1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ሰኔ 2 2015

በሸገር ከተማ የመስጂዶች ፈረሳ የፈጠረውን ቀውስ ለመፍታት የተደረገው ውይይት፤ በአሰቃቂ ሁኔታ የሚገደሉ ሰዎች የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስልና ከወደ ዚምባብዌ በፎቶ ብቅ ያሉት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በሣምንቱ መነጋገሪያ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል ናቸው። በዚህ ሣምንት በሞት የተለዩት ሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ ጀግንነት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተወስቷል።

https://p.dw.com/p/4SOgp
Äthiopien | Beisetzung Ali Berke
ምስል Seyoum Getu/DW

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ላለፉት ሁለት ሣምንታት ተቃውሞ የተሰማበት የታላቁ አንዋር መስጂድ የጁምዓ ጸሎት ዛሬ በሰላም ተጠናቋል። ሰባህ ረዲ ጁምዓ "አንዋር መስጂድ በሰላም ተሰግዷል" ሲሉ በፌስቡክ ጽፈዋል። ፋኖስ ሐሚዶ ፎቶ አስደግፈው "ታላቁ አንዋር መስጂድ ወደ ቀድሞ ሰላሙ ተመልሷል" የሚል አስተያየት አስፍረዋል። እነዚህ አስተያየቶች ባለፉት ሁለት የጁምዓ ጸሎቶች በአንዋር መስጂድ የተከሰተው ባለመደገሙ ለእስልምና እምነት ተከታዮች እፎይታ መሆኑን የሚጠቁሙ ናቸው።

በአንዋር መስጂድ ባለፈው ሣምንት ማለትም አርብ ግንቦት 25 ቀን 2015 ከጁምዓ ጸሎት በኋላ በሸገር ከተማ አስተዳደር ውስጥ የሚገኙ መስጂዶች መፍረሳቸውን የሚያወግዝ ተቃውሞ ተሰምቶ ነበር። በታላቁ አንዋር መስጂድ ከተሰማው ተቃውሞ በኋላ ለጁምዓ ጸሎት የወጡ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ሰዎች ለእስር ተዳርገዋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራሮች እና ከኃይማኖት አባቶች ጋር ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ ለጉዳዩ መፍትሔ ለማበጀት መስማማታቸው ተገልጿል። ከውይይቱ በኋላ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የፕሬዝደንት አማካሪ የሆኑት ኡስታዝ አሕመዲን ጀበል በፌስቡክ ባሰፈሩት ጽሁፍ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት በሸገር ከተማ ውስጥ "አስፈላጊውን የቤተእምነት መሥሪያ መሬቶችን በፕላኑ መሠረት ለምዕመኑ እንደሚሰጥ" መናገራቸውን ገልጸዋል።  

Der äthiopische Rat für islamische Angelegenheiten Addis Ababa
በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የፕሬዝደንት አማካሪ የሆኑት ኡስታዝ አሕመዲን ጀበል በፌስቡክ ባሰፈሩት ጽሁፍ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት በሸገር ከተማ ውስጥ "አስፈላጊውን የቤተእምነት መሥሪያ መሬቶችን በፕላኑ መሠረት ለምዕመኑ እንደሚሰጥ" መናገራቸውን ገልጸዋል።ምስል Seyoum Getu Kori Addis Ababa

ሌላ ፈረሳ….አዲስ አበባ ድሆችን እየገፋች ነው?

ከፈረሳ ጋር በተያያዘ ገጣሚ እና ጸሐፊ በዕውቀቱ ሥዩም በተረጋገጠ የፌስቡክ ገጹ ያሰፈረው አጭር ትዝብት ሌላ መነጋገሪያ የነበረ ጉዳይ ነው። በዕውቀቱ ግንቦት 28 ቀን 2015 የጻፈውን ትዝብት "አዲስአበባ ውስጥ እንደ ቦሌ መድሀኒያለም እሚገርመኝ ሰፈር የለም" ሲል ይጀምራል። "ከመድሀኒያለም ፊት ለፊት አስፓልቱን ተሻግሮ ትልልቅ ህንጻዎች ይበቅላሉ፤ ምርጥ ካፌዎች ሬስቶራንቶች እና በርገር ቤቶች ያብረቀርቃሉ። አስፓልቱ ሁሌም በእግረኞች እንደተሞላ ነው" ይላል በዕውቀቱ።  "ከመድሀኒያለም ጀርባ ደግሞ ሌላ እዩኝ እዩኝ የማይል አለም አለ። በቆርቆሮ እና በሰማያዊ ሸራ የተዋቀሩ የንግድ ቤቶች ተደርድረዋል። ባብዛኛው ምግብ ቤቶች ናቸው። "የኛ ሽሮ፥ እድላዊት ምግብ ቤት" ወዘተ የሚል መጠርያ አላቸው። እንደ “ቃተኛ” ያሉ የቅንጦት ምግብ ቤቶች ውስጥ የመብላት አቅም የሌላቸው የመንግስት ሰራተኞች እዚህ በተመጣጣኝ ዋጋ ደህና ምግብ ይሸምታሉ። ለመጨረሻዎቹ ድሆች “ርጥብ” የተባለ ምግብ ይቀርባል! ርጥብ የቅቅል ድንች ክትፎ ነው፤ በዳጣ ሰላሳ ብር ሲሆን እንቁላል ሲታከልበት ስድሳ ብር ያስከፍላል፤ ሁሌም ከምግብ ቤቶች ፊት ለፊት ሞተርሳይክሎች ተደርድረው ቆመው ይታያሉ፤ እቃ ለማመላለስ ላይ ታች ሲሉ የሚውሉ ልጆች ባብዛኛው የዚህ ሰፈር ታዳሚ ናቸው"ይላል በዕውቀቱ ያሰፈረው ትዝብት።

"በዚያ ሳልፍ ቤቶች እየፈረሱ ነው፤ ተወዳዳሪ የሌለው ሀዘን ወረረኝ" የሚለው በዕውቀቱ  "በቅርቡ እየተደረገ ያለው የዶዘር ዘመቻ፥ የትምና መቼም ታይቶ የሚታወቅ አይደለም፤ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ በቻይና የዙረት እድል የገጠመን ሰዎች እንደምንመሰክረው ጉሊት አለምአቀፍ ነው። በየትኛውም ትልልቅ ከተማ ምግብ ሰርተው መንገድ ላይ የሚሸጡ ሰዎች ይኖራሉ፤ መንግስት መብታቸውን ያከብርላቸዋል" በማለት በአዲስ አበባ የተመለከተውን ከተቀረው ዓለም ልምድ እየጠቀሰ ያመዛዝናል። “ሰው በላው ካፒያሊዝም” የሚባለው ስርአት በሰፈነባቸው ሀገሮች ሳይቀር ድሆች በዚህ መጠን አይገፈተሩም፤ ቤቶች መስጊዶች ያለ ነዋሪው ፈቃድ አይፈርሱም፤ የግድ ሆኖ ሲፈርሱ እንኳ ለባለቤቶች ካሳ እና ምትክ ቦታ ይሰጣቸዋል" ብሏል።

"አዲስ አበባ እኔ ሳውቃት፥ ትልቁን እና ትንሹን አቻችላ የምታሳድር ሆደ ሰፊ ከተማ ነበረች" የሚለው ጸሐፊው "አሁን ይሄ እየቀረ ነው" የሚል ሥጋት ተጭኖታል። "የተወሰኑ ሰዎች መሬት ሸጠው ሌክሰስ እንዲነዱ በላባቸው የሚተዳደሩ አያሌ ድሆች መድረሻ አልባ መሆን አለባቸው? እየተስተዋለ እንጂ ጎበዝ!" የሚለው የበዕውቀቱ ሥዩም ትዝብት በፌስቡክ ከ13 ሺሕ በላይ ሰዎች ወደውታል፤ ከ1500 በላይ ሰዎች ደግሞ በግል ገጻቸው አጋርተውታል።

አዲስ አበባ
አዲስ አበባምስል DW

ለትዝብቱ ከተጻፉ ከ130 በላይ አስተያየቶች መካከል በዕውቀቱን የተቹት የታሪኩ አባዳማ ነው። ታሪኩ አባዳማ "በውቀቱ ስዩም እንደሚለው የላስቲክ እና ሸራ ንግድ ቦታዎች ባደጉ አገሮች ጭምር በይፋ እንደሚሰራበት እና ህጋዊ ድጋፍ ይሰጠዋል ብሏል። የትኛው ያደገ አገር ወይንም ከተማ እንደዚያ እንደሚያደርግ አልጠቀሰም -- ብዙ አገሮች ተዘዋውሬ እንዳየሁት በማለት ነው ጉዳዩን የሚያወሳው" ይላሉ።

ታሪኩ አባዳማ "በመሠረቱ በምዕራቡ ዓለም ከተሞች የመንግሥት ፈቃድ ሳይኖረው እና ለመንግሥት ታክስ ሳይከፍል የሚደረግ ምንም ዓይነት ንግድ የለም። ንግድ ቤት ለመክፈት ስታስብ ደግሞ ማመልከቻ ታቀርባለህ፤ በማመልከቻህ መሠረት የጠየከው የንግድ ዓይነት በጠየከው ክፍለ ከተማ እና ቦታ ላይ ይፈቀዳል ወይ የሚለው ጥያቄ በቅድሚያ ይቀርባል።  ዞኒንግ ይሉታል። እዚህ ሥፍራ የዚህ ዓይነቱ ንግድ ሊከናወን ይችላል ወይ የሚለው ጥያቄ አዎንታዊ መልስ ካገኘ ደግሞ ሶስት ወይንም አራት አይነት ባለሙያዎች ወደ ሥፍራው ይመጣሉ። የንግድ ቦታው ወሀ አለው? ሽንት ቤት አለው? በእሳት አደጋ ጊዜ ማምለጫ አመቺ ኮሪደር ተመቻችቷል? ይህን እና ያንን ያሟላል የሚለው በባለሙያው ፀድቆ ተፈርሞ clearance ይለፍ ወረቀትህን ይዘህ ስትሄድ ነው ፈቃድ የምታገኘው። እርግጥ ነው ለጊዜያዊ ፌስቲቫል ወይንም ዓመታዊ ዝግጅት ተብሎ ሲበዛ ቢውል ለሳምንት የሚቆዩ የድንኳን ንግድ ቤቶች ይፈቀዳሉ - እሱም ቢሆን ከፍ ብዬ የጠቃቀስኳቸው መሠረታዊ አገልግሎቶች መመቻቸታቸው /በማዘጋጃ ቤቱ ወይንም በዝግጅቱ ባለቤት/ በባለሙያ መረጋገጥ አለበት" ሲሉ የራሳቸውን ትዝብት ያካፍላሉ።

"ከሶስት አሰርት ዓመታት በኋላ አዲስ አበባ ስሄድ ያሳዘነኝ እና ያስደነገጠኝ ነገር ቢኖር በዋና ዋና ጎዳናዎች ፣ በዩንቨርሲቲ አጥር ግንቦች ሥር እና በመኖሪያ አካባቢዎች ሁሉ ሳይቀር በላስቲክ እና በሸራ ተቀልሰው የሚካሄደው ንግድ ነበር። የእግረኛ መተላለፊያ መንገዶች በሙሉ በቅራቅንቦ ሸቀጥ ነጋዴዎች ተጨናንቀው ማየት እጅግ ያሳዝናል። በውቀቱ ስዩም የዚያን አይነቱን ቅጥ ያጣ በማናቸውም የከተማ ህይወት መለኪያ ተቀባይነት የሌለውን ሁኔታ መፈረስ እንደ ጭካኔ ድርጊት አድርጎ ለህዝብ ሲያቀርብ ማየት ደግሞ ህብረተሰባችን የት ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው ብለን እንድንተክዝ ያስገድደናል" ሲሉ ታሪኩ አባዳማ መልሰዋል።

ሌላ የአሰቃቂ ግድያ ቪዲዮሌላ ሐዘን

በሣምንቱ በማኅበራዊ ድረ ገፆች ሲዘዋወር የሰነበተ አንድ ደቂቃ ከአስራ ስድስት ሰከንዶች ገደማ የሚረዝም ተንቀሳቃሽ ምስል ለበርካታ ሰዎች ሐዘን የፈጠረ ሆኗል። ይኸ  ቪዲዮ ሁለት እጃቸውን የፊጥኝ የታሰሩ ሰዎች ወታደራዊ መለዮ በለበሱ ታጣቂዎች ሲገደሉ የሚያሳይ ነው። ሟቾች እነማን ናቸው? የየትኛው ብሔር አባላት ናቸው? ገዳዮችስ? የሚሉ ጥያቄዎች የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎችን በጎራ በጎራ ሲያወዛግብ ቆይቷል። አንዳንዶች አረጋግጠናል ያሉትን መረጃ እያቀረቡ ሲከሱም ታይቷል።

መላኩ ተስፋ "ሟቾቹ ማንም ይሁኑ ምንም አይነት ወንጀል ይስሩ እንደዚህ አይነት አሰቃቂ ግድያ ሊፈፀምባቸዉ አይገባም" ሲሉ ጽፈዋል። ቡኒ ኦሪሳ "እነዚህን አሰቃቂ የግድያ ቪድዮ ምስሎች ቀስ እያለ የሚለቅልን አካል ዓላማው ምንድርነው? ስቃይ እና ሞትን ማለማመድ? ህዝብን ከህዝብ ባላንጣ አድርጎ መሳል? ፍርሃት እና ሽብርን ማንገስ ወይንስ የጂል ነፍሰ ገዳዮች ማንአለብኝነት? እየገደሉ ቪዲዮ መቅረፅ ምን የሚሉት ጉድ ነው? ኧረ በፈጠራችሁ! ቢያንስ በግልፅ የሚታዩትን በአስተማሪ ሁኔታ በህግ በመቅጣት መንግስታዊ ኃላፊነታችሁን ተወጡ" የሚል አስተያየት ጽፈዋል። ማሙሼ ኃይሌ "መተሳሰብ ቀረ በሲኖ ትራክ መጨፍለቅ፤ በጥይት ጭንቅላት ማፍረስ፤ ሰው መሆናችን እኮ ቀረ። ማንም ያድርገው የማንም ብሔር ይሁን እጅ የሰጠን ሰው በዚህ መልኩም መግደል ኢ-ሰብዊ ነው" ብለዋል። አሕመድ አሚን "ይሄ አውሬነት መቸ ይቆማል?" በማለት ጠይቀዋል።

የመንግሥቱ ኃይለማርያም ፎቶ እና የሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ ሥንብት

የቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ መንግሥቱ ኃይለማርያም በዚምባብዌ ዋና ከተማ ሐራሬ ከደቡብ ሱዳን ባለሥልጣናት ጋር የተነሷቸው ፎቶግራፎች በማኅበራዊ ድረ ገጾች ሲዘዋወሩ ሰንብተዋል።  በፎቶዎቹ መንግሥቱ ከደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት አማካሪ እና ሌሎች ባለሥልጣናት ጋር ይታያሉ። የደቡብ ሱዳን ባለሥልጣናት የቀድሞውን የኢትዮጵያ መሪ "መጎብኘት መቀጠላቸው ጥሩ" እንደሆነ የገለጹት ማሉዋል ቦል ኪር በትዊተር ባሰፈሩት አጭር አስተያየት "የደቡብ ሱዳን ሕዝብ በኻርቱም አገዛዝ ይደርስበት በነበረው መገለል እና ጭቆና ላይ ያደረገውን ትግል የደገፉ የመጀመሪያው የአፍሪቃ መሪ ናቸው" ብለዋል።

ኡመር ኢድሪስ "ጓድ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ክፉም ደግም ሰርተዋል። አሁን ግን አልፏል። ላገራቸው አፈር እንዲያበቃቸው ምኞቴ ነው" የሚል አስተያየት ጽፈዋል። ሙሉነህ ዘነበ ደግሞ የጓድ መንግሥቱን የቀድሞ እና የዘንድሮ ፎቶግራፎች በፌስቡክ ገጻቸው ጎን ለጎን አስቀምጠው "ያለፈበትንና ያሳለፈውን እሱ የሚያውቀው ሆኖ ኢትዮጵያ አንደበት በኖራት ምን ባለች ይሆን? ኢትዮጵያዊያን መቼም አንድ አይነት ነገር መናገር የሚሆንልን ስላልመሰለኝ ነው" በማለት ሐሳባቸውን አስፍረዋል።

አሕመድ ሐቢብ "ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ወደ ሀገራቸው ቢመጡ በሚል ዙሪያ ምን አስተያየት አላችሁ?" የሚል ጥያቄ በፌስቡክ አቅርበው ነበር። ኢድሪስ አል ቃፋሪ "መንግሥቱ ለብዙ ሺ ምሁራን ሞት፤ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ወጣቶች እልቂት እና ስደት መጠይቅ የሚገባቸው ወንጀለኛ ሰው ናቸው። ለፈፀሙት ወንጀል ከመሞታቸው በፊት እጅ ቢሰጡ ለታሪካቸው መልካም ነበር" ሲሉ መልሰዋል። ኤፍሬም ተካልኝ "ሕጉ በዘር ማጥፋት የተከሰሰን ሰው በይቅርታ ወይም በምህረት መልቀቅ ስለማይቻል እንጂ እኔ በበኩሌ ቢመጣ ደስ ይለኝ ነበር" የሚል አቋም አላቸው። ኃይሌ ደረሰ "ለፈፅመው ጭፍጨፋ ለስቅላት ነው የሚመጣው?" ብለው ሲጠይቁ ግርማ ገብረሚካኤል "ሰላሙን ለማጣት ነው የሚመጣው? ባለበት ፈጣሪ ያኑረው" ብለዋል።

ጓድ መንግስቱ ሥልጣን ላይ በነበሩበት ዘመን ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ስትዋጋ በውትድርና የተፋለሙት ሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ በዚህ ሣምንት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው ሥርዓተ ቀብራቸው ግንቦት 30 ቀን 2015 ተፈጽሟል። ወሰንሰገድ ገብረኪዳን "ሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ ጀግና ነው፤ የጀግኖች ጀግና። የወንዶች ቁና። ለዚህ የምስራቅ ጦር ግንባር (በ1969) የአቡሸሪፍ ሜዳ ምስክር ነው። በእጅ ቦንብ ታንክ የደመሰሰ ልበ ሙሉ ጀግና ነው። ይህ ጀግንነቱ በአለቆቹ ተመስክሮለት የሕብረተሰባዊት ኢትዮጵያ አንደኛ ደረጃ ሊሻን ተሸላሚ ለመሆን የበቃ ነው" በማለት ጽፏል።

ደቻሳ አንጌቻ በግንቦት 1983 መንግሥት ሲለወጥ በስደት ከነበሩበት ኬንያ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት ሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ ለአስራ አንድ ዓመታት ታስረው እንደነበር ጽፏል። "ከግፍ እስሩ ሲወጣ ትዳሩና ቤተሰቡ ተበትኖ ጠበቀው፤ ጡረታ አልተከበረለትም፤ የአገልግሎት ክፍያ አልተሰጠውም። ህይወት ሲጨልምበት የጥይት ፍንጣሪ በተሸከመ ገላው ሸክም በመሸከም ፣ የቀን ስራ በመስራት ፣ ጎዳና እያደረ ኑሮውን መግፋት ተያያዘው" ሲል ሻለቃ ባሻ አሊ ፈታኝ ሕይወቱ እንዳሳለፉ ጽፏል።

ደቻሳ እንደጻፈው ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሚመሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሲቃረብ የመኖሪያ ቤት ሊሰጣቸው ቃል ገብቶ የነበረ ቢሆንም ተግባራዊ አልሆነም። ዳዊት ግርማ " ነፍስ ይማር ምስኪን ሀገሬን ባለ ይሄ ሁሉ መከራ" ሲሉ ቁጭታቸውን ገልጸዋል።  "ለጀግና ይሄ አይገባውም ነበር" የሚል አቋም ያላቸው ዘላለም መሉ "በሰራው ጀብዱ ታሪክ ደጋግሞ ያወሳዋል። የአባቶቹን ገድል የማይዘነጋ ትውልድ ይዘክረዋል። የታንክ ማራኪውን ጀግና ነፍስ ይማርልን" ብለዋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ