1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ የካቲት 27 2012

ኢትዮጵያ የህዳሴው ድርድር እንዲገፋ መጠየቅዋን ተከትሎ፤ ኢትዮጵያ የታላቁ የኅዳሴ ግድብ «የመጀመሪያ ሙሌት እና የውሃ አለቃቅ መመሪያ እና ደንብ ለማዘጋጀት የሚደረገው ድርድር ተጠናቋል በሚል» አሜሪካ ያወጣችውን መግለጫ ውድቅ ማድረግዋ እንዲሁም ኦነግ መንግሥትን አስጠነቀቀ በሚል ዘገባ ስር ላይ በርካታ አስተያየቶች ተንሸራሽረዋል። 

https://p.dw.com/p/3YzZz
Symbolbild Digitalsteuer & US-Internetkonzerne
ምስል picture-alliance/dpa/S. Jaitner

የሕዳሴዉ ግድብና የኦነግ ማስጠንቀቅያ

ሰሞኑን በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች በርካታ አስተያየት ከተሰጠባቸዉ እና ከአወያዩ ርዕሶች መካከል ኢትዮጵያ የህዳሴው ድርድር እንዲገፋ መጠየቅዋን ተከትሎ ፤ ዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያ ላይ እያሳረፈች ያለዉን ጫናን በመቃወም ኢትዮጵያዉያን ዋሽንግተን ዲሲ ላይ ያሰሙትን ተቃዉሞ ፤ ኢትዮጵያ የታላቁ የኅዳሴ ግድብ «የመጀመሪያ ሙሌት እና የውሃ አለቃቅ መመሪያ እና ደንብ ለማዘጋጀት የሚደረገው ድርድር ተጠናቋል በሚል» አሜሪካ ያወጣችውን መግለጫ ውድቅ ማድረግዋ እንዲሁም የሕዳሴ ግድብን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን ምን ይላሉ? በሚል በዶቼ ቬለ በቀረቡ ዘገባዎች እንዲሁም ኦነግ መንግሥትን አስጠነቀቀ በሚል ዘገባ ስር ላይ በርካታ አስተያየቶች ተንሸራሽረዋል። 

ሙሉነህ ሱጌቦ የተባሉ የፌስ ቡክ ተከታታይ ፤ «የትራምፕ አስተዳደር እንስራ ይዛችሁ ወደ ወንዝ ስትወርዱ እኔን ወይም ግብፅን አስፈቅዱ ማለት ነው የቀረው:: ኢትዮጵያውያን የባዕድ ወረራንና አስከፊ ድህነትን ጨምሮ የብዙ ችግር ልምድ አለን:: ያልለመድነውና የማንለምደው ግን ነፃነት ማጣትን ነው:: ይህን ወዳጅም ጠላትም ቢያውቅልን ጥሩ ነው:: ኢትዮጵያውያን ለአገራችን ነፃነትና ክብር መሞት ብሔራዊ ኩራታችን ነው:: ነፃነት ሥነ-ልቡናችን ውስጥ ያለ ጉዳይ ብቻ አይደለም። ደማችን ዉስጥም ያለ ጉዳይ ነዉ» ብለዋል። 

BG Grand Renaissance Dam | Standort des Grand Ethiopian Renaissance Damms (2013)
ምስል picture-alliance/AP Photo/E. Asmare

አሜሪካ ለጥቅሟ የሞተች ሀገር ነች እንጂ ፍታህዊ ሀገር አይደለችም፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን የሚጀምሩት ግርማ ሙሉነህ የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ ናቸዉ። «በእልህ እኛ ኢትዮጵያዊን ግድቡን ከዳር እናደርሰዋለን። ነገር ግን ሁሉንም ነገር በጥንቃቄ መከታተል ይገባል። ለግድቡ የአይር መቃወሚያ መሳሪያ ማስገጠምና ቀን ከለሊት መጠበቅ ተገቢ ነዉ። ለጦር ኃይል ተገቢዉን የገንዘብና የሰዉ ኃይል ማደራጀት የግድ የሚልበት ሰዓት ነዉ። እዲያዉም በቶሎ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ቢደረግና ለግድቡ መስሪያ ገቢ ቢሰበሰብ በጣም ጥሩ አጋጣሚ ነዉ» ባይ ናቸዉ።

ምኒሉ ዳጉ የተባሉ የፉስ ቡክ ተከታታይ፤ በበኩላቸዉ ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጀርባ እስራኤል መኖርዋ ጥያቄ ዉስጥ የሚገባ አይደለም ። ምኒሉ አስተያየታቸዉን ይቀጥላሉ። ኢትዮጵያዉያንም ለግብጽ ወገንተኝነትን ባሳየዉ የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስቴር አድሎዋዊ መግለጫ አዝነዋል። ግብጽ በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል ያለዉን ፍጥጫ ለማርገብ እና የሰላም ስምምነት አመጣለሁ ብላ አሸማጋይ እሆናለሁ ብላ በምዕራባዉያኑ ዘንድ ለዓመታት ጠቃሚ መስላ ለመታየት ስትንቀሳቀስ ነበር በርግጥ የፈየደጥዉ ነገር የለም። በዚህም ምክንያት ግብዝ ከምዕራባዉያኑ ዘንድ በንግዱና በፖለቲካዉም ዘርፍ ከፍተኛ ተጠቃሚ ናት። በዚህም አለ በዝያ ኢትዮጵያዉያን በአንድነትና በጥንካሪ መቆም ይጠበቅባቸዋል፤ ብለዋል።     

የግብጽ ህዝብን የሚጎዳ አሠራር የኢትዮጲያ ህዝብ እንደማይደግፍ ሁሉ የግብጽም ህዝብ ይሄ አመለካከት ሊኖረው ይገባል፤ ያሉት ደግሞ አላሌ አለበል ዎርክነህ ናቸዉ። በመቀጠል አፍሪካዊ ወንድም ሀገሮች እንደመሆናችን እኛው የራሳችንን ጉዳይ እራሳችን ልንወጣው ይገባል፡፡ የቀኝ ገዥ አመለካከት ያላቸውን ሀገሮች በዚ ድርድር ማስገባት በአባይ ወንዝ ምክንያት ሁለቱ ሀገሮች ከሚገቡበት ችግር በላይ ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላልና፡፡ ስለዚህ የግብጽ ህዝብ በሠለጠነ መንገድ ነገሩን ሊያስተውለው ይገባል ብለዋ። 

USA Treffen über die äthiopische GERD-Delegation in Washington
ምስል Fitsum Arega, Ethiopian ambassador to the United States

ሳንታ ሎካስ የተባሉ  የዶቼ ቬለ አድማጮ በበኩላቸዉ የአሜሪካ ችግር እኔ የዓለም ፖሊሲ ነኝ ማለቷ ነው፡፡ ከኔ በላይ ዲሞክራሲያዊ አገር የለም ባይም ናት፡፡፡ የውጪ ግንኙነት ፕሊሲዋ ግን ፀረ ዲሞክራሲያዊ ነው፡፡ ለዛም ነው ዓለም ሰላም ያጣው፡፡ የዓለምን የኃይ ቁንጮ ይዞ ፀረ ሰላም መሆን ያሳፍራል፡፡

አለም ሰይፉ አንዋር አህመድ እንዲሁም ባሃር አሊ የተባሉ የፊስ ቡክ ተከታታዮች ያስቀመጡ አስተያየት ከሞላ ጎደል አንድ  ሃሳብ ያለዉ ነዉ። እኛ ኢትዮጵያውያን በተፈጥሮ ሀብታችን የማልማት እና የመበልፀግ መብታችንማንም ሊነፍገን አይችልም።  ትንሽ የምላስ ወለምታና የአቋም መዋዠቅ ካለ ልነወጣው የማንችለውን አይነት ጫና ሊፈጥሩና ሊያሰናክሉን መስራታቸው አይቀርምና ይታሰብበት ፡፡  እውነታውን ነጋሪ አያሻውም የሚያዋጣው ግድቡን ለማጠናቀቅ እና ለመጠበቅ አቅም መገንባት ነው ሌላ ዋስትና የለንም፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ጽፈዋል። 
አበባዉ ብርሃኑ አዱ በበኩላቸዉ  የሃገር ክብር እና ብሄራዊ ጥቅም እንዳለ ሆኖ ከአሜርካ ጋር እልክ ውስጥ መግባት አደገኛ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል ። በዲኘሎማቲክ መንገድ ማሸነፉ ይመርጣል፤ ሲሉ ያሳስባሉ። 
አምደማርያም ሙጬ በበኩላቸዉ አሜሪካ ለኢትዮጵያ መቼም ወዳጅ ሆና አታውቅም። ሲሉ ረዘም ያለዉን አስተያየታቸዉን ይጀምራሉ። አማሪካ የጭቃ ውስጥ እሾህ ነች።ጉልበት እንጅ አንድም አኩሪ ታሪክ የሌላት የትናንቷ አሜሪካ የታሪካዊቷ እና ጥንታዊት ኢትዮጵያ ቁጥር አንድ ጠላት መሆኗ ዛሬም እየታየ ነው። ምክንያቱ ደግሞ በነጭ አውሮጳዊ ወራሪ ኃይል ላይ ኢትዮጵያ በአድዋ የተቀዳጀችውን ድል ተከትሎ ከአፍሪቃ ጀምሮ በመላው ዓለም፤ በተለይ በአሜሪካ በባሪነት ቀንበር ስር እየማቀቁ የነበሩት ጥቁር ሕዝቦች ለነጭ ጌቶቻቸው አንገዛም የሚል የተጠናከረ ትግል ማድረግ መጀመራቸው ነው። ኢትዮጵያ መላው ጥቁር ሕዝቦች ራሳቸውን ከፍ አድርገው እንደሰው እንድቆጥሩ የመንፈስ አባት ሆናለች ብለው ካሰቡበት ግዜ ጀምሮ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ነጭ አውሮጳዊያን በተለይ አሜሪካና ኢትዮጵያን በጠላትነት ፈርጀዋታል። በዚህም ታሪኳ እና ክብሯ እንድጠፋ ብዙ ሰርቷል። እስከዛሬም ቀጥሏል። በተለይ ስር የሰደደ የአሜሪካ ጠላትነትን ለማሳየት ያህል ከብዙ በጥቅቱ እነሆ፣ አንድ፡ በባርነት ስር የነበሩ ጥቁር አፍሪካውያን ጉልበት በመበዝበዝ ያደገችው አሜሪካ በአድዋ ጦርነት እና ስቀጥልም በሁለተኛው የኢጣልያ ወረራ ወቅት በርካታ ሺህ የሆኑ የአሜሪካና የካረቢያን ጥቁር ሕዝቦች ከኢትዮጵያ ጎን ለመሆን በሚል ገንዘብ አዋጥተው እና መርከብ ተከራይተው ለጉዞ ሲሰናዱ አይታ ጉዟቸውን በኃይል ከልክላለች። 
ሁለት፡ በንጉስ ኃይሌ ስላሴ የስልጣን መጨረሻ አካባቢ ከሶማሊያ የተቃጣብንን ወረራ ለመመከት በሚል ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ብዙ ሚሊዮን ዶላሮቿን አውጥታ ግዢ የፈፀመችውን በርካታ የጦር መሳሪያዎችን በመከልከል ሶማሊያ የልብ ልብ ተሰምቷት ኢትዮጵያን እንድትወር አይነተኛ ሚና ተጫውታለች። ሦስት፡ የንጉስ ኃይሌ ስላሴ ስልጣን ማብቃት በኋላም የአሜሪካው ሲአይኤ በካርቱም ከተማ በከፈተው ግዜያዊ ቢሮ በኩል ለሻዕብያ እና ለወያኔ በቀጥታ አስፈላጊ የሆነውን ሁሉ እርዳታ በመስጠት ኤርትራ እንድትገነጠል እና ወያኔ ስልጣን ላይ ወጥቶ ኢትዮጵያን በጎሳ እንዲከፋፍል አይነተኛ እገዛ አድርጓል። ስለዚህ እንንቃ እንጅ ጎበዝ!! ስንዴ ስለሰጠችን አንሸወድ። አምደማርያም ሙጬ አስተያየታቸዉን ያበቃሉ። 

 Logo Oromo Liberation Front

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ «በሀገሪቱ ታሪክ እስከ ዛሬ ያልተፈጸመ» ያለው ግፍ እየተፈጸመብኝ ነው ሲል በዚህ ሳምንት ረቡዕ  በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ «የፖለቲካ ምህዳሩ የሰፋ መስሎን ወደ ሀገር ቤት ብንመለስም፣ መንግሥት በጦር ሠራዊቱ እና በሃብቱ በመተማመን በፓርቲያችን ላይ ግፍ እየፈጸመብን ነው» ይህ  መቆም ካልቻለ የማያባራ እሳት ይቀጣጠላል ሲል ማስጠንቀቁን ተከትሎ  ፤ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል ፤ 
ኤፍሬም ይልማ  የማዝነው መሬት ጠብ ለማይል ትግል በድርጅቱ ስር ገብተዉ ለሚሞቱ ኢትዮጵያዊ እህትና ወንድሞቼ!ነዉ  ( ደግሞ ኤፍሬም በቅንፍ ባስቀመጡት አስተያየት ደሞኮ እኮ ተዋግተው አይደለም የሚሞቱት እርስ በእርስ ባላቸው የስልጠን ሽኩቻ ነዉ)
ናና ቴሜ የተባሉ የፌስ ቡክ ተከታታይ በበኩላቸዉ ፤  አረ ኦነግ ለ40ዓመታት የኢትዮጵያን ምድር እንዳትረግጡ  እንዳልተደረገ ዛሬ በጨዋነት መንቀሳቀስ ሲፈቀድ  ዋ  ህወሓት መጥታ በአሸባሪነት እንዳትፈርጃችሁ።  ግፍንፈጣሪ ያያል ብለዋል። ቱሉ ቱፋ እርምጃ መውሰድ አይደለም ከነጭራሹ ብትጠፉልን ደስታውን አንችለውም ከናንተ ያገኘነው ነፃነት ሳይሆን ሞትና ዝርፊያ ብቻ ነው፤  ሲሉ የሺነህ ወልዴ ደሞ ይቺን ፊልምሽን እናውቃታለን ሳይነኩ  ነኩኝ ። መጪው ዘመን ከአብይ ጋር ብሩህ ነው ። ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል። 
ሳምሶን ሳምሶን የተባሉ የፌስ ቡክ ተከታታይ በበኩላቸዉ ፤ ኦነግ ግን በዚህ ሰአት የግብጽ ጠበቃ ነኝ ለማለት ነው መንግስት የምታስጠነቅቀው? አንድ ነገር ሳትሰስሩ እድሜ ቁጠሩ ብቻ።  የኦሮሞ ህዝብ ግን ፈርዶበት በስንቱ ይሰደብ? ሲሊ በጥያቄ ምልክት አስተያየታቸዉን ቋጭተዋል። እኔ የምገርመኝ ይላሉ አብዲ አብዶ የተባሉ አስተያየት ሰጭ እኔ የሚገርመኝ ኦነግ የከሰሰው ወይም የኦነግ መግለጫ የሚመለከተው መንግስትን ነው።ታድያ በዚህ መግለጫ ስር ሀሳባቸውን ያስቀመጡት አብዛኞቹ ከመግለጫው ፅንሰ ሀሳብ ጋር የሚጋጭ እና ኦነግን በመስደብ ሀሳብን ብቻ ያንፀባርቃል። እነኝህ ግለሰቦች በግልፅ የሚታወቁ በጥላቻ የታወሩ ፣ የኦሮሞ ጥላቻ ያላቸው የምንሊክ ልጆች ናቸዉ። ብለዋል። ደምሴ አባተ የተባሉ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸዉ ፤ ወንጀል እየፈፀሙ አባላቶቼ ታሠሩ ምናምን አይሠራም። ህግ መከበር አለበት። የፓርቲ አባል ስለሆነ ከተጠያቂነት ማንም አያመልጥም። ማንኛውም ፓርቲ የሚያዋጣው ህግን አክብሮ መንቀሳቀስ ብቻ ነው።

Äthiopien  Äthiopien Bekele Gerba in Mekelle
ምስል DW/M. Haileselassie

አዜብ ታደሰ 

ሸዋዬ ለገሠ