1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚአፍሪቃ

የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ትኩሳት በአፍሪካ ገበያዎች

ረቡዕ፣ የካቲት 30 2014

ኢትዮጵያ ከዩክሬን ጦርነት በብዙ ሺሕ ኪሎ ሜትሮች ብትርቅም ቀውሱ ካስከተለው ኤኮኖሚያዊ ጫና መቋደሷ አይቀርም። በዓለም ገበያ ከሚሸጠው ስንዴ 30 በመቶ ድርሻ ያላቸው ዩክሬንና ሩሲያ በበቆሎና የሱፍ አበባ ዘይት ግብይት ሚናቸው ላቅ ያለ ነው። ስንዴን የመሰሉ የእህል አይነቶች ዋጋ ማሻቀብ በአፍሪካ አገራት የምግብ ዋጋ መረጋጋትን ሊያውክ ይችላል።

https://p.dw.com/p/48F7w
Russland Getreide Weizenanbau
ምስል Dmitry Feoktistov/dpa/TASS/picture alliance

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ትኩሳት በአፍሪካ ገበያዎች

ባለፈው ሳምንት ወደ ፖላንድ አቅንተው የዩክሬን ስደተኞችን ያነጋገሩት የዓለም የምግብ መርሐ-ግብር (WFP) ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤስሌይ ሩሲያ የጀመረችው ጦርነት በዓለም የሸቀጥ ገበያ ያስከተለው ጫና አስግቷቸዋል። ከጦርነቱ መቀስቀስም በፊት በግጭት፣ የከባቢ አየር ለውጥ እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ በርካታ የዓለም አገራት በጎርጎሮሳዊው 2022 ዓ.ም ለብርቱ ረሐብ ተጋልጠዋል። "ጦርነቱ ያስከተለው መፈናቀል የዩክሬን የውስጥ ቀውስ ብቻ አይደለም። ቀውሱ በምግብ ሸቀጦች የአቅርቦት ሰንሰለት እና ዋጋ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል" ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ከጦርነቱ በፊት የዓለም የምግብ መርሐ-ግብር ከሚያስፈልገው ስንዴ 50 በመቶውን ከዩክሬን ይሸምት እንደነበር ገልጸዋል።

ዴቪድ ቤስሌይ ስንዴ "ይኸ የዳቦ ቅርጫት ዓለምን እንድንመግብ ረድቶናል" ያሉት ዴቪድ ቤስሌይ  የመን፣ ኢትዮጵያ እና ሶሪያን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ። "አሁን በዚህ ቀውስ ምክንያት የተከተለው የዋጋ ጭማሪ በወር ከ60 እስከ 75 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ያስወጣናል" ያሉት ኃላፊው በዳፋው "ምግብ የሚያገኙ ሰዎች ቁጥር ይቀንሳል፤ የሚራቡት ይጨምራል" ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ከሩሲያ ጋር ያላቸው የንግድ ግንኙነት ከአንድ በመቶ ያነሰ ነው። ግብጽ እና ኬንያ በአንጻሩ ከሩሲያ ያላቸው የንግድ ልውውጥ መጠን ወደ 2 በመቶ ገደማ ይጠጋል። ኢትዮጵያ ውጊያው ከሚካሔድበት ዩክሬን ያላት ርቀትም ሆነ ውስን የንግድ ልውውጧ ግን ከተጽዕኖዕው እንደማያድናት ኦክስፎርድ ኤኮኖሚስ በተባለው ተቋም ተንታኝ የሆኑት ካሊ ዴቪስ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

"ሩሲያ የተወሰኑ ሸቀጦች ለዓለም ገበያ ከሚያቀርቡ ዋንኛ አገሮች አንዷ ናት። የንግድ ልውውጥ መረበሽ እና በሩሲያ ላይ የሚጣሉ ማዕቀቦች የእነዚህን ሸቀጦች አቅርቦት ያስተጓጉላል። ኢትዮጵያ ከውጭ በምታስገባው ስንዴ ላይ በኃይል ጥገኛ በመሆኗ ተጽዕኖው ይደርስባታል። ምክንያቱም ሩሲያ እና ዩክሬን በጥምረት ስንዴን ጨምሮ የጥራጥሬ ምርቶችን በከፍተኛ ደረጃ ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡ አገሮች ናቸው። ስለዚህ ኢትዮጵያ እና በርካታ የአፍሪካ አገሮች በአቅርቦት እጥረት፤ የጥራጥሬ እና የስንዴ ዋጋ መጨመር የመሳሰሉ ተጽዕኖዎች ይደርሱባቸዋል። ምንም እንኳ ኢትዮጵያ የጥራጥሬ ምርቶችን በሙሉ ከሩሲያ እና ከዩክሬን ባታስገባም በጦርነቱ ምክንያት በዓለም አቀፍ ገበያ የተፈጠረው እጥረት በበርካታ የአፍሪካ አገሮች ተጽዕኖ ይኖረዋል" ሲሉ ካሊ ዴቪስ ተናግረዋል።

David Beasley
የዓለም የምግብ መርሐ-ግብር (WFP) ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤስሌይምስል Domenico Stinellis/AP Photo/picture alliance

በዓለም ገበያ ከሚቀርበው ስንዴ 30 በመቶው በዩክሬን እና በሩሲያ ማሳዎች የሚመረት እንደሆነ የዓለም የምግብ መርሐ-ግብር መረጃ ይጠቁማል። በዓለም ገበያ ከሚሸጠው በቆሎ 20 በመቶው፣ ከሱፍ አበባ ዘይት 80 በመቶው ዛሬ በዩክሬን ምድር ጦርነት ከገጠሙት ሁለቱ አገሮች የሚቀርብ ነው።

ይሁንና የዩክሬን ገበሬዎች የእርሻ ማሳቸውን ጥለው ከሩሲያ ወታደሮች ውጊያ ለመግጠም አሊያም ለደህንነታቸው ለመሸሽ ተገደዋል። ስንዴ እና በቆሎ የሚጫንባቸው ወደቦችም ተዘግተዋል። ሩሲያ በአንጻሩ ከዓለም ገበያ የሚያገል ብርቱ ማዕቀቦች ሰለባ ሆናለች። የቻይና አፍሪካ አማካሪ ተቋም መሥራች እና ዳይሬክተር አቶ አሌክሳንደር ደምሴ "የስንዴ ምርት ለዓለም ገበያ በማቅረብ ትልልቆቹ ዩክሬን እና ሩሲያ ነበሩ። ያ ምርት አሁን ወደ አፍሪካ አገሮች ሊገባ የሚችለው በከባድ መንገድ ነው። ባለፈው ሳምንት እንዳየነው ከሆነ ዋጋው በጣም ተጋኗል፤ ከሚገባው በላይ ከፍ ብሏል።  የነዳጅ ዘይትን ዋጋ ስናይ በአንድ በርሜል ወደ 140 ዶላር ደርሶ ነበር። አሁን ትንሽ ወረድ ብሏል። የነዳጅ ዘይት ዋጋ እና የስንዴ ዋጋ ቀጥታ የሰውን ሕይወት ይነካል ብዬ ነው የማስበው። ዳቦ ከሌለ አብዮት ይጀምራል" በማለት ጉዳዩ ፖለቲካዊ ጣጣ ሊያስከትል እንደሚችል ጠቁመዋል።

ስንዴን ጨምሮ የጥራጥሬ ግብይት ሰንሰለት ላይ የሚፈጠር መስተጓጎል በተለይ ለሰሜን አፍሪካ አገሮች እጅግ አሳሳቢ ሊሆን ይችላል። ግብጽ፣ ሞሮኮ እና ቱኒዝያ የገበያዎቻቸውን ፍላጎት ለማሟላት ከሩሲያ እና ከዩክሬን በሚሸምቱት ጥራጥሬ ላይ ጥገኛ ናቸው። ግብጽ ከዓለም ገበያ ከምትሸምተው ጥራጥሬ 60 በመቶው ከሩሲያ እና የዩክሬን የሚገዛ ነው። ይኸ በቱኒዚያ 46 በመቶ፣ በሞሮኮ ደግሞ 17 በመቶ ይደርሳል። የኤኮኖሚ ተንታኟ ካሊ ዴቪስ ግብጽ፣ ሞሮኮ እና ቱኒዝያ "ከሩሲያ እና ከዩክሬን በሚያስገቡት ጥራጥሬ ላይ ጥገኛ ናቸው። በአሁኑ ወቅት የአገራቸውን የጥራጥሬ ፍላጎት ለማሟላት የሚያስፈልጋቸውን ምርት ለማግኘት ትግል በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በዚህ ምክንያት ዳቦን ጨምሮ የሚያስፈልጓቸውን የምግብ አይነቶች ለማሟላት እጥረት ሊገጥማቸው ይችላል" ሲሉ ይናገራሉ።  

Bäckerhandwerk in Ägypten
"ከዚህ ቀደም ግብጽ የዳቦ ድጎማ በማቆሟ በርካታ ተቃውሞዎች ተነስተው፤ መንግሥትን ከሥልጣን ለማውረድም ተቃርበው ያውቃሉ" የሚሉት ኦክስፎርድ ኤኮኖሚስ በተባለው ተቋም ተንታኝ የሆኑት ካሊ ዴቪስ የስንዴ ዋጋ መናር አሁንም ጣጣ ሊያስከትል እንደሚችል ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። ምስል Fadel Dawod/NurPhoto/picture alliance

"ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር በጀመረው የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ ግብር መመሠረት የግብጽ መንግሥት ለተለያዩ ጉዳዮች የሚያደርገውን ድጎማ ለማቆም መወሰኑን ባለፈው አመት ይፋ አድርጓል። የግብጽ መንግሥት ሊያቋርጥ ካሰባቸው ድጎማዎች መካከል አንዱ ለዳቦ የሚደረገው ነው። በመጪዎቹ ሳምንታት የጥርጣሬ እና የዳቦ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር ስለሚችል ይኸን ድጎማ ማቋረጥ እንዲህ ቀላል አይሆንም" በማለት ጉዳዩ ቀድሞም በግብጽ ከነበረው ኤኮኖሚያዊ ሁኔታ ጋር ተደማምሮ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ገልጸዋል። "ከዚህ ቀደም ግብጽ የዳቦ ድጎማ በማቆሟ በርካታ ተቃውሞዎች ተነስተው፤ መንግሥትን ከሥልጣን ለማውረድም ተቃርበው ያውቃሉ። ስለዚህ በተለይ በሰሜን አፍሪካ የምግብ ዋጋ መናር የፖለቲካ አደጋ ያስከትላል። በቅርቡ በሞሮኮ የነዳጅ ዋጋ መጨመርን በመቃወም የአገሪቱ ሰላማዊ ሰዎች አደባባይ ወጥተዋል። ስለዚህ ጉዳዩ ተጨማሪ ፖለቲካዊ አደጋ ያስከትላል" ብለዋል።

ለተወሰኑ የአፍሪካ አገሮች የዩክሬን ጦርነት እና በሩሲያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች መልካም ዕድል ማቅረባቸው አይቀርም። ነዳጅ እና ጋዝ አምራች የሆኑ እንደ አንጎላ፣ አልጄሪያ፣ ሊቢያ እና ግብጽ ያሉ አገሮች በዓለም ገበያ የታየው የዋጋ ንረት ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ኦክስፎርድ ኤኮኖሚክስ በጉዳዩ ላይ ያዘጋጀው ትንታኔ ያሳያል። በትንታኔው መሠረት ፖላድየም፣ ወርቅ እና ዳይመንድ የመሳሰሉ ማዕድናት ዋጋ ሲጨምር እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ቦትስዋና፣ ዚምባብዌ፣ ታንዛኒያ እና ጋና ያሉ አገራት ሊጠቀሙ ይችላሉ።  በአይረን፣ ብረት እና አሉሙኒየም ዋጋ ማሻቀብ ደግሞ ሞዛምቢክ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ናሚቢያ የተሻለ ገበያ ሊኖራቸው ይችላል። ይኸ የሚወሰነው ግን ሰነዱ እንደሚለው አገራቱ የተከፈተውን የገበያ ጉድለት በቅጡ መጠቀም ከቻሉ ብቻ ነው።  

ሩሲያ ከአውሮፓ ኅብረት እና ሌሎች እንደ ኅብረቱ ማዕቀብ ከጣሉ አገሮች ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት ሲገታ ለአፍሪካ ላኪዎች ኹነኛ ዕድል ሊፈጠር ይችላል። ይሁንና ሩሲያ ከተቀረው የዓለም ክፍል የነበራት የመጓጓዣ ግንኙነት የገጠመው መሰናክል እና የተወሰኑ ባንኮቿ ስዊፍት ከተባለው ዓለም አቀፍ የክፍያ ሥርዓት ውጪ መሆናቸው መልሶ እንቅፋት መፍጠሩ እንደማይቀር የኦክስፎርድ ኤኮኖሚክስ ተንታኞች ያስረዳሉ።

Nigeria Amenem Abfackeln von Gas auf Total-Ölplattform
ለተወሰኑ የአፍሪካ አገሮች የዩክሬን ጦርነት እና በሩሲያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች መልካም ዕድል ማቅረባቸው አይቀርም። ነዳጅ እና ጋዝ አምራች የሆኑ እንደ አንጎላ፣ አልጄሪያ፣ ሊቢያ እና ግብጽ ያሉ አገሮች በዓለም ገበያ የታየው የዋጋ ንረት ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ኦክስፎርድ ኤኮኖሚክስ በጉዳዩ ላይ ያዘጋጀው ትንታኔ ያሳያል።ምስል PIUS UTOMI EKPEI/AFP

"ከውጪ በሚያስገቡት ምርት ላይ ጥገኛ የሆኑ አገሮች አሁን ባለው የገበያ ሁኔታ ከሩሲያ እና ዩክሬን የሚሸምቱትን ለመተካት ስለሚቸገሩ የምግብ ዋጋ መረጋጋት ላይ ተጽዕኖ ሊደርስባቸው ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ የነዋሪዎች ወጪ ስለሚጨምር ፖለቲካዊ አደጋም ያስከትላል" በማለት ካሊ ዴቪስ አስረድተዋል።

ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችው ጦርነት መጨረሻ እጣ-ፈንታ አለመታወቅ እና ሩሲያ በተወሰኑ ሸቀጦች የገቢ እና ወጪ ግብይት ላይ ማዕቀብ ለመጣል መዘጋጀቷ ለተወሰኑ አገሮች ሌላ ውስብስብ ሁኔታ እንደፈጠረ የኤኮኖሚ ተንታኟ ተናግረዋል።  የሩሲያ ባለሥልጣናት "የትኞቹን አገሮች እና የሸቀጦች ግብይት እንደሚያግዱ አናውቅም" የሚሉት ካሊ ዴቪስ "ይኸ ደግሞ ወደ ፊት ሩሲያ ከአፍሪካ እና ከአውሮፓ ጋር የሚኖራት ግንኙነት መልክ ይወስናል። ስለዚህ ምን እየመጣ እንደሆነ አናውቅም። ነገር ግን በእርግጠኝነት ለአንዳንድ አገሮች በመንግሥት ወጪ ላይ አንዳች አንድምታ ይኖረዋል። በወጪ ንግድ ላይ ጥገኛ የሆኑ የተወሰኑ አገሮች በአንጻሩ ተጠቃሚ ይሆናሉ" ብለዋል።

ሩሲያ ከምዕራባውያኑ ስትቃቃር የተፈጠረውን የገበያ ዕድል የመጠቀሙ ጉዳይ ግን የአፍሪካ መሪዎች በሚይዙት ዲፕሎማሲያዊ አቋም ይወሰናል። ከአውሮፓ እና ከአሜሪካ የጠበቀ የንግድ ልውውጥ ያላቸው የአፍሪካ አገራት በማዕቀብ መደራረብ ለመንገዳገድ ከተገደደው የሩሲያ ኤኮኖሚ ይልቅ ቀድሞም የነበረ ጥቅማቸውን ማስጠበቅን ሊመርጡ እንደሚችሉ ባለሙያዎች ያምናሉ። ባለፉት ዓመታት ከሞስኮ ግንኙነታቸውን ያጠበቁ የተወሰኑ የአፍሪካ አገሮችም ቢሆኑ ከሩሲያ የሚያደርጉት የንግድ ልውውጥ በጥንቃቄ የተሞላ ሊሆን ይችላል። አቶ አሌክሳንደር እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ከውጪ በሚሸምቷቸው እና ዋጋቸው በዓለም አቀፍ ገበያ በሚወሰን ሸቀጦች ላይ ካላቸው ጥገኝነት መላቀቅ እንደሚያሻቸው ያስረዳሉ። በምዕራባውያኑ እና በሩሲያ መካከል በበረታው ትንቅንቅ ወደ አንዱ ማዳላትም ዘላቂ ጠቀሜታ ላይኖረው ይችላል።

አቶ አሌክሳንደር "ራሳችንን መቻል ስንጀምር በዓለም አቀፍ ገበያ ዋጋቸው የሚወሰን እንደ ስንዴ አይነቶች ምርቶች ላይ ብዙ እንዳንቸገር ያደርገናል። ከዚያ አልፎ በግድ ለአንድ ወገን ብቻ መደገፍ ብዙ ያስኬደናል ብዬ አልገምትም። ሩሲያ እና ምዕራባውያን ሲፋጠጡ የራሳችንን መንገድ ብንፈጥር፤ ገለልተኛ የሆነ አቋም ብንይዝ ይመረጣል" ሲሉ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ