1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምርጫ ዝግጅት፣ ፀጥታና ዉዝግብ  

እሑድ፣ ጥር 2 2013

አምና መደረግ የነበረበት ምርጫ ሁለቴ ለመራዘሙ የተሰጠዉ ምክንያት የፀጥታና የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭት የሚል ነዉ።ዘንድሮ፣ የኮሮና ተሕዋሲ የሚይዝና የሚገድለዉ ሰዉ ቁጥር ጨመረ እንጂ አልቀነሰም።ፀጥታዉም፣ ምርጫ ቦርድ «ሁኔታ» ብሎ ከገለፀዉ ከትግራይ እስከ መተከል፣ ከምዕራብ ኦሮሚያ (ወለጋ) እስከ አፋርና-ሶማሌ ድንበር ድረስ ሰዎች እየተገደሉ---

https://p.dw.com/p/3ni4O
Logo | National Election Board of Ethiopia
ምስል National Election Board of Ethiopia

ዉይይት፣ የኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግሮችና ምርጫ

የኢትዮጵያ 6ኛዉ አጠቃላይ ምርጫ ዘንድሮ ግንቦት 28 እንዲደረግ የሐገሪቱ አስመራጭ ኮሚሽን ሐሳብ አርቧል።ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣዉ የጊዜ ሠሌዳ መሠረት ለፖለቲካ ፓርቲዎች ዕዉቅና መስጠት ወይም መንፈግ፣ ለቴክኒካዊ ጥያቄዎች መልስና ማብራሪያ መስጠት፣ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን መክፈት የመሰሳሉ ዝግጅቶችን ጀምሯልም።

የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች መሪዎቻችን የሚመርጡት ሌላዉ አካባቢ በመረጠ በሳምንቱ፣ ሰኔ 5 ነዉ።ከዚሕ ቀደም የምርጫ ጊዜ በመራዘሙ ሰበብ (ምክንያት አላልኩም) የተካረረዉ ጠብ የዉጊያ አዉድ ባደረጋት ትግራይ ምርጫ መደረግ አለመደረጉን፣ ቦርዱ «የሁኔታዎች አመቺነት ታይቶ» እንደሚወሰን አስታዉቋል።

አምና መደረግ የነበረበት ምርጫ ሁለቴ ለመራዘሙ የተሰጠዉ ምክንያት የፀጥታና የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭት የሚል ነዉ።ዘንድሮ፣ የኮሮና ተሕዋሲ የሚይዝና የሚገድለዉ ሰዉ ቁጥር ጨመረ እንጂ አልቀነሰም።ፀጥታዉም፣ ምርጫ ቦርድ «ሁኔታ» ብሎ ከገለፀዉ ከትግራይ እስከ መተከል፣ ከምዕራብ ኦሮሚያ (ወለጋ) እስከ አፋርና-ሶማሌ ድንበር ድረስ ሰዎች እየተገደሉ፣ እየቆሰሎ፣እየተፈናቀሉም ነዉ።

በአብዛኞቹ የግጭት አካባቢዎች የተጣለዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ (በኢትዮጵያ መንግስት ቋንቋ ኮማንድ ፖስት) ቢያንስ እስካሁን አልተነሳም።ኢትዮያና ሱዳን የገጠሙት የድንበር ግዛት ይገባኛል ዉዝግብም እልባት አላገኘም።በአብዛኛዉ የደቡብ ኢትዮጵያ የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ሕዝብ ያነሳዉ የራስ-ገዝ አስተዳደርነት ጥያቄ መልስ አላገኘም።

ምርጫ ቦርድ ባወጣዉ የጊዜ ሰሌዳ ግንቦት 28 የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ነዋሪ የወደፊት አስተዳደሩን ለመወሰን ድምፅ ይሰጣል።የየትኛዉን መስተዳር መሪ መርጦ፣ የየትኛዉን መስተዳድር ሥልጣን እንዴትነት እንደሚወስን ማብራሪያ መጠበቅ ግድ ነዉ።የሕዝብ ቆጠራ ባለመደረጉ የኢትዮጵያ ሕዝብ-ባጠቃላይ፣ መምረጥ የሚችለዉ ዜጋ-በተለይ-ስትነት በግልፅ አይታወቅም።የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፣ ታዋቂ ፖለቲከኞችና ደጋፊዎቻቸዉ ታሥረዋል። መገናኛ ዘዴዎቻቸዉ ተዘግተዋል።ከሐገር ዉጪ የሚገኙ ሙሕራን ሳይቀሩ «ሐገር አፍራሽ» ተብለዉ የእስር ዋራንት ተቆርጦባቸዋል።

የመንግስት ባለስልጣናት፣ መንግስት የሚቆጣጠራቸዉና የሚደጉማቸዉ ምንደኛ «ጋዜጠኛ» ተብዬዎች፣ መገናኛ ዘዴዎችና ብሎገሮች፣ ገለልተኛ መገናኛ ዘዴዎችና ጋዜጠኞችን ማኪኪያስ-መሳደባቸዉን እንደቀጠሉ ነዉ።ከኮሮና በተጨማሪ የአንበጣ መንጋ ወረርሺኝ ብዙ ሕዝብ የዕለት ጉርሱን እያሳጣ ነዉ።በዚሕ መሐል ምርጫ ማድረግ ይቻል ይሆን? ምንም ዓይነት ምርጫ?

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ