1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሩስያ የአፍሪቃ የመረጃ ዘመቻ ሚናው ምን ይመስላል?

ቅዳሜ፣ ኅዳር 24 2015

በርካታ ኢትዮጵያውያን በእንግሊዝኛ ቋንቋ «ሩስያ ቱዴይ» የተባለውን የቴሌቪዥን መርኃ ግብር እንደሚከታተሉም ቤቴልሔም ገልጣለች። ከቤተሰቦቿ ጋር የምታደርገው ንግግርም ብዙውን ጊዜ የሚቋጨው በጭቅጭቅ ነው።

https://p.dw.com/p/4KPXo
Russische Desinformation im Nahen Osten | RT Arabisch Studio in Moskau
ምስል Misha Friedman/Getty Images

በእርግጥ RT የቴሌቪዥን ጣቢያን የሚከታተለው ማን ነው?

ቤቴልሔም እንዳለ የጥርስ ሐኪም ናት። ሩስያ ዩክሬን ውስጥ ጥቃት መሰንዘር ስትጀምር ከሁለት እህቶቿ ጋር ከቻርኪቭ ወደ ጀርመን ሽቱትጋርት ሸሽታለች። ወላጆቿ ደግሞ ከዩክሬን ወጥተው በቀጥታ ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ነው ያቀኑት። ቤቴልሔም ከዶይቸ ቬለዋ ማርቲና ሽቪኮቭስኪ ጋር ባደረገችው ቃለ መጠይቅ ቤተሰቦቿ ለሩስያ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎች መጋለጣቸውን ትናገራለች።

«እንደ እኔ አመለካከት የሩስያ ፕሮፓጋንዳ አፍሪቃ ውስጥ ስር የሰደደ ነው። ከኢትዮጵያ ዜና እመለከታለሁ። ሰዉ በርካታ የተዛቡ መረጃዎችን እንደሚመለከትም መገንዘብ ችያለሁ። በእውነቱ በጣም ይረብሻል።» 

ፕሮፓጋንዳ እና የአእምሮ መታጠብ

በርካታ ኢትዮጵያውያን በእንግሊዝኛ ቋንቋ «ሩስያ ቱዴይ» የተባለውን የቴሌቪዥን መርኃ ግብር እንደሚከታተሉም ቤቴልሔም ገልጣለች። ከቤተሰቦቿ ጋር የምታደርገው ንግግርም ብዙውን ጊዜ የሚቋጨው በጭቅጭቅ ነው። የቤቴልሔም ቤተሰቦች እንደ በርካታ አፍሪቃውያን በሶቪየት ኅብረት ዘመን በተማሪዎች ልውውጥ መርኃግብር ዩክሬን የመጡ ናቸው። ዩክሬን በሶቪየት ኅብረት ዘመን የሪፐብሊኩ አንድ አካል ነበረች። ቤተሰቦቼ «የተማሩ ቢሆኑም» ትላለች ቤቴልሔም፦ በሩስያ ባሕል ማእከል በኩል ስለ ሩስያ ጦርነት «የሐሰት መረጃዎችን» ነው የሚያገኙት ስትልም ትናግራለች።

«ቤተሰቦቼ ዩክሬን እንደ ሀገር የመቀጠል መብት ያላት መሆኑን ባለመረዳታቸው እንጨቃጨቃለን። ልክ 1991 ከበርካታ ሃገራት እንደመጡት እና እንደነበረው ነው የሚያስቡት። ግን እንደ በርካታ ሩስያውያን በፕሮፓጋንዳው ስለተጠዘጠዙ ላስረዳቸው በጣም እጥራለሁ።» 

RT-Logo auf einem Smartphone-Bildschirm
ሩስያ ቱዴይ የተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ዓርማ በተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ እንዲሁም ታንክ ይታያልምስል Muhammed Ibrahim Ali/IMAGESLIVE via ZUMA Press Wire/picture alliance

ቤሌልሔም ቤተሰቦቿን ስለ ሩስያ ጦርነት ለማስረዳት ብትጥርም በርካታ ኢትዮጵያውያን ግን «ሩስያ ቱዴይ» ቴሌቪዥንን እንደ አማራጭ የሚመለከቱት ከምእራባውያን ዘንድ ከአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚፈልቅ ፕሮፓጋንዳን ላለመጋት በሚል መሆኑን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣል። በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት በርካታ የምእራባውያን የመገናኛ አውታሮች እና ጋዜጠኞች እጅግ ዐይን ባወጣ መልኩ ኢትዮጵያ ላይ ያደርጉት የነበረው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ብርቱ እንደነበረም ብዙዎች በምሬት ይናገራሉ።

ክሪስቶፍ ፕሌት ደቡብ አፍሪቃ ጆሐንስበርግ ከተማ የሚገኘውን የጀርመኑ ኮንራድ አደንአወር ተቋም ከሰሐራ በታች ክፍል በኃላፊነት ይመራሉ። ሰዎች ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ለምን በሩስያ መንግሥት የሚደገፈውን የ«ሩስያ ቱዴይ» የቴሌቪዥን ሥርጭት እንደሚመለከቱ ያብራራሉ።

«በተለይ ሩስያ ዩክሬን ላይ ጦርነት ከከፈተችበት ጊዜ አንስቶ በመላ የአፍሪቃ አኅጉር በሩስያ ትረካዎች ተጠምደናል። የሩስያ ትረካ እዚህ ሩስያ ፈጽሞ የቅኝ ግዛት አልነበራትም ብሎም የኢምፔሪያሊዝም ጉጉት ኖሯት ዐያውቅም ወደሚለው አመለካከት ተቀይሯል። በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ መንጸባረቅ ጀምሯል። ግን ደግሞ የሰዉን ስሜት ለመረዳት እንደሚቻለው እዚህ ለምእራባውያን የበላይነት ግንባሩን ኮስተርተር ማድረጉን ነው።»

የዶይቸ ቬለዋ ማርቲና ሽቪኮቭስኪ የሩስያ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ የኤኮኖሚ ማእከል በሆነችው የደቡብ አፍሪቃዋ ጆሐንስበርግም መሰራጨት መጀመሩ የጊዜ ጉዳይ ነው ትላለች።  የሩስያው በምኅጻሩ RT የተሰኘው «ሩስያ ዛሬ» የቴሌቪዥን ጣቢያ ሥርጭት ሩስያ ዩክሬን ላይ በከፈተችው ጦርነት የተነሳ በሚል በምእራባውያን ዘንድ እንዳይታይ ታግዷል። ይህ ጣቢያ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚያሰተላልፈውን የቴሌቪዥን ሥርጭት ዋና ጽ/ቤት ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ለመክፈት ዓልሟል። ቀደም ሲል የኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ውስጥ ለማድረግ ንግግር ነበር። ጣቢያው ቅርንጫፎችን አፍሪቃ ውስጥ ለመክፈት ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑም ተዘግቧል።

ፕሮፓጋንዳ የግዙፉ ስልት አንዱ አካል ነው

የሩስያ የመገናኛ አውታር ዘመቻ ይላሉ ኔዘርላንድ የሚገኘው ክሊንጌንዳዬል ተቋም ባልደረባ ጉዊዶ ላንፍራንቺ ሩስያ አኅጉሪቱ ለማስፋፋት ለምትሻው የፕሮፓጋንዳ «ግዙፉ ስልት አንዱ አካል ነው።

Straßburg | Russland vom Europarat ausgeschlossen | russische Flagge eingeholt
ሽትራስቡርግ ውስጥ ከሚገኘው የአውሮጳ ምክር ቤት ቅጽር ግቢ የሩስያ ሠንደቅ-ዓላማ ከተሰቀለበት ሲወሰድምስል Jean-Francois Badias/AP/picture alliance

«የዚህ መገናኛ አውታር አፍሪቃ ውስጥ የመገኘት አድማሱ የአፍሪቃ ነዋሪዎችን ምልከታ በመቅረጽ ረገድ ተጽእኖው ምን ያህል እንደሆነ አሁንም ድረስ ግልጽ አይደለም። አንዳንድ ተከታታይ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አፍሪቃ ውስጥ ይህን የመገናኛ አውታር የሚመለከቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። ይህም ለሩስያ ያላቸው አመለካከት ቀና እንዲሆን አድርጎ ይቀርጻል። ይሁንና በተመሳሳይ ጊዜ ተጽእኖው በሚገባ ለማወቅ በተለይ የተከታታይ ጥናቶች እጥረት አስቸጋሪ ያደርገዋል።»

የሩስያ ተጽእኖ በፍጥነት እያደገ ነው

የሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር አዲስ አበባ በገቡበት ወቅት

Äthiopien | Russlands Außenminister Sergei Lawrow in Addis Ababa
የሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ሠርጌ ላቭሮቭ ከኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚንሥትርና ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ደመቀ መኮንን ጋር አዲስ አበባ ውስጥምስል Office of foreign minister

ቀደም ሲል የሶቪየት ኅብረት ውስጥ የትምህርት እድል ያገኙ በርካታ እንደ ደቡብ አፍሪቃ፣ አንጎላ እና መካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ ውስጥ በመሪነት ቦታዎች ላይ የሚገኙ ሰዎች ያኔ የአፍሪቃ የነጻነት ንቅናቄዎችን ትደግፍ ከነበረችው የያኔዋ ሶቪየት ኅብረት ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ጠብቀው ቆይተዋል። በርካታ የአፍሪቃ ሃገራት መሪዎችም ሩስያን እንደ ተባባሪ ሀገር ነው የሚመለከቱት ይላሉ ጉዊዶ ላንፍራንቺ። ያንንም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የድምፅ አሰጣጥ ላይ ዐሳይተዋል ሲሉ አክለዋል።

በተጨማሪም ሩስያ ለአፍሪቃ የጦር መሣሪያ በማቀበል ከፍተኛ ሚና ትጫወታለች ብለዋል። በምጣኔ ሐብት በኩል ያለው ትብብር ዝቅ ቢልም ሩስያ አፍሪቃ ካስገባችው የጦር መሣሪያ 44 በመቶውን ድርሻ ትሸፍናለችም ብለዋል ተንታኙ። ሩስያ አፍሪቃ ውስጥ ያላት ተጽእኖ በብዙ መልኩ እያደገ መምጣቱንም አልሸሸጉም። ያም በመሆኑ ሩስያ አፍሪቃ ውስጥ የሚኖራት ሚና ጠንከር ሊል እንደሚችል ጉዊዶ ላንፍራንቺ ግምታቸውን አኑረዋል። የመገናኛ አውታሮች ከውጭ ሃገራት ወደ ሀገራቸው የሚላኩ ሥርጭቶችን በሰላ ዐይን መመልከት ይኖርባቸዋል ሲሉም አክለዋል።

ማርቲና ሽቪኮቭስኪ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ