1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ የካቲት 5 2013

«የምዕራባውያን ድራማ ለእኛ ጠፍቶን ነው? ቢሆንም የኤርትራ ሰራዊት ከትግራይ ይዉጣ፤ መንገዶች ለዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶችና ለገለልተኛ አጣሪ ኮሚቴዎች ክፍት ይሁን። ሌላዉ አስተያየት ሰጭ መንግስት ሆይ የነጀዋር መብት ይከበር ብለዋል። ሌላዉ በአስተያየታቸዉ ሰው ግን ይኼን ያህል ቀን ያለምግብ መቆየት ይችላል ማለት ነው? ቀልድ ነው»

https://p.dw.com/p/3pHGg
Symbolbild I BigTech I Social Media
ምስል Nicolas Economou/NurPhoto/picture alliance

የአውሮጳ ትግራይ መግለጫና የእነ አቶ ጃዋር የርሃብ አድማ

የኢትዮጵያ መንግስት የአውሮጳ ሕብረት «በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ቀውስ እየደረሰ ነው» በማለት ያወጣውን መግለጫ በዚሁ በያዝነዉ ሳምንት ነበር የነቀፈዉ። የኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር እንደሚለዉ የሕብረቱ መግለጫ መንግሥት በክልሉ እያቀረበ ያለውን የሰብዓዊ ርዳታ ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው። የአውሮጳ ሕብረት በዚሁ ሳምንት ባወጣዉ መግለጫ የኤርትራ ወታደሮች ትግራይ ዉስጥ መግባት እና በክልሉ እየተፈጠረ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ አሳስቦኛል ማለቱ እና  የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢያዎች ያለ ገደብ እንዲገቡ  እና ለስደተኞችና ለሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ እንዲያደርግ መጠየቁ ነበር። ቀደም ሲል የአሜሪካ መንግሥት ተመሳሳይ መግለጫን ማዉጣቱ አይዘነጋም ። በሌላ በኩል  የኢትዮጵያ መንግሥት እና አጋሮቹ ቀደም ሲል 1,8 ሚሊዮን ለሚጠጋ ነዋሪ ትግራይ ውስጥ ርዳታ ማድረሳቸውን የዓለም ምግብ ድርጅት ኃላፊ ማወደሳቸውን በዚሁ ሳምንት  የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንሥቴር በሰጠው ሳምንታዊ መግለጫ ገልጾአል። በትግራይ የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦቱ በበርካታ የትግራይ ክልል ተደራሽ እንዲሆን መንግሥት እየሰራ ነው ሲልም በመግለጫዉ አሳዉቆአል። በአዉሮጳ ኅብረት መግለጫን ተከተሎ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል፤አቤል ካሳይ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ፤ እኔም እንዲህ ነው ብየ በርግጠኝነት መናገር አልችልም። ግን በጦርነቱ ብዙ የተጎዱ ንፁሐን ዜጎች አሉ። እነዚህ የተጎዱት የትግራይ ህዝቦች በርሃብ ፣ በሥነ-ልቦና እና በኢኮኖሚ ተጎድተዋል። ብዙ ችግር እየደረሰባቸው እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም። ከጎናቸው መሆን ያስፈልጋል፤ ብለዋል። 

Äthiopien Addis Ababa | Minister | Mufrihat Kamil
ምስል Yohannes Geberegziabher/DW

የትግራይ ህዝብ ጥያቄ ሲሉ አስተያየታቸዉን የሚጀምሩት አሸናፊ ጃርሶ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ በበኩላቸዉ፤  የኤርትራ ሰራዊት ከትግራይ ክልል ይዉጣ፤  መንገዶች ለዓለም አቀፍ ሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች እና ለገለልተኛ አጣሪ ኮሚቴዎች ክፍት ይሁን። 

ይሄነዉ ገብርዬ የተባሉ ሌላዉ አስተያየት ሰጭ ፤ የኦዉሮጳ ኅብረት በሰው ሀገር ግብቼ ካልበጠበጥኩ ነውኮ የሚለው። ለትግራይ ህዝብ አሥቦ እንዳይመስልህ እስሬ  የሚጮኸው። ለሁለቱም መሣሪያ እያቀበሉ ዘላቂ ጦርነት ለማድረግ ነው።  ሶሪያ ፣ሊቢያ ፣የመንን እንዳደረጉቸው ተመልከቱ ። የአዉሮጳ ህብረት እራስዋን የቻለች ሉዓላዊ አህጉር አፍሪቃን  አይፈልግም ። የራሣቸውን አሸንጉሊት ማስቀመጥ ነው የሚፊልጉት። ድንቄም ሰብዓዊ ድጋፍ ብለዉ ይሄነዉ ገብርዬ  አስተያየታቸዉን ያጠቃልላሉ።

አለማየሁ አንጀሎ አዳሙ ፤ የትግራይ ህዝብ ይህ ሁሉ መከራ የማይገባው ፍቅር የሆነ ህዝብ ነበር ።ለዚህ ያበቁት ሁሉ ቀናቸውን ጠብቀው የእጃቸውን ያገኛሉ።  በእርግጠኝነት እላለሁ ፈጣሪም ዋጋቸውን ይከፍላል አትጠራጠሩ  ሲሉ አስተያየታቸዉን ይቋጫሉ።

ሰናይ ልመንህ የተባሉ ሌላዉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ የአውሮጳ  ህብረት--በሰው ሀገር ላይ እንደልብ ለመፈንጨት መመኘት የለበትም፣ የመይሆን ነው ! ሲሉ አስተያየታቸዉን በቃል አጋኖ ይደመድማሉ።

አሁን ሁላችንም ወሬ ትተን ሀገራችን የምታድግበትን ጠግበን የምንበላበት የምንማርበትን በሠላም ወተን በሠላም የምንገባበት ሃገር እንድትሆን መስራት አለብን ።  መፀለይ አንዱ ላንዱ መልካም ነገር መመኘት አለብን ።  እንደድሮአችን መተሳሰብ ቀና ልብ እንዲኖረን መፀለይ ነዉ ሲሉ አስተያየታቸዉን የፃፉት ፀሐይ ደለለኝ ይባላሉ። ፀሐይ በመቀጠል በውስጣችን ብዙ የተመረዝንበትን ነገር እግዚአብሔር  ከውስጣችን ያጥፋልን።  መጥፎ አስተያየት የምትፅፉ እግዚአብሔር ቀና ቀናውን ያሳስባችው እላለሁ ብለዋል።

ስዩም ክንፈ በበኩላቸዉ ህወሓት መሰሪ እብሪተኛ እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀል እንዳለችው እንስሳ ዓይነት ራስ ወዳድ ዘራፊ ቡድን ነው፡፡የተንኮሎች ሁሉ ምንጭ ነው፡፡እንዲህ ዓይነት ነውረኛ ቡድን ኢትዮጵያን ሊገዛ አይገባም ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።

Äthiopien Konflikt Tigray | Mai Aini-Flüchtlingszentrum
ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

የኛ ጥያቄ ሲሉ አስተያየታቸዉን የሚጀምሩት ኢሳይያስ አይናለም በበኩላቸዉ የኛ ጥያቄ የ ሻእቢያ ወታደር ከ ትግራይ ክልል ይውጣ ንፁሀንን አትግደሉ እናቶቻችንን እህቶቻችንን ህፃናትን አትድፈሩ የትግራይን ንብረት አትዝረፉ አታዘርፉ ነው ፤ ይላሉ።

ሳይለንስ አም የሚል ስም ለራሳቸዉ የሰጡ የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚ ደግሞ ወይ ብልጽግና እሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ ሆኖ ይገኝ እስከ ምስራቅ አፍሪካ የተባለው ለእኛም አልሆነን ሲሉ አስተያየታቸዉን ይደመድማሉ።

ሬማ ሮክ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ደግሞ  አሁን የምዕራባውያን ድራማ ለእኛ ጠፍቶን ነው። እኔ የእርዳታውን ስንዴ በጣሳ ሰፍሬ ዘይቱን በስኒ ለክቸ ካልሰጠሁ ማለት ግብዝነት ነው። በደርግ ዘመን የሰሩትን ድራማ እንዲደግሙት አይፈቀድላቸውም  ሲሉ አስተያየታቸዉን አብቅተዋል።

አሸብር መኮንን በበኩላቸዉ መቸም ቢሆን የማምነው የችግሩ መነሻ ህወሓት ናት። ብሔር ለይታ በድንበር ጥበቃ ላይ ያለውን መከላከያ የጨፈጨፈ ማነው? ይጠይቃሉ። በማይካድራ 1000 ሰው በላይ ብሔር ለይተው የጨፈጨፈ ዐብይ ነው? ዐቢይ በትግራይ ውስጥ ወታደራዊ ኢላማን ደምስሷል ። ይህ ተገቢ ነው፡፡የጀግና ሽልማት ይገባዋል። አሁን ትግራይ ውስጥ ባለው ቀውስ ፡ረሐብ ተጠያቂ ወያኔ ብቻ ነው ብለዋል።

ሮባ ኤራ ረዘም ያለ አስተያየት ነዉ ያስቀመጡት ። እውነቱን ለመናገር ይላሉ ሮባ እዉነቱን ለመናገር ጁንታውን ለመደምሰስ ረድተውናል።  ግን አሁን እነሱ በኢትዮጵያ ንብረት ዘረፋ ላይ ስለሚሰሩ ትግስታችን አስጨርሶናል።  ምንም ቢሆን ሀገራችን ስትዘረፍ እና ስትደፈር ማየት ለወታደር ህመም ነው። የኤርትራ ወታደሮች እንዲወጡ እንደ አንድ ሀገር ወታደር ሁላችንም እንፈልጋለን።  ግን እውነት መነጋገር ጥሩ ነው። እነሱ በፍጹም መወጣት አይፈልጉም። እኛ ደግሞ እነሱ ለማስወጣት በቂ አቅም የለንም። ስለዚህ መፍትሄዉ ምንድነው ብትሉ የሁላችንም ጥያቄ ሆኗል። በዚህ  ከቀጠሉ ነገሮች ወደማያባራ ጦርነት ይወስደናል። ስለዚህ  መወጣታቸው ግድ ነው ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

ሰላማዊት ማለደ የተባሉ ሌላዋ የፌስቡክ ተከታታይ፤ የተራበው የትግራይ ህዝብ ምግብ እንዳይደርሰው ህውሃት የደፈጣ ውጊያ ከጀመረ ታዲያ የአውሮጳ ህብረት ማስጠንቀቅ ያለበት ህውሓትን ነው ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።መናገር መብት ነው ማድረግ ግን አይችልም የሚሉት ደግሞ ግርማ አሰፋ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ናቸዉ። የሚኒሊክ እጆች በባንዳ እጁን አይጠመዘዝም።አውሮጳውያን ያውቁታል። ጁንታውም ጠንቅቆ ያውቀዋል። የሚኒሊክን መንፈስ ቅኝ ገዥወች ሚኒሊክን እያስታወሳቹ መግለጫ ብትሰጡ ጥሩ ነው ሲሉ አቶ ግርማ አሰፋ አስተያየታቸዉን ይቋጫሉ።

Äthiopien I  Sudan I Konflik
ምስል Ashraf Shazly/AFP

መኮንን አዘዘዉ  የተባሉ ሌላዉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ በአስተያየታቸዉ ፤ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለይም ትግራይ ዉስጥ አንድ የኤርትራ ወታደር የለም። ምኑን ነዉ ይዉጣ የሚሉት ሲሉ አስተያየታቸዉን በጥያቄ ይዘጋሉ ? አጋጣሚውን ተጠቅመው ኤርትራን መጎንተላቸው ነው የሚሉት ደግሞ በጋሻዉ ስማርት ናቸዉ ረዘም ያለዉን አስተያየታቸዉን ሲጀምሩ። አጋጣሚውን ተጠቅመው ኤርትራን መጎንተላቸው ነው ። ምናልባት የሕብረቱን አንጎል እያዞረች ያለችውን ቱርክ በአጋርነት ኤርትራ እንዳትወዳጃት በመስጋት የመጣ ነው። የጭንቀታቸው ምልክትም ግብጽ ከኤርትራና ከኢትዮጵያ ጋር የገባችው እሰጥአገባ ነው።ይህንንም ተከትሎ ግብጽን በፍርሃት ቆፈን ለማንቀጥቀጥ የቱርክና የኤርትራ ወዳጅነት ወሳኝ ነው ።ይሕ ደሞ በሜዲተራንያን  ባሕር አካባቢ ይዞታዋን በማስፋፋት ግሪክንና የፈረንሳይን እያስጨነቀች ያለችውን ቱርክ ሕብረቱ በፍርሃት ዓይን እያየ ባለበት ሁኔታ የኢትዬ-ኤርትራ ከግብጽ ጋር መወዛገብ ጉዳዩን ከሜዲንትራንያን ወደ ቀይባሕር ይለጥጥብኛል ብለው የፈሩት ምእራባውያን፤ መሠረተ ቢስ ክስ በመደርደር ኤርትራን በጎን የዲፕሎማቲክ ግብዣ እያቀረቡ መሆኑ ለኤርትራ ግልጽ ነው ። ለትግራይ ሕዝብ ከኤርትራና ከኢትዬጵያ ሕዝብ የበለጠ ቀራቢ ይመስል ሕብረቱ ዝም ብሎ ይጮሃል ብለዋል አስተያየታቸዉን ሲያጠናቅቁ። ፈሪስ ሲራጅ የተባሉ የፌስ ቡክ ተከታታይ የሰጡትን አስተያየት ላካፍልና በአዉሮጳ ትግራይ መግለጫ ላይ የተሰጠዉን አስተያየቶች ላብቃ። እኔ የሚገርመኝ ይላሉ ፈሪስ ሲራጅ እኔ የሚገርመኝ የአውሮጳ  ሕብርት ምናምን እርዳታ ስጪ ምናምን የሚባሉት ድርጅቶች እውነት እውነት እንነጋገር ከተባል፤ ይህን ያህል የተጨነቁልን ስብአዊነት ተስምቷቸው ከሆነ ከዚህ በፊት የሰብዓዊ  ቀውስ ኢትዮዽያ ውስጥ ሲከስት የት ነበሩ ?  ምንስ አደረጉ ? የአፍሪካ ሕዝብ በፖለቲካ በተለያዩ ችግሮች ወደ አውሮጳ  ባህር አቋርጠው ለገባ ስደተኛና በባሕር ላይ ላለ ስደተኛ ምን አይነት ግብረ መልስ እንዳደረጉ ከዓለም ሕዝብ የተስወረ አይደለም። ታድያ እነዚህ አሁን ላይ ያሳከካችሁን ቦታ እኛ ነን የምናውቀው፤ እንከክላችሁ የሚሉን፤ ይህን ሰብዓዊነታቸውን ያኔ ለምን አላሳዩንም። በጎርፍና በአበጣ መንጋ ስንወረር አለስሙም፤ አላዩም፤ ብለን እንኳ ብናልፈው አሁን ሱዳን ስትወረን ለምን ብለው ጠይቀው ያውቃሉ፤ ወይስ ጦርነቱ ተጀምሮ ትርምስምሱ እስኪፋጠን  እየጠበቅ ነው ማለት ነው ? በችግረኛው ወይም በተቸገሩ ስዎች ወይም ሐገሮች ስም በሚስበስበው የሚነግዱ ድርጅቶችን ለማገልገል አላያም የስራ እድል ለመፍጠር ካልሆን ችግር ከመፈጠሩ በፊት ለምን ችግሩ እዳይፈጠር አላደረጉም ? ሲጀመር ሲጀመር ለጥቅር ሕዝብ ያላቸው ግምት እየታወቀ እያለ ደረት እየመቱል ያለቅሳሉ እዝኑ ካላችሁ መንግስት አለን፤ ሕግ አለን መንግስታችንና ሕጋችንን አክብሩ፤ ቢያስ ቢያስ በሐገራችን ጉዳይ  እኛ ሕዝቦቿ እንበቃለን። ልታግዙን ካስባችሁ አክብሩን እንከባበር ይባስ እሳተ አታቀጣጥሉ !

Äthiopien Jawar Mohammed
ምስል Tiksa Negeri/Reuters

 የእነ አቶ ጃዋር ሞሐመድ እና የታሳሪ የፖለቲካ ፓርቲ  ከፍተኛ አመራሮች የርሃብ አድማን በተመለከተ በተዘገበዉ ዜና ላይ ከተሰጡት አስተያየቶች መካከል አብዛኞቹ ማለት ይቻላል የጣብያችን ስርዓት በአጠቃላይ የሚዲያን ስነምግባር ያላሟሉ በመሆናቸዉ ለማቅረብ ይቸግራል ። ይሁንና አንድ ሁለት ተመርጦ ከተገኘዉ መካከል ፤ ቢኒያም ካሳሁን የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት  በርሀብ አድማው ጉዳይ ምን ተብሎ ነው ውይይት የሚያካሂዱት? መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ቆፍጠን ያለ ግልፅ አቋም መያዝ አለበት አለበለዚያ የከፋ ነገር እንዳይገጥመን እሰጋለው። መንግስት ብሉ ከማለት ውጪ ሌላ ምንም ሊል አይችልም። መንግስት ላይ እና አገር ላይ ጫና ለመፍጠር የታሰበ  ከሆነ ግን አደጋ አለው። ግለሰቦች እና ቡድኖች ከኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት አይገዝፉም፣ አገራችን ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘወርዋሪ  ጫና እና አለመረጋጋትን የሚፈጥሩ ግለሰቦችም ሆነ ህቡዕ ቡድኖችን አጥብቄ እቃወማለው! ድል ለሰፊው እና ነፃነት ናፋቂው ህዝብ! ኢትዮጵያ ታሸንፋለች! ሲሉ አስተያየታቸዉን ይቋጫሉ።

አማ ታከለ የተባሉ ሌላዉ የፌስቡክ ተከታታይ በበኩላቸዉ ፤ የረሀበ አድማ ኢስያስና ዐብይ ምንም አይመስላቸውም። ህይወታቸው ቢጠፋም ጪምር ። ስለዚህ  የነዚህ  ኦሮም የፖለቲከኞን  ለማዳን ሰፊው የኦሮሞ ህዝብ በአንድነት ተነስቶ መብቱ እንዲከበር መቆም አለበት። ያለማቓረጥ ከእስር እስኪለቀቁ ድረስ ትግሉ መቀጠል አለበት።

ብርሃን አስረሴ የተባሉ ሌላዉ አስተያየት ሰጭ ፤ መንግስት  ሆይ የነ ጀዋር መብት ይከበር ብለዋል። ወይንሸት ጥበቡ በበኩላቸዉ ሰው ግን ይኼን ያህል ቀን ያለምግብ መቆየት ይችላል ማለት ነው? ቀልድ ነው ሲሉ አስተያየታቸዉን ያበቃሉ ።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ