1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሩሲያ ነዳጅ እና የአውሮፓ ኅብረት ስድስተኛ ማዕቀብ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 25 2014

የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት በሩሲያ ላይ ስድስተኛ ማዕቀብ ለመጣል ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ የኅብረቱ የዉጪ ግንኙነት ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል ዛሬ ይፋ አድርገዋል። ኃላፊው እንዳሉት ማዕቀቡ ተጨማሪ የሩሲያ ባንኮችን ስዊፍት ከተባለው ዓለም አቀፍ የክፍያ ሥርዓት ለማገድን ይጨምራል። ሩሲያ ለኅብረቱ የምታቀርበው ነዳጅ ሌላው የማዕቀቡ ዒላማ ነው።

https://p.dw.com/p/4AmSR
Schwedt PCK-Raffinerie bei Nacht
ምስል Patrick Pleul/dpa/picture alliance

አውሮፓ እና ጀርመን፦ የሩሲያ ነዳጅ እና የአውሮፓ ኅብረት ስድስተኛ ማዕቀብ

የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በአውሮፓ ህብረትና አባል አገሮች ላይ የደህንነት ስጋት ከመፍጠሩ ባሻገር፤ የኢኮኖሚ ተጽኖውም እያደገና እየከፋም ነው። ጦርነቱን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኖች ወደ ህብረቱ አገሮች እንዲሰደዱ በማስገደድ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና ፈጥሯል፤ የኑሮ ውድነተንም አስከትሏል።  አባል አገራቱ በተናጠልና በህብረት፤ በአንድ በኩል ለዩክሬን በሚሰጡት የገንዘብና የመሳሪያ እርዳታ፤ በሌላ በኩል፤ በሩሲያ ላይ እየወስዷቸው ባሉት የማዕቀብ እርምጃዎች ለክፈተኛ ወጭ እንደተጋለጡና ኢክኖሚያቸው እየተዛነፈ እንደሆነ እየተገለጸ ነው። ከአንድ ወር በላይ በዘለቀው ጦርነት የአውሮፓ ህብረት ለዩክሬን ካንድ ቢሊዮን ኢሮ በላይ እንዳወጣና በሩሲያ ላይ በሚወሰዱት እርምጃዎች ምክኒያትም በአባል አገሮች ኢኮኖሚ ላይ እየደረሰ ያለው ጫና ወደ ሀዝቡ ደርሶ ኑሮውን እያናጋው መሆኑ በስፈው እየተስተዋለ ነው። ይህም ሆኖ ግን የህበረቱ አገሮች እስካሁን ለዩክሬን በሚሰጡት እርዳታም ሆነ በሩሲያ ላይ በሚወስዱት እርምጃዎች አንድነታቸውን ጠብቀው ነው የቆዩት። እስካሁን በሩሲያ ላይ አምስት ዙር ማዕቀቦችን የጣሉ ሲሆን፤ ስድስተኛውን ዙር የማዕቀብ ውስኔ ለማስተላለፉም በምክክር ላይ እንደሆኑ ነው ከኮሚሽኑ የሚወጡ መረጃዎች የሚጠቁሙት።  በዚህኛው ዙር ማዕቀብ፤ የሩሲያ ጋዝና ነዳጅ ዘይት እንዲካተቱ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለ ቢታወቅም፤ በዚህ በኩል ግን በአባል አገሮች ዘንድ ስምምነት መኖሩን ብዙዎች ይጠራጠራሉ።

 ሩሲያ በዓለም በነዳጅ ዘይት ምርት ቀዳሚ ከሆኑት አገሮች አንዷ ስትሆን፤ በተለይ ለአውሮፓ ዋናዋ የንዳጅ ዘይትና ጋዝ አቅራቢ ነች።፡ ከጠቅላላ የንዳጅ ዘይት ምርቷ ከ40-50 ከመቶውና ከጋዝ ምርቷ ደግሞ ከ60 ከመቶው በላይ ለአውሮፓ ገበያ የሚላክ ሲሆን፤ በዙዎቹ የአውሮፓ ህብረት አገሮችም የሩሲያ ነዳጅ ዘይትና ጋዝ ጥገኛ እንደሆኑ ነው የሚታወቀው። ኦስትርያ 80 ከመቶ፤ ጀርመን 55 ከመቶ ጣሊያን 40 ከመቶ የሚሆነውን የነዳጅ ፍላጎታቸውን ከሩሲያ በማግኘት ቀዳሚዎቹ የሩሲያ ደንበኖች ናቸው፡ ሩሲያም 60 ከመቶ የሚሆነውን ገቢያዋን ከነዳጅ ዘይት እንደምታገኝ ነው የሚታመነው። ቤሌላ በኩል ግን ከዩክሬን ጋር ባለው ጦርነት ሳቢያ ሩሲያ ጠል አቋም ያራምዳሉ በምትላቸው የህብረቱ አገሮች ላይ፤ አጸፋዊ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል ስትገልጽ የቆየች ሲሆን፤ ባለፈው ሳምንት አጋማሽም በፖላንድና ቡልጋሪያ ላይ የምትልከውን ጋዝ ማቋረጧን ዋናው የሩሲያ የሀይል ኩባንያ ጋዝፕሮም አስታውቋል።  ሩሲያ ለዚህ የስጠችው ምክኒያት ደንበኖቿ ለጋዝና ነዳጅ የሚከፍሉትን ገንዘብ በሩብል የሩስያ ገንዘብ እንዲከፍሉ ያቀረበችውን ጥያቄ ሁለቱ አገሮች አላሟሉም የሚል ነው ። የሁለቱም አገሮች መነግስታትም ሆኑ የአውሮፓ ህብረት ግን ከመጅመሪያው ግብይቱ በኢሮ እንዲደረግ በስምምነቱ የሰፈረ መሆኑን ገልጸው፤ የሩሲያ ድርጊት የተደረሰውን የንግድ ስምምነቱን የሚጥስ ነው በማለት አውግዘውታል።  የአውሮፓ ኮሚሺን የኢነርጂ ኮሚሽነር ካድሪን  ሲምሶን፤ የሩሲያ ውሳኔ አሁን ያለው ቀውስ ሌላ ምራፍ ነው በማለት ድርጊቱ ህገወጥ መሆኑን አስምረውበታል። ‘ውሳኔውን ምንም አይነት ማሳማኝ  ምክኒያት የሌለው፣ የተፈረሙ የንግድ ስምምነቶችንና ውሎችን የሚጥስና ለሌሎች አባል አገሮች ማስጠንቀቂያ እንዲሆንና ለመክፍፈልም ታስቦ የተወሰደ  እርምጃ ነው’ ሲሉ ኮንነውታል።  

Niederlande | LNG-Terminal Rotterdam
የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ስድስተኛ ማዕቀብ ካነጣጠረባቸው መካከል የሩሲያ የነዳጅ ግብይት ይገኝበታል። ምስል LEX VAN LIESHOUT/ANP/AFP/Getty Image

ሁለቱም ጋዝ የተቋረጠባቸው መንግስታት፤ ችግሩን ለመቋቋም ጥረት እያደረጉ ሲሆን፤ አባል አገሮችና ህብረቱም የሚረዷቸው መሆኑን እየገለጹላቸው ነው፡፤ በትናንትናው እለትም  ያባል አገሮች የኢነርጂ ሚኒስትሮች ልዩ ስብሰባ አድርገው ድርጊቱን በማውገዝ፤ ከሁለቱ አገሮች ጋር ያላቸውን አጋርነትና አንድነት ገልጸዋል። የፖላንድ የአየር ንብረት ሚኒስተር በበኩላቸው ሩሲያ በወስደችው እርምጃ ሊፈጠር የሚችለውን የሀይል አቅርቦት ችግር ለመቋቋም አገራቸው የተዘጋጀች መሆኑን በመግለጽ የሩሲያ ወዳጆች ካልሆኑ አገሮች ውስጥ ተመድበን ይህ እርምጃ የተላለፈብን መሆኑ ለኛ ክብር ነው ሲሉ ተስምተዋል 

ትናንት ብራስልስ የተሰበሰቡት የህብረቱ ሚኒስተሮችም፤  ለፖላንድና ቡልጋሪያ ድጋፍ በመስጠት ማንኛውም የህብረቱ ኩባንያ፤ ሩሲያ በጠየቀችው መሰረት ከጋዝፕሮም ጋር በሩብል ክፍያ እንዳይፈጽም በማሳሰብ ይህን ማድረግ  ግን፤ ህብረቱ በሩሲያ ላይ የጣለውን ማዕቀብ የሚጥስ መሆኑን ተስማምተውበታል ተብሏል:: የኮሚሽኑ  የኢነርጂ ኮሚሽነር ወይዘሪት ካድሪስ ይህንን ሲያብራሩ ‘በሩብል ክፍያ መፈጸም ስምምነቱን ለብቻ መቀየር መሆኑን አስታውቀናል ። እንዲህ አይነቱ ድርጊት በንግድ ህግም ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ፤ ህጉን ተጠቅሞ ውድቅ ማድረግ ታስፈልጋል’ በማለት ኮሚሽኑ ተጨማሪ መመሪያ የሚያስተላልፍ መሆኑንም ገልጸዋል ። 

ቀደም ሲልም የኮሚሽኑ ፕሬዝድንት ወይዘሮ ቮንዴርሌየን ሞስኮ ያቀረበችው ጥያቄም ሆነ የወሰደችው እርምጃ የህብረቱን አንድነት ለመፍታተን ክልሆነ በስተቀር፤ክፍያን በሩብል ለመፈጸም ውል የገባ ኩባንያ የለም በምለት 97 ከመቶ የሚሆኑትን የኩባንያ ውሎቹን እንዳዩና ሁሉም ክፍያ በዩሮ ወይም ዶላር እንዲሆን የሚጠይቁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ሆኖም ግን ጥቂት የማይባሉ የአባል አገሮች ኩባንያዎች ሩስያ በጠየቀችው መሰረት በጋዝ ፕሮም የዩሮና ሩብል ሂስብ በመክፈት ክፍያቸውን በሩብል ለመፍጸም ተስማምተዋል እየተባለ ነው። ። ሀንጋሪና ኦስትሪያ በግልጽ ሩሲያ በጠየቀችው መሰረት ክፍያቸውን በሩብል እየፈጸሙ ወደ የአገሮቻቸው የሚላከው ጋዝ እንዳይስተጓጎል የሚያደርጉ መሆኑን አስታውቀዋል። የሌሎቹ የህብረቱ አገሮች ኩባንያዎች ክፍያ ከአስራ አምስት ቀናት በሁዋላ መፈጸም ያለበት ሲሆን፤ ያኔ ሩሲያ የጠየቀችውን በማሟላት ክፍያውን ይፈጽማሉ ወይንስ የኮሚሽኑንን ማሳሰቢያ ያከብራሉ የሚለው ግን፤ በእርግጠኘት ማወቅ ይስቸግርል። 

ፕሬዝዳንት ፑቲን ይህን መመሪያ ያስተላለፉት  በማዕቀቡ ምክኒያት የተዳከመውን የአገሪቱን ገንዘብ ‘ሩብለስ ዋጋ ለማጠንከርና እንደተባለውም  የህብረቱን አንድነትንም ለመሸርሸር ነው ሲሉ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ሰዎች ይናገራሉ። ይህ እቅዳቸው ሙሉ በሙሉ የተሳክላቸው ስለመሆን አለመሆኑ  በርግጠኝነት መናገር ባይቻልም፤ አባል አገራቱን እያወዛገበ መሆኑና የጋዝና ነዳጅን ዋጋ መጨመሩ ብቻ ሳይሆን አቅርቦቱንም ከጥያቄ ውስጥ ያስገባ መሆኑ ግን እየታየ ነው።

ከዚሁ ሩሲያ በፖላንድና ቡልጋሪያ ላይ ከጣለችው የጋዝ ክልከላና በሩብል የመጠቀም አለመጠቀም ጉድዮች ጎን ለጎን፤ የህብረቱ አገሮች በቀጣይ በጋዝና ነዳጅ ላይ ማዕቅብ ስለሚጥሉበት ሁኒታ ተወያይተው  ከስምምነት ደርሰዋል ተብሷል። እሳክሁን ሀሳቡን ሲቃወሙ ክነበሩት አገሮች ውስጥ የነበረችው ጀርመን፤ አሁን ተቃውሞዋን የምታነሳ መሆኑን የኢኮኖሚ ሚኒስትሯ ሚስተር ሮበርት ሃቤክ ትናንት አስታውቀዋል። ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ ጀርመን ከንግዲህ ማዕቀቡን አትቃወመም።  ‘ጀርመን በሩሲያ ነዳጅ ላይ የሚጣለውን ማዕቀብ የማትቃወም መሆኑን ማረጋገጥ እወዳለሁ። በእርግጥ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላል  ግን ይህንኑ ለመክፈል ዝግጁ ነን` በማለት ጣቢያዎችንና የማስተላለፊያ መስመሮችን ለማስተካከል ግን ግዜ ወሳኝ መሆኑን አስታውሰዋል።፡

ህብረቱ በሩሲያ ነዳጅ ላይ የሚያስተላለፈው የማዕቀብ ውሳኔ በመጭው ታህሳስ ወር መጨረሻ የሚጸድቅ ይሆናል ተብሏል። የማእቀቡን እቅድ እስካሁን እንደተቃወሙ የቆሙት አስትሪያና  ሀንጋሪ ግን በልዩ ሁኒታ ውሳኔው የማይመለክታቸው ሆኖ እንደተዘጋጀ ተነግሯል። 

Pro russische Truppen Ukraine Krieg Azovstal
ሩሲያ እና ዩክሬን የሚያደርጉት ውጊያ እንደቀጠለ ነውምስል ALEXANDER ERMOCHENKO/REUTERS

ይሁን እንጂ የማዕቀቡ ተግባራዊነትም ሆነ በሩሲያ ላይ የተፈለገውን ውጤት ማምጣቱን የሚጠራጠሩ ጥቂቶች አይደሉም። አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ማዕቀቡ የነዳጅ ዘይትን ዋጋ በእጅጉ በማስደግ እንደውም ለሩሲያ ተጨማሪ ገቢ ሊያስገኝ ይችላል። ብራስልስ የሚገኘው የቡሩገል ተቋም የኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት ሚስተር ሲሞኔ ታግሊያፒየትራ፤ ማቀቡ ይተፈለገውን ውጤት ማምጣት መቻሉን ከሚጠራጠሩት ውስጥ ናቸው፤ `የአውርፓ ህብረት በሩሲያ ዘይት ላይ ማዕቀብ ቢጥል የነዳጅ ዘይት ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ሊጨምርና ሩሲያም ወደ ውጭ የምትልከው ሊቀንስ ቢችልም እንኳ ከዚያው ግን ደህና ገቢ ልታገኝ ትችላላች` ባይ ናቸው። በሳቸው እምነት የህብረቱ አላማ በመለስተኛ የኢኮኖሚ ጉዳት፤ ሚስተር ፑቲን ከነዳጅ ዘይት የሚያገኙትን ገቢ ማሳጣት ከሆነ፤ የተሻለው ዘዴ   በሩሲያ ነዳጅ ዘይት ላይ ተጨማሪ ታሪፍ መጣል ነው። 

 ይሁን እንጂ በሩሲያ ላይ የተፈለገውን ውጤት ያምጣም አያምጣም የህብረቱ አገሮች ግን ኮሚሽኑ ባቀረበው አጠቃላይ ማዕቀብ ተስማምተው ክታህሳስ ወር በኋላ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት መጀመራቸው እየተገለጸ ነው። በአንጻሩ ፕሬዳንት ፑቲን የሚስወዱት አጸፋዊ እርምጃ  ምን ሊሆን እንደሚችል በትክክል ባይታወቅም፤ በፖላንድና ቡልጋሪያ ላይ ከተወሰደው እርምጃ አንጻር ግን ጫና ፈጣሪ የአጸፋ እርምጃ ሊሆን እንደሚችል ነው የሚገመተው። ጦርነቱ እስከቀጠለ ድረስም፤ ዋናዎቹ ተጎጂዎች ከዩክሬን ቀጥሎ የአውሮፓ ህብረት አገሮች ሆነው እንደሜቆዩ ክወዲሁ ግልጽ ሁኗል። 

ገበያው ንጉሴ

እሸቴ በቀለ