1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማንዶሊኑ ንጉስ ጋሽ አየለ ማሞ 

ሐሙስ፣ ግንቦት 5 2013

ሙዚቀኛ ግሩም መዝሙር እንደሚለዉ ጋሽ አየለ ማሞ በሞት ቢለየንም ሥራዎቹን በማስቀጠል ህያዉ እናደርገዋለን። አየለ ማሞ ከ1949 ዓ.ም ጀምሮ ለ64 ዓመታት በሙዚቃ ህይወት በጥበብ ስራዎቹ ሕዝብን አስደስቶ እዉቀቱንም አካፍሎ አስተምሮ ትዉልድን ተክቶ ሕያዉ የሆኑትን ስራዎች ትቶ መጋቢት 29፤ 2013ዓ.ም ላይመለስ አሸለበ።  

https://p.dw.com/p/3tLxg
Äthiopien | Jazz Band | Addis Acoustic Project
ምስል Girum Mezmur

በኢትዮጵያ ብቸኛዉ የማንዶሊን ንጉስ የሆነበት ምስጢሩ ምንድን ነዉ?

አየለ ማንዶሊ የማንዶሊኑ ንጉስ፤ አየለ ማንዶሊን ፤ አየለ ማሞ ከሁሉ ከሁሉ አብዛኛዉ አድናቂዎቻቸዉ ጋሽ አየለ ማሞ ሲሉ ይጠሩታል። የዜማ የግጥም ደራሲና ድምፃዊዉ ጋሽ አየለ ማሞ የዛሬ ዘጠኝ ዓመት እዚህ ራድዮ ጣብያችን ዶቼ ቬለ በሚገኝበት በጀርመንዋ ቦን ከተማ በመጣ ጊዜ ሰፋ ያለ  ቃለ ምልልስ ሰጥቶናል በዚህ ዝግጅት ዉስጥ በድምፅ ዘገባዉ ተካቶአል። የማንዶሊኑ ንጉስ ጋሽ አየለ ማሞ አዲስ አኩስቲክ ከተባለዉ እና ይሰራበት ከነበረዉ የሙዚቃ ቡድን አባላት ጋር በተለይም በጀርመን ኮለኝና ፍራንክፈርት ከተማ «ትዉስታ» የተባለዉን በባህላዊ እና በዘመናዊ የሙዚቃ መሳርያ የተቀናበረ የጃዝ ሙዚቃ ድግሱን ሲያሳይ ኢትዮጵያዉያኑን ጥንት በጠዋቱ ሙዚቃ አሳፍሮ፤ ኢትዮጵያን በአካል ተገኝተዉ ለሚያዉቁ ደግሞ በሃሳብ ወደ ኢትዮጵያ አስጉዞ በዉዝዋዜ አስቦርቆ እና፤ በትዝታ አንጉዶ፤ በጀርመናዉያኑ ዘንድ «እዉነት ኢትዮጵያዉያን የጃዝ ሙዚቃን እንዲህ ዉብ አድርገዉ ይጫወታሉ? የሚል ጥያቄ  ማስነሳቱን የባህል ዝግጅት ክፍላችን የዓይን እማኝ ነበር። ሙዚቃ የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ለ 10 ቀናት ግድም በጀርመን የጃዝ ድግስን ለማሳየት አዲስ አኩስቲክ ከሚባለዉ የጃዝ ሙዚቃ ቡድን ጋር የመጣዉ ጋሽ አየለ ማሞ ፤ማንዶሊንን ከመጫወት ባሻገር የጃዝ ቡድኑን አንዳንዴም በዘፈን ማለትም በድምፅ ከመደገፍ ባለፍ በመድረኩ ላይ ያሳይ በነበረዉ ዉዝዋዜ እና ፈገግታ የሚስተካከለዉ አልነበረም። ጋሽ አየለ ማሞ እድሜዉ በቁጥር ከሙዚቃ ባልደረቦቹ ቢበልጥም ከወጣት ሙዚቀኛ ባልደረቦቹ ጋር ሲሰራ በፍጥነት፤ በንፁህ ገፅታ እና የስራ ወኔ  እንዲሁም  በአዲስ የሙዚቃ ፈጠራ የሚስተካከለዉ እንዳልነበር ባልደረቦቹ ራሳቸዉ ይመሰክራሉ። ከወጣት ሙዚቀኞች ራሱን አዛምዶ እና አስተካክሎ እንደሚሰራም ነግሮናል፤ የዛሬ ዘጠኝ ዓመት።  አየለ ማንዶሊን ከአዲስ አኩስቲክ ጃዝ ባንድ ጋር ወደ ጀርመን ሁለት ጊዜ መጥቶአል ። ደስተኛም እንደነበር ገልፆልን ነበር። በጋሽ አየለ ማሞ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ማዘኑን የነገረን የአዲስ አኩስቲክ የጃዝ ሙዚቃ ቡድን መስራች እና የሙዚቃ መሳርያ አጨዋወት አስተማሪዉ ግሩም መዝሙር ፤ ጋሽ አየለ ማሞን የማዉቀዉ ይላል የ ዛሬ 14 ዓመት የጋሽ አየለ ማሞ የሞያ ባልደረቦች ለጋሽ አየለ  ለ 50 ኛ ዓመት የሙዚቃ ስራ  እዉቅና ለመስጠት ያዘጋጁት መረሃ-ግብር  በቴሌቭዥን ሲሰራጭ ካየ በኋላ እንደነበር ያስታዉሳል። ግሩም መዝሙር ከአንጋፋውን ድምፃዊ፣ የዜማ እና የግጥም ደራሲ ብሎም ከማንዶሊኑ ንጉስ ከጋሽ አየለ ማሞ  ጋር ላለፉት 14 ዓመታት የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ዳበረ በተባለበት በ 50ቹ እና በ60ዎቹ ዓመታት የወጡ ሙዚቃዎችን በጃዝ ቅላፄ በማቀናበር በአዲስ አኩስቲክ የሙዚቃ ቡድን ዉስጥ አንድ ላይ ተጫዉተዋል። ይህንም ሙዚቃቸዉን ለተለያዩ የዓለም ሃገራት አሳይተዋል።  የማንዶሊኑ ንጉስ ጋሽ አየለ ማሞ ከማንዶሊን ውጪ ቤዝ ጊታርና ሊድ ጊታርም ይጫወታል።  ከ 50 ዓመታት በላይ  ግጥምና  ዜማን በመድረስ እና ለሙዚቀኞች በመስጠት ተወዳጅ ዘፈን እና ለሙዚቀኞችም እዉቅናን አስገኝቶአል። በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃም ከመጀመርያዎቹ ተርታ እንደሚሰለፍ ይነገርለታል።  አናጋፋዉ ሙዚቀኛ አየለ  ማሞ ግጥምና  ዜማን ደርሶ  ከሰጠው አንጋፋና ወጣት ድምፃውያን መካከል  ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ፣ መሐሙድ አህመድ ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ኩኩ ሰብስቤ ፣ኤፍሬም ታምሩ፣ ሀመልማል አባተ፣ ብፅአት ስዩም፣ ወረታው ውበት፣ አስቴር ከበደ፣ ህብስት ጥሩነህ፣ ምንያህል ጥላሁን ገሠሠ፣ እና ሌሎችም እንዳሉ የጋሽ አየለ ማሞ ታሪክ ያሳያል።  ካፈራቻቸው ወጣት አርቲስቶች  መካከል ደግሞ ተወዳጆቹ ድምፃዉያን ጎሳዬ ተስፋዬ ፣ አብነት አጎናፍር፣ የሚጠቀሱ ናቸዉ። አየለ ለአንጋፋ ድምጻውያን በርካታ ዜማዎችን ሰርቶ ከመስጠት ባለፈ ወይ ካሊፕሶ በሚለው ሙዚቃ በህዝብ ዘንድ ይበልጥ እውቅናን አግኝቷል፡፡ ሙዚቀኛ ግሩም መዝሙር እንደሚለዉ ጋሽ አየለ ማሞ በሞት ቢለየንም ሥራዎቹን በማስቀጠል ህያዉ እናደርገዋለን። አናጋፋዉ ሙዚቀኛ ገጣሚና ዜማ ደራሲ አየለ ማሞ ከ1949 ዓ.ም ጀምሮ ለ64 ዓመታት በሙዚቃ ህይወት በጥበብ ስራዎቹ ሕዝብን አስደስቶ እዉቀቱንም አካፍሎ አስተምሮ ትዉልድን ተክቶ ሕያዉ የሆኑትን ስራዎች ትቶ መጋቢት 29፤ 2013ዓ.ም ላይመለስ አሸለበ። የቀብር ሥነ ሥርዓቱ መጋቢት 30 ቀን 2013 ዓ.ም  በአዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ተፈፅሞአል። 

Äthiopien | Jazz Band | Addis Acoustic Project
ምስል Girum Mezmur
Äthiopien | Addis Acoustic Project Jazz Band
ምስል Girum Mezmur
Äthiopien | Jazz Band | Addis Acoustic Project
ምስል Girum Mezmur

 

አዜብ ታደሰ  

ኂሩት መለሰ