1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ማብራሪያ 

ሐሙስ፣ ጥር 27 2013

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሕዝብ ለቀረቡ ጥያቄዎች ዛሬ መልስና ማብራሪያ ሰጠ። የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ «በብዛት ቀረቡ» ያሏቸው የምርጫ ዝግጅት፣ የፀጥታ ሁኔታና ተአማኒነትን ለሚመለከቱ ጥያቄዎች ማብራሪያና መልስ ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ከሕዝብ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ቀጥተኛ መልስና ማብራሪያ ሲሰጡ ብዙም አይታዩም።

https://p.dw.com/p/3otjK
Äthiopien Sidama stimmen für Teil-Autonomie
ምስል AFP/M. Tewelde

«አዲስ ጅምር ለሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ»

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ካለፈዉ ሰኞ ጀምሮ «ምርጫ ቦርድን ይጠይቁ» የሚል መልዕክት በትዊተርና ፌስ ቡክ ገፁ አሰራጭቶ ነበር። ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ዛሬ ማርፈጃዉ ጀምሮ መልስና ማብራሪያ የሰጡት  ባለፉት 3 ቀናት ከተለኩ ከአንድ ሺህ በላይ ጥያቄዎች በየፈርጁ ለሰደሯቸዉ በብዛት ለቀረቡ ጥያቄዎች ነዉ። የቦድሩ ሰብሳቢ ማብራሪያቸውን የጀመሩት «በአዲስ አበባና ድሬደዋ ለፓርላማ እና ለክልል የሚደረገው ምርጫ ቀኑ ለምን የተለያየ ሆነ?» ለሚለዉ ጥያቄ ነዉ። ሰብሳቢዋ ለጥያቄዉ ተደጋጋሚ መልስ መሰጠቱን ጠቅሰዉ፣ በከተማዎቹ ላይ በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉት የቀበሌ፤ የወረዳ እንዲሁም የክፍለ ከተማ አዳዲስ አደረጃጀትና ለውጦች ምክንያት ሊያጋጥም ይችላል በሚል ከሰጡት ረዥም ማብራሪያ ተከታዩ ይገኝበታል። 

«አሁን ባለው የክፍለ ከተማ አደረጃጀት ምክንያት፤ የክፍለ ከተማው አደረጃጀት የድሮውን ወረዳ ስለማይከተል ማለት ነው አንድ ሰፈር ያሉ ሰዎች ለክልል ምክር ቤት በሌላ ጣቢያ መምረጥ ሊገባቸው ይችላል ለፓርላማ ደግሞ በሌላ ጣቢያ መምረጥ ሊገባቸው ይችላል። በአችሩ ለማስቀመጥ፤ እነዚህ ሁለት የምርጫ ክልሎች ወሰናቸውና አደረጃጀታቸው በጣም ምስቅልቅል ያለ በመሆኑ የተነሳ ለአፈጻጸም በጣም ስለሚያስቸግረን ነው።»
ይኽ አስቸጋሪነቱ ለምርጫ አስፈጻሚዎች ብቻ ሳይሆን ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ቢሆን እጩዎቻቸውን የቱ ጋር እንደሚወስዱ፤ ቅሬታቸውንም ቢሆን ወደየትኛው የምርጫ ክልል እንደሚያቀርቡ ሁሉ ግልፅ እንዳልሆነም ዘርዝረዋል። ለፓርላማው ሁለት መቀመጫ ያላት ድሬደዋን በተመለከተም የክልል ምክር ቤት አባላት በ47ቱ ቀበሌ እንደሚመረጥ በመጠቆምም አደረጃጀቶቹ ፍፁም አይገናኙም ያሉት የምርጫ ቦርዱ ሰብሳቢ የምርጫው ቀን መለየቱ ፖለቲካዊ አንድምታ አለው የሚለውን ጥርጣሬ አጣጥለዋል። ከዚህ በተያያዘም ሁለት ቦታ የመምረጥ ጥርጣሬን በተመለከተ ቦርዱ አስቀድሞ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለመቆጣጠር ጥንቃቄ ማድረጉን ተናግረዋል።
በምርጫው ሂደት የተለያዩ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ የሚል ስጋትን አስመልክቶም በርካቶች መጠየቃቸዉን የጠቀሱት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ቅሬታዎች የሚቀርቡባቸውን መንገዶችም አብራርተዋል። ሌላው ብዙ ጥያቄ የቀረበበት፣ ምርጫው የሐገሪቱን የጸጥታ ችግርን ሊያባብስ አይችልም ወይ? የሚል መሆኑን በመግለጽ ፀጥታውን የማረጋገጥ በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላት ኃላፊነት እንደሆነ አስታዉቀዋል።
የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ዛሬ ከአንድ ሰዓት በላይ ወሰደው በፌስቡክ የቀጥታ ስርጭት ማብራሪያ ከሰጡባቸው የሕዝብ ጥያቄዎች መካከል ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸው የተለያዩ አቤቱታዎች፤ የአንዳንድ ፓርቲዎች የውስጥ ውዝግብ፣ ክልል የመሆን ጥያቄ ያቀረቡ አካባቢዎች ጉዳይ፤ እንዲሁም ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ስላለው ሕጋዊነት የሚመለከቱ ጥያቄዎች መነሳታቸዉም ተወስቷል።  የምርጫ ታዛቢያዎችን በተመለከተ ቀድሞ ምርጫ ቦርድ ታዛቢዎችን ያስመርጥ ነበር፣ እንዲታዘቡ የሚመረጡትም የመንግሥት ደጋፊዎች እንደነበሩ ምንም «አንደባበቅም» ያሉት የቦርዱ ሰብሳቢ አሁን ይህን ምርጫ ቦርዱ እንደማያደርግ አሳውቀዋል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሻለ ምርጫ ለማካሄድ አስተማማኝ ቁመና ላይ ነው ያሉት ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ እንደዛሬው ያለው ከሕዝብ የሚያገኘው መድረክ ቀጣይነት እንደሚኖረው ተናግረዋል። 
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ብዙ አነጋጋሪ በሆነው በሀገሪቱ ምርጫ ጉዳይ በግላጭ ከሕዝብ ጥያቄዎችን በማሰባሰብ መልስና ማብራሪያ ሲሰጥ ያሁኑ የመጀመሪያዉ ነዉ።ማብራሪያዉን ከሁለት ሺህ በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ተከታትለውታል። ከተከታተሉት በርካቶች ቦርዱ ለየት ያለ ጅማሮ ማሳየቱን ቢያበረታቱም፣ የዚህ ወይም የዚያ ፓርቲ ተወካይ በሚል ትችት የሰነዘሩም አልጠፉም።አጋጣሚዉን በመጠቀም የተለያዩ «የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ» የሚሉ ጥያቄዎችን ደጋግመው የጻፉም አሉ። የምርጫ ቦርድ ከትናንት ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል የብልፅግና  ፓርቲን ለመደገፍ  በተባለው ሰልፍ ላይ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲያችን ያለ አግባብ ተወንጅሏል ይህም ፓርቲዎች የፈረሙትን የጋራ የስነምግባር ስምምነት ደንብ የጣሰ ነው ሲል ለቦርዱ ላቀረበው አቤቱታም ትናንት ምላሽ ሰጥቷል።
የምርጫ ቦርዱ ከደረሰው አቤቱታ በተጨማሪ አብን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ፓርቲዎችም ያለ አግባብ መነሳታቸውን መከታተሉን በመጠቆም «ሰልፎቹ ላይ የተንጸባረቁት ንግግሮች እና መፈክሮች በአዋጁ አንቀጾች ላይ የተደነገጉት ላይ የስነምግባር ጥሰት ተፈጽሞ አግኝቻለሁ ሲል ትናንት መግለጫ አውጥቷል። በቀጣይም በምርጫ ቅስቀሳ ንግግርና ሌሎች ለሕዝብ የሚሰራጩ መልእክቶች ላይ ክትትል በማድረግ እንደአስፈላጊነቱ እስከእጩ መሰረድ የሚያደርስ አስተዳደራዊ ርምጃ ሊወስድ እንደሚችልም አሳስቧል። 

Logo | National Election Board of Ethiopia
ምስል National Election Board of Ethiopia

 ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ