1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ሰኔ 15 2010

ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ ሽረው እየሾሙ፤ ለከረመ ቂም መፍትሔ እየፈለጉ ጉዞ ላይ ናቸው። ንግግሮቻቸው እና ውሳኔዎቻቸው ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ድጋፍ አግኝቶላቸዋል። ወቀሳም አላጣቸውም። ኢትዮጵያውያን በጠቅላይ ምኒስትሩ ውሳኔዎች እና ንግግሮቻቸው ላይ ያላቸውን አቋም ለመረዳት ፌስቡክ እና ትዊተርን መቃኘት ሁነኛ ዘዴ ነው። 

https://p.dw.com/p/306lM
Äthiopien Vorbereitungen zur Kundgebung im Unterstützung zum Premierminister Abiy
ምስል DW/Y. Gebregziabeher

የማሕብራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ሰኞ ጠቅላይ ምኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነበሩ። ንግግራቸው በፅሁፍ ከተሰጣቸው የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ውጪ ጠቅላይ ምኒስትሩ ምን ሊሉ እንደሚችሉ የሚያውቅ አልነበረም። ኢትዮጵያ ላይቭ አፕዴት የተባለ የትዊተር ገፅ እንደፃፈው "ETV, OBN, Fana, Walta, Debub Tv, Amhara Tv ሪፖርቱን በቀጥታ" አስተላልፈዋል።  ጠቅላይ ምኒስትሩ ሁለት ሰዓት ተኩል ገደማ በረዘመ የምክር ቤት ቆይታቸው ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል ከዚህ ቀደም የመንግሥታቸው ሹማምንት ከሚናገሯቸው የሚቃረኑ ይገኙበታል። ትልቁን ትኩረት የሳበው "ሽብር ስልጣን ላይ ለመቆየት ኢ ህገመንግስታዊ በሆነ መልኩ ሃይልን መጠቀምን ይጨምራል" ያሉት ጉዳይ ነበር።  የፖለቲካ ተንታኙ እና የዶይቼ ቬለ የኬንያ ዘጋቢ ቻላቸው ታደሰ ታዲያ "አብይ በተረከባት ሀገር መንግሥታዊ ሽብር (state terror) ተንሰራፍቶ መኖሩን በይፋ አመነ! እነሆ! ለ50 ዐመታት የምናውቀው ታሪክ እና ፖለቲካ ቢያንስ በትርክት ደረጃ በዛሬው ዕለት በይፋ አበቃ" ሲል ፅፏል። የሆርን አፌርስ መሥራቹ ዳንኤል ብርሐነ "ጠቅላይ ምኒስትሩ እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግሥት የሽብር ድርጊቶች ፈፅሞ ከሆነ ራሱን አፍርሶ የሽግግር መንግሥት እንዲመሰረት ጥሪ ማቅረብ አለበት" የሚል ሐሳቡን አጋርቷል።  

ጠቅላይ ምኒስትሩ በሕብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር እና አርበኞች ግንቦት ሰባትን የመሳሰሉ ተቃዋሚዎቻቸው እንዲመለሱ ያቀረቡት ጥሪ በጎ ምላሽ ያገኘላቸው ይመስላል።  አርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ ጠቅላይ ምኒስትር አብይ"ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን በመቆም በሚያደርጉት ትግል አብረናቸው መሆናችንን ልናረጋግጥላቸው እንወዳለን" የሚል መግለጫ አውጥቷል። ውሳኔውን የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ወርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጃዋር መሐመድ "የብልጥ ውሳኔ" ሲል ገልጾታል። የኢትዮጵያ መንግሥትን ለመጣል ነፍጥ አንግቦ ኤርትራ የወረደው ግንቦት ሰባት "ከዛሬ ሰኔ 15 ቀን 2010 ዓም ጀምሮ አርበኞች ግንቦት 7 በማናቸውም መልኩ በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍሎች ምንም አይነት አመጽ ነክ እንቅስቃሴ ከማድረግ ታቅቧል" የሚል መግለጫ አውጥቷል።

Logo Patriot Ginbot 7

ጋዜጠኛ አመዩ ኢታና በግል የፌስ ቡክ ገፁ እንዳሰፈረው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ሊቀ-መንበር ዳውድ ኢብሳ ድርጅታቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ ነው። ጋዜጠኛው እንደፃፈው አቶ ዳውድ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ሊደረግ ለሚችል ውይይት ግን ቅድመ-ሁኔታ አስቀምጠዋል።አቶ ዳውድ "በ1990ዎቹ እንደተፈጠረው አይነት ስህተትን ለማስቀረት የሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት አስያስፈልግም" ብለዋል። ሌላው ጋዜጠኛ መሐመድ አዴሞ በትዊተር ላይ እንደፃፈው መቀመጫውን በኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ያደረገውን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የሚመሩት አቶ ዳውድ "በኢትዮጵያ በሚታዩ ለውጦች መበረታታቸውን እና አሁን የሚታየው ለውጥ ከቀጠለ ኦነግ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በሰላማዊ መንገድ እንደሚታገል" ተናግረዋል። 

ብሔር ተኮሩ ጥቃት እና አሰቃቂው ቪዲዮ

ፌስቡክ ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድንን ማልያ የለበሰ ወጣት በደቦ ሲደበደብ የሚያሳይ ቪዲዮ እየተዘዋወረ ይገኛል። ድርጊቱ የት እና መቼ እንደተፈጸመ በግልጽ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም በሐዋሳ ከተማ ከተፈጠረው ብሔርን ያማከለ ጥቃት ጋር የተገናኘ ለመሆኑ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ፅፈዋል። የወላይታ ድምፅ የተባለ የፌስቡክ ገፅ "በወላይታ ህዝብ ላይ ከባድ ግፍ፤ እንግልት እና ሞት እየተፈፀመ ነዉ፡፡ ወላይታነት ወደ ሞት ፤ ወደ ስቃይ፤ወደ እንግልት ውስጥ መግቢያ ካርድ ከሆነ ቆይቷል፡፡ ይህንን ስቃይ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያየው እና ከወላይታ ህዝብ ጎን እንዲሆን ጥሪ እናቀርባለን" ከሚል አቤቱታ ጋር ይኸንንው ምስል አጋርቶታል። ምስሉ ለመመልከት የሚከብድ ከመሆኑ የተነሳ ፌስቡክ ጭምር ደንበኞቹ ቪዲዮውን ከመመልከታቸው በፊት እንዲጠነቀቁ ይመክራል። አቤኔዘር ቢ ይስሐቅ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ "በሀዋሳ በወላይታ ብሔር አባላት ላይ ያንን ዘግናኝ ድርጊት የፈጸሙና ያስፈጸሙ ሰዎች በአስቸኳይ ተይዘው ለፍርድ መቅረብ አለባቸው" ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት የሲዳማ የዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ ሲከበር በሐዋሳ ከተማ በተፈጠረ ኹከት ብሔርን ያማከለ ጥቃት መፈጸሙ ተሰምቶ ነበር። በወላይታ ብሔር ተወላጆች ላይ ባነጣጠረው ጥቃት በርካታ ሰዎች መፈናቀላቸው፤ መደብደባቸው ተሰምቷል። ጉዳዩ በወላይታ ሶዶ ቁጣ ቀስቅሷል፤ የሰው ሕይወት መጥፋቱን ንብረት መውደሙን የአካባቢው ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረው ነበር። ወደ ደቡብ አቅንተው ግጭቱን የተመለከተ ውይይት ያደረጉት ጠቅላይ ምኒስትር አብይ የሲዳማ፣ ወላይታ፣ ጉራጌ፣ ቀቤና የዞን እና የወረዳ አመራሮች ከሥልጣን እንዲለቁ መጠየቃቸውን የፅህፈት ቤት ኃላፊያቸው አቶ ፍጹም አረጋ በትዊተር ጽፈው ነበር። የወላይታ ዞን የባሕል ቱሪዝም እና የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት በፌስቡክ ገፁ ባጋራው ደብዳቤ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ እና ምክትላቸው፣ የድርጅት ፅህፈት ቤት ኃላፊ፣ የገጠር እና የከተማ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊዎች የጠቅላይ ምኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው ሥልጣን መልቀቃቸውን ይገልፃል። 

Eritrea Präsident Isaias Afwerki
ምስል Eritrea Minister of Information/Y.G. Meskel


የኢሳያስ አፈወርቂ ምላሽ እና የማኅበራዊ ድረ-ገፅ አቀባበል

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሚነጋገር የልዑካን ቡድን ወደ አዲስ አበባ ለመላክ መወሰናቸው በማኅበራዊ ድረ-ገፆች አነጋጋሪ ከነበሩ ጉዳዮች አንዱ ነበር።  ዶክተር ሰለሞን አየለ ደርሶ "በእርግጥም ለሁለቱም አገሮች እና ለአፍሪቃ ቀንድ ታላቅ እርምጃ" ብለውታል። ዶክተር ሰለሞን በትዊተር ገፃቸው በፃፉት አጠር ያለ መልዕክት "ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ ስለ ሰላም ለማለም በመድፈራቸው ሊደነቁ ይገባል" ሲሉ አክለዋል። የስዊድን ውጭ ጉዳይ ምኒስትሪት ማርጎት ዎልስትሮም በትዊተር ገፃቸው የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ውሳኔ አድንቀው "በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለውን ግንኙነት ማሻሻል ለቀጣናው ልማት እና መረጋጋት ቁልፍ ነው" ብለዋል።  በዓለም አቀፉ የቀውስ ጥናት ማዕከል የአፍሪቃ ቀንድ ኃላፊው ራሺድ አብዲ በበኩላቸው ውሳኔው የተላለፈበትን ዕለት "ታላቅ" ብለው ሁለቱም አገሮች በድንበር ይገባኛል ለገቡበት ግጭት ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር ሊጠቀሙበት ይገባል ሲሉ መክረዋል። 


ሰልፍ እና ሥጋት -አዲስ አበባ 

የጠቅላይ ምኒስትር አብይ ደጋፊዎች "ለውጥን እንደግፍ፣ ዴሞክራሲን እናበርታ" በሚል መፈክር ሰኔ 16 ቀን ከጠዋቱ 2 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ ሰልፍ ሊወጡ ዝግጅት ላይ ናቸው። በከተማዋ አደባባዮች የጠቅላይ ምኒስትሩ ምስሎች የታተሙባቸው ቲ-ሸርቶች ለሽያጭ ቀርበዋል። አጥናፍ ብርሐኔ በትዊተር ገጹ እንዳጋራው ከሆነ "የጸረ-ሽብርተኝነት፣ የሚድያ እና የሲቪል ማኅበራት ዐዋጆች ይሻሩ" የሚል መፈክር ለቅዳሜው ሰልፍ ተዘጋጅቷል። አዘጋጆቹ በፌስቡክ ባሰራጩት መልዕክት ቅዳሜ ሰላማዊ ሰልፍ የሚደረግባቸው አምስት ምክንያቶች ዘርዝረዋል። አዘጋጆቹ እንደሚሉት ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ማረጋገጥ ቀዳሚው ነው። 

"በቀጣዩ ቅዳሜ በመስቀል አደባባይ ሰላማዊ ስልፍ የምናደርግበት የመጀመሪያ ምክንያት ዴሞክራሲያዊ መብታችን ስለሆነ ነው። በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 30 መሰረት ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን በሰላም የመሰብሰብ፥ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው። በተለይ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ይህ መብት ሙሉ በሙሉ ተገድቧል። መስቀል አደባባይ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የወጡ ዜጎች ፍፁም ጭካኔ በተሞላው መልኩ ተደብድበዋል፣ ታስረዋል፣ ተንገላተዋል። በመሆኑም ቅዳሜ ዕለት በተመሳሳይ ቦታ ሰላማዊ ሰልፍ የምናደርገው እንዲህ ያለ በደልና ጭቆና መቅረቱንና ዴሞክራሲያዊ መብታችን መከበሩን በተግባር ለማረጋገጥ ነው"

የቀድሞው የኢሕአፓ እና የኢሕዲን ታጋይ አቶ ያሬድ ጥበቡ የሰልፉ አስፈላጊነት ላይ ጥያቄ አላቸው። አቶ ያሬድ በፌስቡክ ባሰፈሯት አጠር ያለች ፅሁፍ "ጉልበታችንን ተቋማት ግንባታ ላይ እንጂ ሰልፍ ላይ ማባከኑ ተገቢ መስሎ አይሰማኝም። የድጋፍ ሰልፍ በባህላችን ውስጥ ደድሮ የቆየውን አድርባይነት ከማጠናከር ውጪ የሚፈይደው መልካም የለውም" ሲሉ ሞግተዋል። 

ጸሐፊው አፈንዲ ሙተቂ ግን "ልብ ያለው ልብ ይበል!! ሰልፉ የተጠራበት ዓላማ አንድና አንድ ነው። ይኸውም ዶ/ር አቢይ ከህዝቡ የሚጠብቁት ድጋፍ እንደማይነፈጋቸው ለሁሉም አካላት ማሳወቅ ነው። ሰልፉ መካሄዱ ደግሞ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። ዛሬ ዶ/ር አቢይ የህዝቡን ድጋፍ በጠየቁበት ወቅት ከጎናቸው መሆናችንን ካላሳየናቸው የጀመሩትን የለውጥና የተሐድሶ እንቅስቃሴ በትጋት ለመቀጠል ወኔ ሊያጡ ይችላሉ" ባይናቸው።  

አሉላ ሰለሞን ፌስቡክ ላይ ባሰፈረው አጠር ያለ ፅሁፍ "ለመኾኑ የቅዳሜው ሠልፍ የድጋፍ ሠልፍ መኾኑ ቀርቶ ወደ ለየለት የጥላቻ: የዘረኝነት ብሎም የዘረፋ እና ውንብድና እንዲሁም የሠው ህይወት መጥፋት ቢለወጥ ተጠያቂው ማነው?" ብሎ ነበር። 

Äthiopien Vorbereitungen zur Kundgebung im Unterstützung zum Premierminister Abiy
ምስል DW/Y. Gebregziabeher

የቀድሞው የአዲስ ነገር ጋዜጣ አዘጋጅ ታምራት ነገራ "ጨዋነታችን መሳሪያችን!" በሚል ርዕስ ስር ባሰፈረው ሐተታ መልስ ለመስጠት ሞክሯል። ታምራት "ነገ ከምናነሳቸው መፈክሮቹም በላይ የሚነበበው ፣ ከምንለብሰው ቲሸርቱም በላይ ደምቆ የሚታየው የጨዋነት መጠናችን ነው። ለከተማችንም፣ ለሀገራችንም ፣ለምንደግፈው ለውጥም እኩይ የሚመኙልንም ፀጥ የምናስብልበት መሳሪያም ጨዋነታችን ብቻ ነው። ከዚህ በፊት ተጠቅመነዋል እንደገና በደንብ እንጠቀመው" ሲል መፍትሔው በተሳታፊዎቹ እጅ መሆኑን ጠቁሟል።

አሚጎ አሚጎ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ በበኩላቸው "በመሃል አገር አዲስ አበባ ሊደረግ በታቀደው ሰልፍ ላይ የፀጥታ ችግር ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት እዚህም እዚያም ሲነሳ አየሁ! አሃ! አዳሜ ለካ ቄሮና ፋኖ በጥይት እየረገፉ፣ የፖለቲካ እስረኞች አካላቸው እየጎደለ በሚከፍሉት መስዋዕትነት የዴሞክራሲ ፀኃይ ስትወጣ ለመሞቅ ቤትሽ ቁጭ ብለሽ ልትጠብቂ ኖሯል?" ሲሉ ነቅፈዋል። 
እሸቴ በቀለ