1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምሥራቅ ወለጋ ነዋሪዎች እሮሮ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 3 2014

በኦሮሚያ ክልል፤ ምስራቅ ወለጋ ዞን፤ ኪራሙ ወረዳ ሀሮ በተባለች ቀበሌ ካለፈው እሁድ  አንስቶ በታጣቂዎች የተገደሉ ሰዎች ከ22 በላይ መሆናቸው ተነገረ።  የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ጥቃቱን ያደረሱት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ የተባለው «ሸኔ» የተባለው ታጣቂ ቡድንና ሌሎች ኃይሎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/41d1r
Äthiopien | Wahlen | Oromia

ከእሁድ ጀምሮ ከ22 በላይ ሰዎች ተገድለዋል

በኦሮሚያ ክልል፤ ምስራቅ ወለጋ ዞን፤ ኪራሙ ወረዳ ሀሮ በተባለች ቀበሌ ካለፈው እሁድ  አንስቶ በታጣቂዎች የተገደሉ ሰዎች ከ22 በላይ መሆናቸው ተነገረ። ባለፈው እሁድ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት የ8 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገልጧል። በቀበሌው የነበሩ  የታጠቁ ሚሊሺያዎች እና ሌሎች ታጣቂዎች ደግሞ በወሰዱት የአጸፋ ርምጃ ከ14 በላይ በቀበሌው የሚኖሩ ለሎች የማኅረሰብ ክፍሎች ሕይወት ማለፉን የወረዳው ነዋሪዎች ዐስታውቀዋል።  የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ጥቃቱን ያደረሱት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ የተባለው «ሸኔ» የተባለው ታጣቂ ቡድንና ሌሎች ኃይሎች መሆናቸውን ተናግረዋል። ሁለቱ ቡድኖች በወረዳው በሚኖሩ የኦሮሞ እና የአማራ ማኅበረሰብን ለማጋጨት የሚሠሩ ናቸው ብለዋል። የአሦሳው ዘጋቢያችን ነጋሣ ደሳለን ዝርዝር ዘገባ አለው።
 
የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡን ማብራሪያ በምስራቅ ወለጋ ኪራሙ ወረዳ አሸባሪ ተብለው የተፈረጀው የሼነ ቡድን እና በስፋራው ይንቀሳቀሳሉ የተባሉ «ጽንፈኛ» የተባሉ ቡድኖች ባደረሱት ጥቃት 15 የሚደርሱ ሰዎች ሕይወት ማለፉን ገልጸዋል። ሁለቱ ቡድኖች በወረዳው በሚኖሩ የኦሮሞ እና አማራ ማህበረሰብን ለማጋጨት የሚሰሩ ናቸው ብለዋል። ከሌላ አካባቢ የመጡ ታጣቂዎች በስፍራው የሉም ያሉት ኃላፊው ጥቃት ያደረሱት በአካባቢው ይንሰቀሳቀሳሉ የተባሉ «ጽንፈኛ» ሀይሎች እና «ሸኔ» ናቸው ብለዋል። 
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ድባጢ ወረዳ ደግሞ ከመስከረም 21 አንስቶ በሁለት ቀበሌዎች ውስጥ በርካታ ሰዎች መታሰራቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል። ታሳሪ ቤተሰቦች ለዶይቸ ቬለ (DW)እንደተናገሩት በድባጢ ወረዳ ከተማውን ጨምሮ ጋለሳ እና በርበር በተባሉ ቀበሌዎች ውስጥ ሰዎች  መታሰራቸውን አመልክተዋል።

ባለፈው እሁድ በምስራቅ ወለጋ ኪራሙ ወረዳ በታጣቂዎች ደረሰ በተባለው ጥቃት ጉዳት ከደረሳባቸው ሰዎች በተጨማሪም በርካታ ነዋሪዎች ወደ አጎራባች ከተሞች መሸሻቸውን ከጥቃቱ ሸሽተው በዞኑ ግዳ አያና ወረዳ እንሚገኙ የነገሩን ነዋሪዎች ገልጸዋል። በወረዳው ከሳምንት በፊት በሥራ ላይ የነበሩ የጸጥታ ኃይሎች መውጣታቸውን ተከትሎ ሐሮ በተባለች ቀበሌ ውስጥ ታጣቂዎች ጥቃት ማድረሳቸውንም አመልክተዋል። 

Äthiopien | Straßenszene in Menge Woreda
ምስል Negassa Dessalgen/DW

ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ሌላው የኪራሙ ወረዳ ሐሮ ቀበሌ ነዋሪ በሰጡን አስተያየት በወረዳው በተለያዩ ጊዜያት ጥቃቶች እንደሚደርስባቸው ተናግረዋል። በወረዳው የሚኖሩ የታጣቁ ኃይሎች እና ከሌላ ቦታ መጡ በተባሉ ታጣቂዎች ባለፈው ሰኞ በደረሰው ጥቃት ደግሞ 14 ሰዎች ሕይወት ማለፉን አክለዋል። 
የነዋሪውን ቅሬታና በኪራሙ ደረሰ የተባለውን ጥቃት አስመልክቶ የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ በሰጡን ምላሽ፦ በሕዝብ ተወካዎች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ሼነ የተባለ ቡድን እና ሌሎች በአካባቢው ይንቀሳቀሳሉ የተባሉ ኃይሎች በምስራቅ ወለጋ ኪራሙ ወረዳ በንጹሐን ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን  ተናግረዋል። እነዚህ ኃይሎች በአካባቢው የሚኖሩ የአማራ እና ኦሮሞ ማኅበረሰብን ለማጋጨት የሚሠሩ ናቸው ያሉ ሲሆን የጸጥታ ኃይሎችም ርምጃ እንደሚወስዱባቸው አክለዋል። የኢትየጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን መስከረም 14 ቀን፤ 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫው «በምስራቅ ወለጋ ኪራሙ ወረዳ ላለው የጸጥታ ስጋት የፌደራል እና የክልሉ መንገስት የጸጥታ ኃይሎች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት  እና በነዋሪዎች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት የሚያደርሱ ኃይሎችን  ከሕግ ፍት ለማቅረብ ተጨባጭ ርምጃዎችን እንዲወስዱ» ሲል አሳስቧል።

በቤኒሻንል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የድባጢ ወረዳ ደግሞ በወረዳው ከተማ እና ጋለሳ በተባለ ቀበሌ ውስጥ ከ30 በላይ ሰዎች ባለፉት 10 ቀናት መታሰራቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል።   የታሰሩበት ምክንያት አለመታወቁንና ክስ እንዳልቀረበባቸውም ሌሎችም የታሳሪ በተሰቦቸ ለዶይቸ ቬለ አብራርተዋል።  የነዋሪዎቹን ቅሬታ አስመክልቶ ከዞኑ ኮማንድ ፖስት መረጃ ለማግኘት በስልክ ያደረግነው ጥረት ስልክ ባለማንሳታቸውን ሐሳባቸውን ማካተት አልተቻለም።
ነጋሣ ደሳለኝ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሰ