1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምስራቅ አጎራባች ክልሎች የፀጥታ ዝግጅት እና የሚጠበቀዉ ምርጫና መንግስት ምስረታ

ዓርብ፣ መስከረም 7 2014

ከሁለት ሳምንታት በኃላ በሶማሌ እና አፋር ክልሎች የሚካሄደውን ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ለማስቻል በምስራቅ ሀገሪቱ የሚገኙ አጎራባች ክልሎች የፀጥታ ኮማንድ ፖስት በጋራ አቅዶ እየሰራ መሆኑ ተገልፃል፡፡

https://p.dw.com/p/40SsZ
Äthiopien Stadansicht Dire Dawa
ምስል DW/M. Teklu

የምስራቅ አጎራባቾች የፀጥታ ኮማንድ ፖስት የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ ውጤቶች እያመጣ ነው ተብሏል

ከሁለት ሳምንታት በኃላ በሶማሌ እና አፋር ክልሎች የሚካሄደውን ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ለማስቻል በምስራቅ ሀገሪቱ የሚገኙ አጎራባች ክልሎች የፀጥታ ኮማንድ ፖስት በጋራ አቅዶ እየሰራ መሆኑ ተገልፃል፡፡ መንግስት ሽብርተኛ ብሎ የፈረጀው ህወሀት እና የእሱ ተላላኪ የተባሉ ፀረ ሰላም ኃይሎች ለምርጫው ተግዳሮት ሊሆኑ እንደሚችሉ በማስቀመጥ አስፈላጊው ጥንቃቄ የሚደረግበት ሁኔታ መመቻቸቱን ተፀቅሷል ፡፡

የምርጫውን ሄደት ሰላማዊነት ከማረጋገጥ ባለፈ በዚሁ ወር የሚካሄዱ በዓላት እና በመስከረም 24 ቀን ይካሄዳል የተባለው የመንግስት ምስረታ የተለየ የፀጥታ ትኩረት የሚሹ በመሆናቸው የጋራ ኮማንድ ፖስቱ በተናጠል እና በጋራ እየሰራባቸው ነው ተብሏል፡፡

የድሬደዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮምሽን ኮምሽነር አለሙ መግራ የጋራ ምክክሩን አስመልክቶ በሰጡት መረጃ የምስራቅ ተጎራባች ክልሎች የፀጥታ ኮማንድ ፖስት በያዝነው ወር የሚካሄዱ በዓላት ፣ ምርጫ እና የመንግስት ምስረታ ኩነቶች ሰላማዊ እንዲሆኑ በጋራ ለመስራት አቅዶ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

Äthiopien Stadt Dire Dawa
ምስል DW/T. Waldyes

ኮምሽነሩ በሶማሌ እና ሀረሪ ከልሎች ከሁለት ሳምንታት በኃላ የሚካሄዱ ምርጫዎችን ሊያውኩ ይችላሉ ከተባሉ አካላት መንግስት ሽብረተኛ ብሎ የፈረጀው ህወሀት እና የእሱ “ተላላኪ ፀረ ሰላም” አካላትን በመጥቀስ ለመከላከል እና ማንኛውንም ህገ ወጥ ዝውውር ለመቆጣጠር የሚያስችል ዕቅድ ተቀምጦ በጋራ እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡

ኮምሽነሩ በቀጣይ የጋራ ፀጥታ ኮማንድ ፖስቱ ከምርጫው ፀጥታ ጋር በተያያዘ የተቀመጡ ዕቅዶችን አፈፃፀም ይገመግማል ቀጣይ አቅጣጫም ያስቀምጣል ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ የተለያዩ ኩነቶች በሚከናወኑበት በያዝነው ወር የተለየ የፀጥታ ጥበቃ ያስፈልጋል ያሉት ኮምሽነር ዓለሙ በተለይ የመንግስት ምስትረታውን ሊፈታተኑ የሚሞክሩ አካላትን እንቅስቃሴ ለመከላከል በአጎራባች ክልሎቹ የፀጥታ ኮማንድ ፖስት ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ የሶማሌ ፣ ሀረሪ እና አፋር ክልሎችን ጨምሮ ድሬደዋ አስተዳደር እንዲሁም የምስራቅ ሀረርጌ ዞንን የሚያካትተተው የምስራቅ አጎራባቾች የፀጥታ ኮማንድ ፖስት የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ የሚያግዙ ውጤቶች እያመጣ ነው ተብሏል፡፡

 

መሳይ ተክሉ

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ