1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምህረት አዋጁ ሊጠናቀቅ የቀናት ዕድሜ ቀርተዉታል

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 9 2011

የኢትዮጵያ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በሚል ባለፈዉ ዓመት የደነገገዉ የምህረት አዋጅ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት ቀርተዉታል። የኢትዮጵያ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዛሬ እንዳስታወቀዉ አዋጁ የወጣዉ የዜጎችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ ታስቦ ስለሆነ፤ አዋጁ ቀነገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት

https://p.dw.com/p/3AKwb
Logo FDRE Federal Attorney Äthiopien

የምህረት አዋጁ ሊጠናቀቅ የቀናት ዕድሜ ቀርተዉታል

 መጠቀም የሚፈልጉና የሚመለከታቸዉ ሰዎች ማመልከቻ እንዲያቀርቡ የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ፅሕፈት ቤት አሳስቧል። 
የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ለተከታታይ 3 ዓመታት ተከስቶ በነበረዉ የአደባባይ ተቃዉሞ ምክንያት የተከሰተዉን አለመረጋጋት ለማስወገድ፣  ሰላም ለማስፈን፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታን ለማሳደግ በሚል ከሀምሌ 16/2010 ዓ.ም ጀምሮ ለስድስት ተከታታይ ወራት ተፈፃሚ የሚሆን የምህረት አዋጅ ማዉጣቱ ይታወቃል።በአዋጁ መሰረትም በወንጀል ድርጊት ተሳትፈዋል በሚል በእስር ላይ የቆዩ በርካታ ጋዜጠኞች፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና አመራሮች እንዲሁም  ግለሰቦች ተፈትተዋል።
በዚህ አዋጅ ነፍጥ አንስተዉ የነበሩ የመንግስት ተቃዋሚ ሀይሎች ሳይቀር ተጠቃሚ ሆነዋል።በተለያዩ ምክንያቶች የተከሰሱ ወይም እንጠየቃለን በሚል ስጋት ከሀገር ተሰደዉ የነበሩ ኢትዮጵዉያንና ትውልደ ኢትዮጲያዉያንም ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ  ሆኗል።ይህ ምህረት አዋጅ የተሰጠዉ ቀነ ገደብ ሊጠናቀቅ የቀናት ዕድሜ እንደቀሩት የኢትዮጵያ የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ አስታዉቋል።ያ ከመሆኑ በፊት ግን  ዜጎች በዚህ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በፅ/ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚንኬሽን ጉዳዮች ሀላፊ አቶ ዝናቡ ቱሉ ለDW ገልፀዋል።
ይህ አዋጅ ተፈጻሚ ሲሆን የነበረዉ ከጸደቀበት ቀን  ጀምሮ እስከ 6 ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ሲሆን ከግንቦት 30 ቀን 2010 በፊት የተፈጸሙ ወንጀሎችን ብቻ የሚመለከት መሆኑን ሃላፊዉ አብራርተዋል።
የምህረት አዋጁ ህገ-መንግስትና ሀገርን አደጋ ላይ መጣልን፣የፀረ-ሽብር ህጉን መተላለፍን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ድንጋጌዎች መጣስን ጨምሮ 12 የወንጀል ህግ አንቀፆችን የሚመለከት ሲሆን በአዋጁ የማይካተቱ ያሏቸዉ ወንጀሎችም አሉ።  «የዚህ ምህረት አዋጅ ተጠቃሚ የማይሆኑት በወንጀል ህግ አንቀፅ 652 ስር ተከሰዉ የሚገኙ በተለይም በወንጀል ድርጊታቸዉ የሰዉ ህይወት ያጠፋባቸዉ የዚህ ምህረት ተጠቃሚ የማይሆኑበት ሁኔታ ነዉ ያለዉ።» ብለዋል።
ነገር ግን የተጠቀሰዉን ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ ሰዎች መፈታታቸዉንና በአንፃሩ ደግሞ መፈታት ይገባቸዉ የነበሩ  ያልተፈቱ አሉ በማለት የሚተቹ አሉ።ይሁን እና አቶ ዝናቡ እንዲህ መሰሉ ትችት የምህረት አዋጁን ከይቅርታ ጋር ከመደባለቅ የሚፈጠር የግንዛቤ ችግር መሆኑን ጠቁመዉ የምህረት አዋጅ 1096/2010 በሚፈቅደዉ መሰረት የሚመለከታቸዉ ሰዎች ሁሉም መፈታታቸዉን ተናግረዋል።
በዚህ የምህረት አዋጅ እስካሁን የክልሎችን እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊት አባላትን ሳይጨምር በፌደራል ደረጃ ክስ ተመስርቶ በሂደት የነበሩ ፣ዉሳኔ የተላፈባቸዉና ማረሚያ ቤት የነበሩ ከ581 በላይ ሰዎች በአካልና በድረ-ገፅ የይቅርታ ሰርተፌኬት ማግኜታቸዉን አቶ ዝናቡ አስረድተዋል።  
አዋጁ የዚጎችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ የወጣ መሆኑን የሚነገሩት ሃላፊዉ ፤ በዚህ መሰረት የሚመለከታቸዉ ሰዎች በአካል ወይም ባሉበት ሆነዉ በፅ/ቤቱ ድህረ ገፅ በተቀመጠዉ አድራሻ መረጃ በመሙላት ቀነ ገደቡ ከመድረሱ በፊት እድሉን እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል።

Äthiopien Kaliti Gefängnis
ምስል DW/Y. Gebregziabher
Äthiopien Kaliti Gefängnis
ምስል Befekadu Hailu

ፀሐይ ጫኔ

ሂሩት መለሰ