1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስልጠና ለሲቪክ ማኅበራት

ሰኞ፣ ሚያዝያ 4 2013

ምርጫው ሁሉንም ኅብረተሰብ ማሳተፍ እንዳለበት ያመለከቱት አቶ ዳን ሲቪክ ማህበራት በዚህ ረገድ ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፣ በተለይም ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችና የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች በምርጫው እንዲሳተፉ መትጋት እንደሚያስፈልግ አቶ ዳን አብራርተዋል፡።አንዳንድ የሲቪክ ማህበራት “ የበጀት እጥረት አጋጥሞናል” የሚል ቅሬታ እያቀረቡ ነው፣

https://p.dw.com/p/3rtP4
Äthiopien Dan Yirga
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ስልጠና ለሲቪክ ማኅበራት

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ ኢሰመጉ መጪው ምርጫ ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሲቪክ ማህበራት በምርጫው ሂደት በስፋት መሳተፍ እንደሚገባቸው አስታወቀ።ምርጫው ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ማካተት እንደሚኖርበትም አመልክቷል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ (ኢሰመጉ) ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የምስራቅ አፍሪካ ጽ/ቤት፣ ከኢትዮጰያ ሰብአዊ መብት ድርጅቶች ህብረትና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ሲቪክ ማህበራት በመጪው ምርጫ ስለሚኖራቸው ሚና ሰሞኑን በባህር ዳር ትምህርት ሰጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳን ይርጋ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት የስልጠናው ዓላማ ሲቪክ ማህበራት በምርጫው ሂደት ሲለሚከናወኑ ተግባራት፣ ስፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር ማዘጋጀት ፣ ስከሰብአዊ መብቶች እና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ ትምህርት መስጠት ነው፡፡ በስልጠናው የሚሳተፉትም በአማራ ክልል የሚገኙ የሲቪክ ማህበራት አካላት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ምርጫው ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ባሳተፈ መልኩ መካሄድ እንዳለበት ያመለከቱት አቶ ዳን ሲቪክ ማህበራት በዚህ ረገድ ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፣ በተለይም ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችና የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች በምርጫው እንዲሳተፉ መትጋት እንደሚያስፈልግ አቶ ዳን አብራርተዋል፡፡ አንዳንድ የሲቪክ ማህበራት “ስለምርጫ ለማስተማር የበጀት እጥረት አጋጥሞናል” የሚል ቅሬታ እያቀረቡ ነው፣ ችግራቸው እንዴት ሊፈታላቸው ይችላል? ተብለው የተጠየቁት ዋና ዳይሬክተሩ፣ “ሲቪክ ማህበራት ወደስራው ሲገቡ የሚያቀርቡት እቅድና በጀት በሚመለከተው አካል ታይቶና ተፈቅዶ መሆኑን ጠቁመው የሚያግዝ አካል ከተገኘ ማህበራቱን በገንዘብ፣ በስልጠናና በሰው ኃይል መደገፍና ማጠናከር ግን ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ምርጫው ለኢትዮጵያውያን ትርጉም ያለው በመሆኑ በተገቢው መንገድ እንዲካሄድ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የምስራቅ አፍሪካ ጽ/ቤት ተወካይ አቶ ኪነጥበብ አረጋ በበኩላቸው ማንም ሰው በአስተሳሰቡ የአካል ጉዳትም ሆነ ሌላ አደጋ ሊደርስበት እንደማይገባ አስረድተዋል፡፡ ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ከባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ሴት ተማሪዎች ፌደሬሽን የተገኘችው ፌቨን ሃይሉ ስልጠናውን በተመለከተ ጠይቀናት “ምርጫን እንዴት መታዘብ እንደሚገባና ችግሮች ቢፈጠሩ እንኳ እንዴት መፈታት እንዳለባቸው ከስልጠናው ትምህርት አግኝተናል” ብላለች፡፡ ተመሳሳይ ስልጠና ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በሀዋሳ መደረጉንና በቀጣይ አዳማን ጨምሮ በሌሎች ከተሞችም እንደሚሰጥ የሰብዓዊ መብት ጉባዔ አስታዉቋል፡፡ 
ዓለምነው መኮንን
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ