ደቡብ ሱዳን ለበርካታ ዓመታት ደም ካፋሰሰው የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ በሕዝበ ውሳኔ 99 በመቶ ድጋፍ አግኝታ ከሱዳን ተነጥላ ራሷን የቻለች ሀገር መሆኗን ካወጀች እንደ ጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ዓመታት ያህል በብሔር ጥቃቶችና በእርስ በእርስ ጦርነቶች ስትታመስ ቆይታለች::

https://p.dw.com/p/3ygVo
Äthiopien Addis Abeba Riek Machar
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Ayene

የሐምሌ 30/2013 ዓ/ም የትኩረት በአፍሪካ ዝግጅት

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ደቡብ ሱዳን ወደ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር የምታደርገው ጉዞ እጅግ አዝጋሚና በቅራኔ የታጀበ መሆኑ ወደከፋ ግጭት ሊያመራ ይችላል ሲል በተደጋጋሚ ስጋቱን ሲገልጽ ቆይቷል:: የፈራው አልቀረም ባለፈው ረቡዕ ማቻር የሚመሩት ትልቁ የተቀናቃኝ ቡድን ወታደራዊ ክንፍ የፖለቲካው አመራር ሃላፊ የሆኑት ሪክ ማቻር የሕዝባቸውንም ሆነ የድርጅቱን መብት እያስጠበቁ አይደልም ሲል ከሶ ከሃላፊነት እንዳነሳቸው ይፋ አድርጓል:: እንደውም ማቻር በተቃራኒው የለውጡን ሂደት የተሳካ ከማድረግ ይልቅ ስልጣንን ከራሳቸው አልፈው የቤተሰቦቻቸውና የወዳጆቻቸው መጠቀሚያ አድርገውታል የሚል ውንጀላም ቀርቦባቸዋል:: ድርጅቱ በሳቸው ምትክ በቡድኑ ወታደራዊ ክንፍ ተጽዕኖ ፈጣሪና ከፍተኛ ተደማጭነት አላቸው የሚባሉትን የጦር አዛዥ ሌተናል ጄነራል ሲሞን ጋትዌክ ዱዋልን የተቀናቃኙ ቡድን ዋና መሪ አድርጎ መሾሙንም ነው ያስታወቀው:: ይህ ሹም ሽረት ፕሬዝዳንት ሳል ቫኪር እና የተቀናቃኝ ቡድኑ መሪ ማቻር ከብዙ ጥረት በኋላ እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በመስከረም ወር 2018 ዓ.ም በጎረቤት ሀገር ሱዳን የአንድነት መንግሥት ለመመስረትና ሥልጣን ለመጋራት የተፈራረሙትን የሰላም ውል ከባድ አደጋና አጣብቂኝ ውስጥ የከተተ መሆኑ ከወዲሁ እየተነገረ ነው::

Südsudan Salva Kiir und Riek Machar | Entscheidigung für  Einheitsregierung
ምስል AFP/A. McBride

ደቡብ ሱዳን ለበርካታ ዓመታት ደም ካፋሰሰው የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ በሕዝበ ውሳኔ 99 በመቶ ድጋፍ አግኝታ ከሱዳን ተነጥላ ራሷን የቻለች ሀገር መሆኗን ካወጀች እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር ከ 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ዓመታት ያህል በብሔር ጥቃቶችና በእርስ በእርስ ጦርነቶች ስትታመስ ቆይታለች:: የዚህም ምክንያቱ ዲንካና ኑዌር ከሚባሉት ሁለቱ የደቡብ ሱዳን ትላልቅ ጎሳዎች የተገኙት ሁለቱ ተቀናቃኝ ኃይላት ሳል ቫኪርና ማቻር በመካከላቸው ለዓመታት ሰፍኖ የቆየው አለመተማመንና የአንዱ ጎሳ ሌላውን በማጥቃት ወንጀል መካሰሳቸው ነው:: እንዲህ በጎሳዎች ግጭት፣ በቅራኔና አለመግባባት ላይ የተመሰረተው የአዲሲቱ ሀገር ደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩትን ዋንኛው የተቀናቃኝ ቡድን መሪና የሜካኒካል ምህንድስና ባለሙያው ዶክተር ማቻር እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር ታህሳስ 2013 ዓ.ም መፈንቅለ መንግስት ለማካሄድ አሲረዋል በሚል ከስልጣናቸው ካባረሯቸው በኋላ ወትሮም ቋፍ ላይ የነበረችው ሀገሪቱ ወደለየለት የእርስ በእርስ ጦርነትና ግጭት ልትገባ ችላለች። ለስድስት ዓመታት የዘለቀውን፣ ከ 400 ሺህ በላይ የንጹሃን ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈውንና ከ12 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ያፈናቀለውን እንዲሁም ለከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት መንስኤ የሆነውን አስከፊውን ጦርነት ለማብቃት ከአስር በላይ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ቢደረጉም አንዳቸውም ውጤት ሳያስገኙ ቀርተዋል:: ምንም እንኳ ደቡብ ሱዳን ለእርሻ ተስማሚ በሆነ መሬት፣ በወርቅ፣ በእንቁ፣ በከፍተኛ የነዳጅና የተፈጥሮ ሃብት የታደለችና የበለፀገች ብትሆንም ዛሬም የሀገሪቱ አብዛኛው ሕዝብ የስብዓዊ እርዳታ ጠባቂና ተመጽዋች ሆኗል:: በጦርነትና ግጭቱ ምክንያት መሰረታዊ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣የምጣኔ ኃብት ድቀት፣የጤናና የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት እጥረት እንዲሁም የመሰረተ ልማት ግንባታ አለመስፋፋት የዜጎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት እጅግ የከፋና የተጎሳቆለ እንዲሆን አድርጎታል:: የሰላማዊ ዜጎች እገታ፣ የፆታ ጥቃትና አስገድዶ መድፈር፣ ልዩ ልዩ የመብት ጥሰትና ሕጻናትን ለጦርነት በግዳጅ የማሰለፍ ወንጀሎችም ተበራክተዋል::  የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ደም አፋሳሹን ግጭት ለማስቆም የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ሲጥል ዩናይትድስቴትስም በተመረጡ የሀገሪቱ ባለስልጣናት ላይ የጉዞና የንብረት ማንቀሳቀስ እገዳን አሳልፋ ነበር::የአፍሪቃ ህብረትና የኢጋድ አባል ሀገራትም ሰላም አስከባሪ ጦር በመላክም ሆነ ችግሩን በሰላም ለመፍታት አያሌ ጥረቶችን አድርገዋል:: በተለይም ዓለማቀፍ የረድኤት ድርጅቶች "ሁለቱም ኃይላት ሰብአዊ ዕርዳትን ለጦርነት ይጠቀማሉ፣ እርዳታም በተገቢው ሁኔታ ሌለተጎጂዎች እንዳይዳረስ እንቅፋት ሆነዋል" የሚል ጠንከር ያለ ወንጀላና ክስ ማሰማት ከጀመሩ በኋላ በመስከረም ወር 2018 ዓ.ም ተቀናቃኝ ኃይላቱ ስልጣን መጋራትና የሽግግር መንግሥት መመስረት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል:: በወቅቱ ፕሬዝዳንት ሳል ቫኪር የሽግግር ሂደቱ እንደማይደናቀፍ ቃል ገብተው ነበር::

Südsudan Schutzzone Malakal
ምስል Getty Images/AFP/A.-G. Farran
Sudan nach dem Bürgerkrieg Polizist
ምስል AP
Südsudan Verhandlungen zwischen Regierung und Opposition
ምስል Reuters/J. Solomun

 

"ብዙዎች ማየት ይመኙት የነበረው የሰላም ስምምነት ተግባራዊ ሆኗል:: በእኔ በኩል ዳግም ወደ ግጭትና ጦርነት እንደማልመልሳችሁ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ:: የባከኑትን አስርተ ዓመታት ለማካካስ ምጣኔ ኃብታችን እንዲያገግምና ልማታችን እንዲፋጠን በጋራ ከማቻር ጋር ጠንክረን እንሰራለን"

በደቡብ ሱዳን በተለይም የ 2016 ዓ:ም የሰላም ስምምነቱን መፍረስ ተከትሎ ፕሬዝዳንት ሳል ቫኪር ከተቀናቃኛቸው ማቻር ደጋፊዎች ጋር ከባድ ፍልሚያ አካሂደዋል። የሰላም ስምምነቱ ተፈርሞ ወደ ሃገር ከተመለሱ በኋላ ግን እሳቸው የምክትል ፕሬዝዳንትነቱን ስልጣን ባለቤታቸው አንጀሊና ቴኒ ደግሞ የሀገሪቱን የመከላከያ ሚኒስትርነትን ቦታ ተቆናጠዋል:: ከስምምነቱ አስቀድሞ በደህንነት ስጋት ጁባን ለቀው የተሰደዱት ማቻር የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ለሶስተኛ ጊዜ ወደ ስልጣን መመለሳቸውን በማስታወስ የቀደመ ልዩነታችሁን አስወግዳችሁ ከሳል ቫኪር ጋር አብራችሁ መስራት የምትችሉ ይመስላችኋል? ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ በሳቸው በኩል ስምምነቱ የሕዝቡን ፍላጎት ያማከለ በመሆኑ ዘላቂነት እንደሚኖረው እምነታቸውን ገልፀዋል::

 

"ከደቡብ ሱዳን ውጪ አዋሳኝ ድንበር ከሆነው የኢትዮጵያ የጋምቤላ አካባቢ የሰላም ድርድሩን ተከትሎ መመለሴ ነው:: ሰላም የሁሉም ነገር ዋናው መሰረት እንደሆነ ይታወቃል:: ምክንያቱም ለሀገርም ለሕዝብም የሚጠቅም ሰላማዊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚም ሆነ ማሕበራዊ እንቅስቃሴዎችን በስኬት ማከናወን የሚቻለው በአንድ ሀገር ውስጥ ሰላም የሰፈነ እንደሆነ ብቻ ነው:: በእኔ እምነት በስምምነቱ የተገባው ቃል ይከበራል የሚል ተስፋ አለኝ:: "

በደቡብ ሱዳን ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ማቻር ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንትነትን ስልጣን መልሰው ቢቆጣጠሩም ለሦስት ዓመት ያህል ይቆያል የተባለው የሽግግር መንግሥት በብዙ ሳንካዎች ውስጥ አልፏል:: የስልጣን ክፍፍል ፍትሃዊነት ጉዳይ፣ የጎሳዎች ግጭት አለመቆም፣ ሁለቱም ወገኖች የሚፈልጉትን ሰው እየመረጡ በአመራር ቦታ መመደብ እንዲሁም የአማጽያኑ ተዋጊዎች ከመደበኛው የሀገሪቱ የጦር ኃይል ጋር የሚዋሃድበት ጉዳይ ለረጅም ጊዜ ሳይፈታ መቆየቱ የሽግግር ሂደቱ ላይ የተደቀኑ ፈተናዎች ነበሩ:: ከዚህ ሌላ ቀያቸውን ጥለው የተሰደዱ ሰዎች ወደመኖሪያ ቀያቸው ይመለሳሉ ቢባልም እንደ ጁባ፣ ሎኡ ኑዌር ፣ ዲንካ ቦር፣ ሌቦንኮ፣ ሙንድሪ፣ ማሪዲና ሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ወንጀሎች መስፋፋትና ልዩ ልዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መቀጠሉ በሀገሪቱ ሥርዓት አልበኝነት እንዲነግሥ ግጭት፣ ሞት ፣ ስደትና የሕዝቦች መፈናቀልንም እንዲባባስ አድርጓል:: በሀገሪቱ ዕድሜያቸው ለትምህርት ከደረሱ ሕጻናት ከሶስት አራተኛው በላይ በግጭቶች ምክንያት ከትምህርት ገበታ እንዲርቁ ተገደዋል::

ደቡብ ሱዳን በእነዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ውስጥ ባለችበት ወቅት ነው እንግዲህ ሪክ ማቻር የሚመሩት ተቀናቃኙ ድርጅት ወታደራዊው ክንፍና ፖለቲካዊ አመራሩ ቅራኔ ውስጥ ገብተው ባለፈው ረቡዕ በስልጣን ባልገዋል፣ በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ የአመራር ብቃታቸውና ክህሎታቸው ተፈትኖ

ከሽፏል፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አመራርን የማይከተሉም ናቸው ያላቸውን ማቻር ወታደራዊ ክንፉ ከስልጣን ማባረሩን በመግለጫው ያስታወቀው:: አሁን በአብዛኛው የድርጅቱ አባላት የሽግግሩን ሂደት ያሳካሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው አዲሱ ተመራጭ የወታደራዊው ክንፍ መሪ ሌተናል ጄነራል ዱዋል በ 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ከተካሄደው የመጀመሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ ዋና መዲና ጁባ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ለሰላም ስምምነቱ ስኬት የበኩላቸውን ሚና እንደሚያበረክቱ ለጋዜጠኞች ገልፀው ነበር::

"በጁባ ለተደረገልን ደማቅ አቀባበል እናመሰግናለን:: ከሳል ቫኪየር ጋር በአዲስ አበባ የሰላም ውይይት አድርገናል:: እንደሚታወቀው ሀገሪቱ ለዓመታት በእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ ቆይታለች:: ሆኖም ልዩነታችንን አጥብበን ያለንን የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ኃይል ተጠቅመን የሕዝባችንን ኑሮ ለመለወጥ ብሎም የሰላምና የሽግግር ሂደቱ እንዲሳካ አስፈላጊውን ጥረት እናደርጋለን::"

UN Soldaten im Südsudan
ምስል picture alliance/Yonhap

በደቡብ ሱዳን የላይኛው ናይል ግዛት በኪትግዋንግል ለ 3 ቀናት በተካሄደው የድርጅቱ ወታደራዊ ክንፍ ግምገማ "ዶክተር ማቻር ከወታደራዊ እዙ ዕውቅና ውጪ ፖለቲካዊ አመራሩን ብቻ ለይተው ወደ ጁባ መጥራታቸውና ስልጣንን መከፋፈላቸው ላለፉት 8 ዓመታት በዋና አመራርነት ለመቆየት ሲከተሉት የቆየው የከፋፍለህ ግዛ ሥልት አንዱ ማሳያ ነው ብሎታል:: ንፁሃንን ዜጎች በሥርዓቱ ላይ እንዲያምፁ ሁከት መፍጠርና ማሳደምም ሌላው የማቻራ እኩይ ባህሪ መገለጫ ነው ሲልም ክፉኛ ነቅፏቸዋል:: ወታደራዊ ኃይሉ ሁሉም የሀገሪቱ ብሔሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የወጣቶችና የሴቶች አደረጃጀቶች እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት የሀገሪቱን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት በሕብረት እንዲነሱም ጥሪ አስተላልፏል:: በ 2018 ዓ.ም የተፈረመውን የሰላም ስምምነት አንቀጾችም በመጥቀስ የውሳኔውን ግልባጭ ለኢጋድ መላኩን ይፋ ድርጓል:: የምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር ቢሮ ግን የቀረበውን ክስና ውንጀላ በሙሉ ውድቅ ያደረገው ሲሆን ሌተናል ጄነራል ዱዋል ከድርጅቱ የጦር አዛዥ ኃላፊነት መነሳታቸውንም አስታውቋል:: ባለፈው ሰኔ ወር ፕሬዝዳንት ሳል ቫኪር ጄነራሉን የሰላም ሚኒስቴር አማካሪ አድርገው መሾማቸውን ቢያስታውቁም አፍታም ሳይቆይ ሹመቱ ውድቅ ሆኗል::

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሪክ ማቻር ከሚመሩት ድርጅት አባላት የአብዛኛውን ድጋፍ ማጣታቸው ይነገራል:: የተቀናቃኝ ድርጅት አባላቱ አመራሩን ከውድቀት ያድኑታል ብሎ ተስፋ የጣለባቸው ሌተናል ጄነራል ዱዋል እዛው ደቡብ ሱዳን በኡሮር ጆንገሊ ግዛት የተወለዱ ሲሆን ለደቡብ ሱዳን ነጻነት ፋና ወጊ ሆነው የታገሉት ዶክተር ጆን ጋራንግ ይመሩት የነበረው የቀድሞው "የደቡብ ሱዳን ሕዝብ የነጻነት ንቅናቄ /ኤስ.ፒ.ኤል.ኤ/ " ሸማቂ ቡድን አባል እንደነበሩም ይነገራል:: እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ 1991 ዓ.ም በሃሳብ አመለካከት ልዩነት ምክንያት ሪክ ማቻር እና ላም አኮል "ኤስ.ፒ.ኤል.ኤ-ናስር" የተባለውን አንጃ ፈጥረው ከድርጅቱ ከተገለሉ በኋላ ይህንኑ አንጃ መቀላቀላቸው ሲነገር በ 1991 ዓ.ም በዛው በደቡብ ሱዳን የተፈፀመውን "የቦር የዘር ማጥፋት ጥቃት" በመባል የሚታወቀውን በመምራትም ይወነጀላሉ:: እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ 2013 ዓ.ም ፕሬዝዳንት ሳል ቫኪር ማቻርን በመፈንቅለ-መንግሥት ሴራ ወንጅለው ከስልጣን ማባረራቸውን ተከትሎ ከተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ግጭት በኋላም የድርጅቱ ወታደራዊ ክንፍ አዛዥ በመሆን ተሹመዋል:: አሁን በማቻር ፓርቲ ውስጥ የተከሰተው ክፍፍልና ሹም ሽር የደቡብ ሱዳንን ፖለቲካዊ ቀውስ በእጅጉ ያባብሰዋል፣ ወደለየለት ጦርነትም ልታመራ ትችላለች ተብሎ ተስግቷል::

 

የብሪታንያ በኬንያ የመሬት መቀራመት ወንጀል በተባበሩት መንግሥታት ዕይታ

 

በቅኝ ግዛት ዘመን የብሪታንያ ጦር አባላት በኬንያ ነባሩን የሀገሬው ተወላጅ ከርስቱ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በማፈናቀል ለፈፀሙት ከፍተኛ የመሬት ወረራ ወንጀል እስከዛሬ ተገቢውን ካሳ አለመክፈላቸው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አሁን ላይ ትኩረት ያገኘ ጉዳይ ሆኗል:: ስድስት የተለያዩ የመንግሥታቱ ድርጅት የክስ መዛግብቶች እንዳመለከቱት በኬንያ ኬሪቾ ግዛት ኪፕሲጊስና ቱላይ በሚባሉ የጎሳ ማህበረሰብ አባላት ላይ የብሪታንያ መንግሥት እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር ከ 1895 እስከ 1963 ባሉት ዓመታት የአካባቢውን መሬት ለምነትና ለእርሻ ተስማሚነት በመገንዘብ ነባሩን የሀገሪቱ ነዋሪ በግፍ አፈናቅለውና አባረው ከ 68 ዓመታት በላይ የሻይ ቅጠልና የትምባሆ ተክል ልማት እርሻን ሲያከናውኑ ቆይተዋል::

Großbritanien I The Duke of Edinburgh |  Prinz Philip
ምስል William Lovelace/Daily Express/Hulton Archive/Getty Images

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመቶ ሺህዎች በሚቆጠሩ ኬንያውያን ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመፈፀና የመኖር ህልውናቸውን አደጋ ላይ በመጣል የብሪታንያ ጦር አባላትና ዜጎች ለፈፀሙት ወንጀል ካሳ እንዲከፍሉ በፍርድ ቤት ውሳኔ ቢተላለፍም እስካሁን ተፈጻሚ ባለመሆኑ ወቅሷል:: የጥቃቱ ተጎጂ የሆኑ የማሕበረሰቡ አባላት በህግ ጠበቆቻቸው አማካኝነት በብሪታንያ መንግሥት ላይ እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ 2019 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የክስ ፋይል መክፈታቸው ታውቋል:: የክሱ መዝገብ እንደሚያመለክተው በፈረንጆቹ 1902 ዓ.ም ብቻ በኬንያ ከኪፕሲጊስና ታላይ ጎሳዎች ወራሪው የብሪታንያ ጦር አባላት ከ 36 ሺህ ሄክታር በላይ ለም መሬት አካላዊ ጥቃት ጭምር በመፈፀም ነዋሪውን አፈናቅለው ለብሪታንያ ዜጎች እንዲከፋፈል አድርገዋል:: ይህ መሬት ደግሞ አሁንም በብሪታንያና የአውሮጳ የሻይ ቅጠል እርሻ አምራች ባለሃብቶች ቁጥጥር ስር ነው የሚገኘው:: የእንግሊዝ መንግሥት ጉዳዩ ለሕዝብ ይፋ ከመሆኑ በፊት ለቀረበበት የመሬት ወረራና የመብት ጥሰት የወንጀል ክስ በ 60 ቀናት ውስጥ ምላሹን እንዲሰጥ ቢጠየቅም እስካሁን በሚመለከተው የመንግሥት አካል በኩል ምንም ዓይነት ቀጥተኛ ማብራሪያ አለመስጠቱንም ነው ዘገባዎች ያመለከቱት::

የጉዳቱ ሰለባዎች ተወካዮች ሮድኔ ዲክሰንና ጆይል ቦሴክ እንዲሁም የኪሪቾ ግዛት ከንቲባ ፓውል ቼኮኒ "ወገኖቻችንና ቤተሰቦቻቸው ለአስርተ ዓመታት አስከፊ የሰቆቃ ሕይወትን ገፍተዋል::ዕውነተኛና ያልዘገየ ፍትህ ተጠያቂነትን የሚወስድና ይቅርታን የሚጠይቅ አካልን ይሻሉ:: የገዛ መሬታቸውን በግፍ መነጠቃቸው ብቻ ሳይሆን ለተፈፀመባቸው አካላዊና የስነ-ልቦና ጥቃትም ጭምር ተገቢውን ካሳ ማግኘት ይኖርባቸዋል:: አሁን ጉዳዩ የዓለማቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት ማግኘቱ አስደስቶናል" ብለዋል::

የብሪታንያ የውጭ ግንኙነት የጋራ ብልጽግናና የልማት ቢሮ ቃል አቀባይ "በቅኝ ግዛት ዘመን አንዳንድ ኬንያውያን በብሪታንያ ወታደሮች አካላዊ ጥቃትና ሰቆቃ እንደተፈፀመባቸው እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ 2013 ዓ.ም በተካሄደ ምርመራ ተረጋግጧል" ሲል የቀድሞ የሀገሪቱ ተቀዳሚ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዊልያም ሄግ በእማኝነት ጠቅሶ ገልጿል:: በመሆኑም በመስከረም 2015 ዓ.ም የብሪታንያ መንግሥት በኬንያ ኡኹሩ የነጻነት ፓርክ የሰቆቃውን ሰለባዎች የሚዘክር ማስታወሻ ሀውልት ማቆሙንም ቢሮው ጨምሮ አስታውቋል::

 

እንዳልካቸው ፈቃደ