1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበረሰብ መስተጋብርን የመለሰዉ የኮሮና ገደብ  

ሐሙስ፣ ሰኔ 3 2013

የኮሮና በመዲናችን አዲስ አበባ በከፍተኛ መሰራጨቱ ከተነገረና ሁሉ ነገር ከተዘጋጋ ወዲህ የጎተራ እና የጎፋ ኮንደሚኒየም ነዋሪዎች ህጻን ወጣት ጎልማሳዉን ሁሉ ስፖርት ለጤንነት ብለዉ በአሰልጣኛቸዉ ሄኖክ ብርሃኑ አማካኝነት ማለዳ ይገናኛሉ። ጎረቤት ሆነን የማንተዋወቅ የነበርን አሁን በስፖርቱ አማካኝነት ኢትዮጵያዊ ባህላችን ተመለሰልን ይላሉ።

https://p.dw.com/p/3ujG8
Äthiopien Neue Bekanntschaften durch Umzug und Corona in Addis Abeba
ምስል Henk Birhanu/Privat

የኮሮና ዝዉዉር እገዳ አንድነታችን መልሶአል

አዲስ አበባ ጎተራ ኮንደሚኒየም የሚኖሩ ስፖርተኞች ሃሙስ ሰኔ 3 ቀን 2013 ዓ.ም ማለዳ ለጤንነት ለብሩህ አዕምሮ መጀመርያ ስፖርት ለመሥራት ወስነዉ ዱብ ዱብ ለማለት ሲነሱ፤ አንድ ቀን ቀደም ብሎ አሰልጣኛቸዉ ሄኖክ ብርሃኑ ነጭ ቲሸርት አድርጋችሁ እንድትመጡ፤ ቅዳሜ ደሞ ሰማያዊ ለብሰን እንገናኛለን ፤ ፈጣሪ እዝያ ያድርሰን ሲል በቴሌግራም ምን አይነት ቲሸርት ለብሰዉ እንደሚመጡ መልክት ይልክላቸዋል።  የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭት በመዲናችን አዲስ አበባ በከፍተኛ መሰራጨቱ ከተነገረና ሁሉ ነገር ከተዘጋጋ ወዲህ የጎተራ መብራት ኃይል ኮንደሚኒየም እና ጎፋ ኮንደሚኒየም ነዋሪዎች ህጻን ወጣት ጎልማሳዉን ሁሉ ጨምሮ ስፖርት ለጤንነት ብለዉ በአሰልጣኛቸዉ ሄኖክ ብርሃኑ አማካኝነት፤ በሳምንት ሦስት ቀን ማለዳ ይገናኛሉ።

Äthiopien Neue Bekanntschaften durch Umzug und Corona in Addis Abeba
ምስል Henk Birhanu/Privat

የፌስ-ቡክ መጠርያዬ ሄኖክ ሄንሪ ያለን የሰዉነት እንቅስቃሴ አሰልጣኙ ሄኖክ ብርኃኑ፤ የታዳጊ ብሔራዊ የሜዳ ቴኒስ ቡድን ተጫዋች ነበር። በምስራቅ አፍሪቃ ሃገራት ላይ በተካሄደ ዉድድርም አሸናፊ ሆኖ ለኢትዮጵያ ሦስት የብር አንድ የወርቅ ሜዳልያን አስገኝቶአል። በኮሮና ተኅዋሲ ምክንያት የሜዳ ቴኒስ መጫወቻዉ ስለተዘጋ በክረምትም ቢሆን ሜዳ ቴንስ መጫወት ስለማይቻል፤ ወደ ስፖርት እንቅስቃሴ አሰልጣኝነት መዛወሩን ተናግሮአል። ከዝያ በኋላ ነዉ በጎተራና በጎፋ ኮንደሜኔየም የሚኖሩ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማዘዉተር የጀመሩት። ሄኖክ ብርኃኑ ከኮሮና በፊት ግን በተለይ በአዲስ አበባ ታዋቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አስተማሪ በመሆኑም ይታወቃል። 

Äthiopien Neue Bekanntschaften durch Umzug und Corona in Addis Abeba
ምስል Henk Birhanu/Privat

ሄኖክ እንደሚለዉ ኮሮና በሃገራችን ብሎም በዓለማችን እጅግ ብዙ ሰዎችን ቢገድልም፤ በኮሮና ተኅዋሲ ስርጭት ሁሉ ነገር መዘጋጋት ሰበብ፤ ሳስቶ የነበረዉ ማኅበረሰባዊ ኑሮዉ መተሰሳሰቡ ዳግም አንሰራርቷል።  እድር ማኅበር፤ መጠያየቅ ሁሉ ጀምረናል። ቤተሰብ ሆነናል ሲል ተናግሮአል። በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ዉስጥ ያሉ ሰዎች በመቶ የሚቆጠሩ መሆኑን የነገረችን ወጣት ሄኖክ ብርሃኑ ስፖርት በሚያሠራበት ቡድን ዉስጥ የምትገኘዉ ቲና አረብ ናት ቲና እንደምትለዉ ከስፖርታዊ እንቅስቃሴዉ ባሻገር ማኅበራዊዉ መስተጋብሩ እጅግ ጠንካራ ነዉ። ስፖርት መስራቱን እንደጀመርን ይከብደን ነበር። አንዳንዴም እንቀር ነበር። አሁን ግን ለምደነዉ በደስታ ነዉ ስፖርትን በጋራ ለመስራት የምንሄደዉ። በየግዜዉ ቀነ-ቀጠሮዉን ጠብቀንም እንገናኛለን።

ሙሴ ሌላዉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አሰልጣኝ እና የእዚህ የስፖርት ማኅበር አባል ነዉ። ሙሴ እንደነገረን በኮደሚኒየም መንደር የሚኖረዉ ሕዝብ እጅግ ብዙ ነዉ። በአንድ የኮንደሚኒየም መንደር ከ 8 እስከ 10 ሺህ ሰዉ ይኖራል።

Äthiopien Neue Bekanntschaften durch Umzug und Corona in Addis Abeba
ምስል Henk Birhanu/Privat

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ባለሞያዉ ሄኖክ ብርኃኑ ብሎም ሙሴ፤ ጤናማ ዜጋን ለመፍጠር ስፖርት ቀዳሚ ስፍራ የሚሰጠዉ ነዉ ሲል ተናግሮአል። እያንዳንዱ ዜጋ በተለይ ወጣቱ ለሃገሩ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ነገርን ትቶ ማፍ እንዳለበትም ተናግሮአል። በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ከተማ በኮንደሚኒየም መኖርያ መንደር የስፖርት ማዘዉተርያ፤ ለህጻናት መጫወቻ ቦታ አለመኖሩ ነዋሪዉን ጎድቶታል። ሄኖክ እንደነገረን በጋራ ኮንዶሚኒየም መንደር የሚኖሩት ስፖርተኛዉ ማኅበር እንቅስቃሴዉን የሚያደርገዉ አስፓልት ላይ  ነዉ።  ስለሆነም  መንግሥት ይህን ታስቢ ቢያደረግ ሲል ስፖርተኞቹ ጠይቀዋል።

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን ተጭናችሁ እንድትከታተሉ እንጋብዛለን።   

 

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ