1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሩሲያ ክተትና የምዕራባዉያን ዉግዘት

ሐሙስ፣ መስከረም 12 2015

ፕሬዝዳንት ፑቲን ተጠባባቂ ሀይላቸውን የጠሩበት ምክኒያት፤ ከዩክሬን ጋር ሰላም እንዲፈጠር ከማይፈልጉት መዕራባውያን መንግስታት ጥቃት ለመላከል እንደሆነ በመግለጽም፤ ዋሺንግተን፣ ለንደንና ብራስልስ ኬይቭ ጦረንቱን ወደ ሩሲያ እንድታሻግር ይፈልጋሉ ብለዋል።

https://p.dw.com/p/4HDzr
Russland | Wladimir Putin hält Rede an die Nation
ምስል Russian Presidential Press and Information Office/Russian Look/picture alliance

የሩሲያ ክተትና የምዕራባዉያን ዉግዘት

በአብዛኛዉ የሩሲያ ጦር የሚቆጣጠራቸዉ አራት የምስራቅ ዩክሬን ግዛቶች የሩሲያ ግዛት አካል ሆነዉ አካሎች ሆነው መቀጠል አለመቀጠላቸዉን የግዛቶቹ ሕዝብ በድምፁ እንዲወስን ሩሲያ የጠራችዉ ሕዝበ ዉሳኔ ነገ ይጀመራል።እስከ ፊታችን ማክሰኞ የሚቀጥለዉ ሕዝበ ዉሳኔ ሕጋዊነት ሲያወዛግብ የሩሲያዉ ፕሬዝደንት የሐገራቸዉ ተጠባባቂ ጦር በከፊል እንዲከት አጠዋል።ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በብዙ ሚሊዮን ከሚቆጠረዉ ተጠባባዊ ጦር እንዲከት ያዘዙት 300 ሺሕዉ ነዉ።ፕሬዝዳንት ፑቲን ተጠባባቂ ሀይላቸውን የጠሩበት ምክኒያት፤ ከዩክሬን ጋር ሰላም እንዲፈጠር ከማይፈልጉት መዕራባውያን መንግስታት ጥቃት ለመላከል እንደሆነ በመግለጽም፤ ዋሺንግተን፣ ለንደንና ብራስልስ ኬይቭ ጦረንቱን ወደ ሩሲያ እንድታሻግር ይፈልጋሉ ብለዋል። የአገራቸው ሉዑላዊነትና የህዝባቸው ደህንነት ስጋት ውስጥ ከወደቀ የማይጠቀሙበት የጦረ መሳሪያ እንደማይኖርም ፕሬዝዳንት ፑቲን  አስጠንቅቀዋል። “ሩሲያ አንዳንድ የኔቶ አባል አገሮች ካላቸው አውዳሚ የጦር መሳሪያ የበለጡ ዘመናዊ መሳሪያች ባለቤት ናት። በአገራችን ሉዑላዊነትና አንድነት ላይ የሚቃጣ ጥቃት ካለ፤ ያለጥርጥር ያሉንን መሳሪያዎች ከመጠቀም ወደኋላ አንልም በማለት ይህ ንግግራቸው እንዲሁ ለማስፈራሪያ የተነገረ እንዳልሆነም አስግንዝበዋል። 
በዚህ የፕሬዝድንት ፑቲን ተጫማሪ ወታደሮችን የመጥራት ውሳኔ፣ የንውክለር መሳሪያ የመጠቀም ዛቻና በሩሲያ በተያዙት የዩክሬን ግዛቶች ህዝበ ውሳኔ የሚደረግ መሆኑ፤ በኒውዮርክ የመንግስታቱ ድርጅት  ጠቃላላ ጉባኤ ለመገኘት የተሰብሰቡትን የመዕራብ መንግስታት መሪዎች አጩጩኋል። የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ማክሮን የጀርመኑ ቻንስለር ሹልዝ ከዚያው ከኒዮርክ ፕሬዝዳንት ፕቱንን በጥብቅ አውግዘዋል። ፕሬዝዳንት ማክሮን በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግርም፤ አባል መንግስታት ሩሲያ እያራመደች ነው  ያሉትን የጦረኝነት ፖሊሲ ለማስተው  ጫና በማድረግ ከምዕራባውያን መንግስታት ጋር እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል።  
ፕሬሬዝዳንት ባይደን በበኩላቸው በዩክሬን ላይ የተከፈተውን ጦርነት አንድ የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት አባል የሆነ አገር (ሩሲያ ማለታቸው ነው)  ጎረበቱ የሆነን ሉዑላዊ አገር ከካርታ ለመፋቅ የሚያደርገው ጥረት ነው በማለት ኮንነውታል።  
ፕሬዝዳንት ባይደን አክለውም፡ “ሩሲያ ለጦርነቱ ተጨማሪ ወታደሮችን መጥራቷና የዩክሬን ግዛቶችን ለማጠቃለል የይስሙላ ህዝበ ውሳኔ ለማካሄድ መወሰኗ፤ የመንግስታቱ ድርጅትን ቻርተር የሚጻረርና የሚወገዝ ድርጊት ነው ሲሉ በተለይ ፕሬዝድንት ፑቲንን በዓላም መሪዎች ፊት ወንጅለዋል። 
ከሞስኮ ኪይቭና ኒውዮርክ የሚሰሙት ድምጾች የዩክሬኑ ጦርነት አሁንም ሰዎችን መግደል ማፈናቀሉን፤ መላው ዓለምም በዚህ ጦርነት ምክኒያት መታመስ መቸገሩ የሚቀጥል መሆኑን የሚሳይ እንደሆነ ነው ታዛቢዎች የሚናገሩት።  
ባለፉት ጥቂት ቀናት የዩክሬን ወታደሮች በተወሰኑ አካባቢዎች ሩሲያኖችን ወደኋላ እየገፉ መሆኑ ሲገለጽ የቆየ ሲሆን፤ ይህ የፕሬዝዳንት ፑቲን ውሳኔ በዩክሬን ሀይሎች እየተገኘ ነው የተባለውን ወታደራዊ ድል በመቀልበስ ሩሲያን ለወሳኝ ድል ሊያበቃ ይችል ይሆናል የሚሉ ተንታኖች እንዳሉ ሁሉ ፤ ውሳኔው እንደውም የሽንፈትና ተስፋ መቁረጥ ማሳያ ነው የሚሉም አሉ።  የኔቶ ዋና ጸሀፊ ሚስተር ስቶንቴልበርግ እንደሚሉት ግን የፕሬዝዳንት ፑቲን  የተጠባባቂ ሀይል ጥሪ፤ ፕሬዝዳቱ ስለጦርነቱ የነብራቸውን የተሳሳተ ስሌት የሚያሳይ ነው: “የተጣባባቂ ሀይል መጠራቱ የሚያሳየው የፕሬዝድንት ፑቲንን የተሳሳተ ስሌት ነው። እስካሁን እንዳየነው የሩሲያ ወታደር የተሟላ ትጥቅና ስንቅ የለውም። ያደረጃጀትና አመራርም ችግር አለበት በማለት ተጨማሪው ሀይል ጦርነቱን ለሁሉም ወገኖች የበለጠ አስከፊ ከሚያደርገው በስተቀር የጦርነቱን ውጤት ፕሬዝዳንት ፑቲን እነሚፈልጉት አይለውጠውም ብለዋል ፤ የኔቶ አባል አገሮች ለዩክሬን የሚሰጡትን እርዳታ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በመግለጽ ጭምር ። 

Russland l Proteste gegen Teilmobilmachung l Moskau
ምስል Vyacheslav Prokofyev/TASS/dpa/picture alliance
Bildkombo | Wladimir Putin und Olaf Scholz
ምስል Kay Nietfeld/Sputnik/AP/dpa/picture alliance
US-Präsident Joe Biden spricht vor der UN
ምስል Evan Vucci/AP/picture alliance

ገበያው ንጉሴ 

ነጋሽ መሀመድ

ሸዋዬ ለገሰ