1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ሚያዝያ 15 2013

አዎ መንግስት ምክንያቱን በግልፅ ለህዝብ ቀርቦ እንደመሪነቱ ማስረዳት አለበት ሲሉ ፋንታሁን መንጌ በሃሳቡ እንደሚስማሙ በፌስቡክ ባሰፈሩት አስተያየት ገልጸዋል። ማሬው ቦረና ደግሞ ምክንያቱ«የመንግሥት አመራሮች ችግር ነው በማለት ሃሳባቸውን አካፍለዋል።

https://p.dw.com/p/3sV6J
Äthiopien Premierminister Abiy Ahmed Parlament
ምስል Yohannes Gebireegziabher/DW

የሣምንቱ ዐበይት ጉዳዮች ተዳሰውበታል

በዚህ ሳምንት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከክልል ፕሬዝዳንቶችና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አመራሮች ጋር በምርጫ ዝግጅትና ባጋጠሙ ችግሮች ላይ በባካሄዱት ውይይት ላይ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ቡርቱካን ሚዴቅሳ ሁሉም እንዲመርጥ የምዝገባው ቀን እንዲራዘም መደረጉ እንደማይቀር ተናግረዋል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐቢይም ዜጎች ሕገ-መንግስታዊ መብታቸውን ለመጠቀም በቀሬው ጊዜ ውስጥ ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል።በዚህ ጥሪ ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ልዩ ልዩ አስተያየቶች ተንሸራሽረዋል። አበራ በቀለ ከአዲስ አበባ

«የምርጫ ጣቢያ ፍለጋ ተንገላታን ፤ግልጽ የሆነ ቦታ ሕብረተሰቡ በቀላሉ ሊያገኘው የሚችልበት ቦታ በለመሆኑ በስንት መከራ ስንደርስ ካርድ አልቋል ይባላል ካርድ ለማግኝት ተንከራተትን አያት አካባቢ»

በማለት ያጋጠማቸውን ችግር በፌስቡክ አጋርተዋል።ፍቃዱ አጥላውም በፌስቡክ ባሰፈሩት መልዕክት ርሳቸው በሚኖሩበት በአዲስ አበባ ለሚኩራ ክፍለ ከተማ በሚገኝ ወረዳ ውስጥ ተመሳሳይ ችግር እንዳለ ጠቁመው፤ጥርጣሪያቸውንም ገልጸዋል።«15% ነዋሪ ሳይመዘገብ ካርድ ጨርሰናል/ኮታ ሞልተናል በማለት ህዝቡ ከምዝገባ እና ከምርጫ ውጭ እንዲሆን የሚሰራ ይመስላል፤ ካሉ በኋላ የሚመለከታችው አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ቢሰጡ መልካም ነው ሲሉ የበኩላቸውን የመፍትሄ ሃሳብ አስተላልፈዋል።

«ይድረስ ለተከበራችሁ ተፎካካሪ ፓርቲዎች» ሲሉ መልዕክታቸው የሚጀምሩት ወርቅነሽ ተካ  «ስልጣንም ህይወትም አገር ስትኖር ነው እና ቅድሚያ ስለሀገር ብታስቡ መንግስትንም በሀሳብ ብትመክሩ መልካም ይመስለኝል ኢትዮጵያ ለዝልአልም ትኑርልን በማለት ሃሳባቸውን ደምድመዋል።

«ማንን እንምረጥ እናንተን ከማዳመጥ በላይ እየሆነ ያለው እጅጉን አስጨንቆናል።እስቲ የሀገሪቷን ሁኔታ ተመልከቱ ሲሉ ስጋታቸውን የገለጹት ደግሞ ህይወት ሲሳይ ናቸው።

ሶል ሶል በሚል ስም የሰፈረ አጭር አስተያየት

«ህዝብ እያለቀ ምን አይነት ምርጫ ነው የሚካሄደው ማንስ ነው መራጩ ትገርማላቹህ»ይላል

ቀልድና ቁም ነገር በሚል የፌስቡክ ስም የቀረበ አስተያየት «ግራ የተጋባ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው።ማንን ነው የምንመርጠው?ብዙ ባለጭንብል ነው ያለው።እንደ ፈጣን ሎተሪ ፋቅ ፋቅ ሲደረግ ሌላ የሚሆን ይላል።

«ከምርጫ በፊት ሰላም ይቅደም ጎበዝ» ይላል እጥር ምጥን ያለው የዮናስ ገብረ ስላሴ አስተያየት

አቡሽ ግዛቸውም ተመሳሳይ አስተያየት ነው የሰጡት« በምርጫ አምናለሁ ሆኖም የመንግሥት ቅድሚያ ሃላፊነት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማስከበር ነው ሲሉ ።

አብዮት እሸቱ 

ለፀጥታ ትኩረት ይሰጥ።ህዝቡን በንቃት እንዲሳተፍ ፣ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ ወይም የሚቀሰቅሱ ፓርቲዎች በሀገርቱ ሁሉን ገዥ የሆነ ሕግ መኖሩን እንዲያውቁ ቢደረግ በማለት ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን መደረግ ያለበትን ጠቁመዋል።

"አሁን የገባንበት ችግር ከጥቂት ልሂቃን ተሻግሮ፣ ያልነካው የማህበረሰብ ክፍልና ተቋም የለም።» በማለት መልዕክታቸውን የሚጀምሩት ያዕቆብ ተሻገር «አብሮ ያስተሳሰረን ክር በብሄር ፖለቲካ ምክንያት ብጥስጥሱ እየወጣ ነው። በዚያ ላይ ምሁራን፣ መገናኛ ብዙሃን እና በውጭ የሚኖሩ ዜጎቻችን ሳይቀሩ ጥሩ የሰሩ እየመሰላቸው በእሳቱ ላይ ቤንዚን ያርከፈክፋሉ። በኔ እምነት ወቅቱ ከስሜት ፖለቲካ ሁላችንም ወጥተን ለሀገራችን የመፍትሄ ሀሳቦችን በስክነት ልንፈልግ ግድ የሚልበት ጊዜ ነው። ስክነት ነው የሚያስፈልገን ሲሉ ሃሳባቸውን ደምድመዋል።

«ከምንም ነገር በላይ ለዜጎች ደህንነትና ህልውና ቅድሚያ ተሰቶ መስራት የመንግስት ውዴታው ሳይሆን ግዴታው መሆን አለበት ። ዜጎች በመንግስታቸው ላይ እምነት የሚኖራቸው በህይወታቸው እና በንብረታቸው ላይ በሚሰጣቸው ህልውና ብቻ ነው ያንን ማረግ ካቃተው ድጋፋቸው ወደ ጥርጣሬ ተስፋቸው ወደ ተስፉ ቢስነት ፍቅራቸው ወደ ጥላቻ ይቀየራል ይህ ደግሞ ዋጋ ያስከፍላል ሀገርን ። ቢያንስ ዳር ዳር የነበረው ግጭት ወደ መሀል ሀገር እና መጠኑ እየሰፋ ሲሄድ የደህንነት መስሪያ መስሪያ ቤቱ ምን እየሰራ ይሆን ? ሲሉ ከጠየቁ በኋላ «ብቻ አንድ ከውስጥ ያልጠራ ነገር ያለ ይመስላል ወደ ሚኒስትር መስሪያ ቤታችሁ እና ሹማምንቶቻችሁ ተመለሱና መፅዳት ያለበትን ብታፀዱ አገርንም መታደግ ይቻላል ባይ ነኝ።»በማለት መንግሥትን ያሳሰቡት ደግሞ ጥበቡ ደምሴ ናቸው።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ኢሰመጉ የኢትዮጵያ መንግስት በሃገሪቱ የተለያዩ አቅጣጫዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶችን መከላከልና ማስቆም ያልቻለበትን ምክንያት እንዲያሳውቅ በዚህ ሳምንት ረቡዕ ባወጣው አስቸኳይ መግለጫ ጠይቋል።  «የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን በማስቆም አገርን እንታደግ» በሚል ርዕስ ኢሰመጉ  በፌስቡክ ገጹ ባወጣው በዚሁ መግለጫው መንግሥት ስለወደፊት እርምጃዎቹ ይፋዊ ማብራሪያ እንዲሰጥም ጥሪ አቅርቧል።

አዎ መንግስት ምክንያቱን በግልፅ ለህዝብ ቀርቦ እንደመሪነቱ ማስረዳት አለበት ሲሉ ፋንታሁን መንጌ በሃሳቡ እንደሚስማሙ በፌስቡክ ባሰፈሩት አስተያየት ገልጸዋል። ማሬው ቦረና ደግሞ ምክንያቱ«የመንግሥት አመራሮች ችግር ነው በማለት ሃሳባቸውን አካፍለዋል። ማንደፍሮ መኮንን በሚል  የፌስቡክ ስም የሰፈረ አስተያየት« ኢህአዴግን ለማዳከም ተሳታፊ የሆነ አካል በሙሉ ሀገራችን ለገባችበት ችግር የታሪክ ተወቃሽ ከመሆን አይድንም ይላል።መሃሪ ወርቅነህ በበኩላቸው

»ወሬ ብቻ እዳይሆን ተጠያቂዉን በተግባር ማሳየት ነዉ።»በማለት አሳስበዋል።

ኢሰመጉ«ከዚህ ቀደም በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የተፈፀሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ይፋ በማውጣት መንግስት አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ ሲወተውት እንደነበር ገልጾ ፣የመብት ጥሰቶቹ ከመባባሳቸው በፊት መንግስት ኃላፊነቱን እንዲወጣ፤ ካልሆነ ተጠያቂነት እንደማይቀር ማሳሰቡንም አስታውሷል።« ሆኖም  የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰና እጅግ አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሶ ሰብአዊ መብቶች ምንም ዋስትና የላቸውም ማለት የሚቻልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል» ብሏል በአስቸኳይ መግለጫው።ለዚህም በአጣዬ ከተማና አካባቢው በቅርቡ የተፈጸመውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንደ ማሳያ አቅርቧል። «አካባቢው የጸጥታ ስጋት እንዳለበት ታውቆ ጥንቃቄ መውሰድ ሲገባ ከሚያዚያ 6፣2013 ምሽት ጀምሮ በተከታታይ ቀናት በተፈጸመው ነዋሪዎች ላይ ባነጣጠረ ከባድ ጥቃት የሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ ንብርት እንዲወድምና ሰዎችም እንዲፈናቀሉ አድርጓል» ሲል ኢሰመጉ በመግለጫው አስታውቋል።

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ

ፖለቲካ  ኢትዮጵያ