1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማትረሳው የሴቶች መብት ተሟጋች፤ ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 2 2012

ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በደቡባዊ የሀገረቱ ክፍል የሴት ልጅ ግርዛት እንዲቆም ከፍተኛ ተግባራትን ያከናወኑት ዶክተር ቦጋለች ገብሬ ከዚህ ዓለም የመለየታቸው ዜና ተሰምቷል። ዶ/ር ቦጋለች ባቋቋሙት መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት አማካኝነት የአዳጊ ሴቶች ሕይወት እንዳይጨልም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳደረጉ ይነገርላቸዋል።

https://p.dw.com/p/3StXu
Dr. Bogalech Gebre Frauenrechtsaktivistin und Gründerin von KMG
ምስል KMG Äthiopien

«የሴት ልጅ ግርዛት በተወለዱበት አካባቢ እንዲቆም ታግለዋል»

 ሴትን ልጅ ማስተማር ይጠቅማል ብሎ ከማያስብ ኅብረተሰብ 14 ልጆች ባሉበት ቤተሰብ ውስጥ የተወለዱት ዶክተር ቦጋለች በልጅነታቸው እስከ 4ኛ ክፍል ዘልቀው መማር መቻላቸውን ተናግረዋል። ሴት ልጅ ከዚያ አልፋ እንትማር በማያበረታታው ባህል ውስጥ ቢያድጉም በሚስዮናውያን ርዳታ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው አዲስ አበባ ላይ ባገኙት የነጻ ትምህርት ዕድል በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት ማጠናቀቅ እንደቻሉ ታሪካቸው ያስረዳል። በዚህ አላበቁም ፊዚዮሎጂ እና ማይክሮ ባዮሎጂን ለማጥናት የነፃ ትምህርት ዕድል አግኝተው ወደእስራኤል በመጓዝ በሂብሩ ዩኒቨርሲቲ ተማሩ። ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ወደሀገራቸው በመመለስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት እያገለገሉ ከቆዩ በኋላ በድጋሚ የትምህርት ዕድል ወደዩናይትድ ስቴትሱ ማሻቹስቴትስ ዩኑቨርሲቲ ጥገኛ ተሀዋሲያንን የሚመለከተውን የፓራሳይቶሊጂ ጥናታቸውን ማካሄዳቸውን ታሪካቸው ያስረዳል። ዶክተር ቦጋለች በተወለዱበት አካባቢ ያለውን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ጠንቅቀው ለማወቃቸው የራሳቸው ግለ ታሪክ ማሳያ ነው። በአካባቢያቸው አንድ ነገር ለኅብረተሰቡ ሠርተው ለማበርከት አልመው እንደነበር በአንድ ወቅት የገለፁት ዶ/ር ቦጋለች በተለይ ራሳቸው በ12 ዓመታቸው ያለፉበትን የሴት ልጅ ግርዛት የማስቆም እና ሌሎችን ከአስከፊው መዘዙ የማዳን ፍላጎታቸው ሚዛን ደፋ። እናም በተመሠረተባቸው ጥቂት ዓመታት በከንባታ እና ጠንባሮ አካባቢ ይንቀሳቀስ የነበረውን ከንባታ ሜንቲ ጌዝማን አቋቋሙ። እሳቸው እንደሚሉትን ይህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ባስከተለው መዘዝ ምክንያት እህታቸውን በወሊድ ወቅት አጥተዋል። ይህም እንዲህ ባለው ድርጊት ምክንያት ለስቃይ የሚዳረገውን የሴቶች ሕይወት እንዴት መታደግ እችላለሁ የሚል ስሜት እንዳሳደረባቸው በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲናገሩ ተደምጠዋል። አሜሪካን ሀገር በነበራቸው የዩኒቨርሲቲ ቆይታ በዚህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ምክንያት ሴቶች የሚያልፉበት ስቃይ እንዲሁም የሚገጥማቸው ችግርን የሚያስረዱ መረጃዎችን ማንበባቸውን ይህን ተግባር አጥበቀው በመቃወም ሌሎችንም በማስተማር መለወጥ እንዳለባቸው ለመወሰን አብቅቷቸዋል። ይህ ድርጊት በሃይማኖት ተቀባይነት እንደሌለው፤ ባህልነቱም ከየት መጣ ቢባል እንኳ እንደማይታወቅ ዶክተር ቦጋለች ተናግረዋል።

እሳቸው ያቋቋሙት ይህን ጎጂ  ልማዳዊ  ድርጊት የሚቃወመው ድርጅታቸው ሥራ ከመጀመሩ በፊት ከንባታ ውስጥ የዚህ ሰለባ ያልሆነች ሴት አልነበረችም። ከዓመታት የማስተማር እና ኅብረተሰቡን የማንቃት ጥረት በኋላ ግን በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሴቶችን ከዚህ ማትረፉ በስኬት ተመዝግቦለታል። በአንድ ኅብረተሰብ ውስጥ እጅግ ሥር የሰደደን ልማድ ለማስቆም የሚደረግ ጥረት በአንድ ጀንበር መከወን አዳጋች መሆኑ ይታወቃል። በባህል ስም በሴት ልጅ የመዋለጃ አካል ላይ የሚደረገው ትልተላ መዘዙ ዘርፈ ብዙ መሆኑን በማስተማር የተለወጡትን በዚያው ኅብረተሰብ ውስጥ ትዳር መስርተው ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ ማድረጉ ብዙ መሰናክሎች እንደነበሩበትም ዶክተር ቦጋለች ገልፀውልናል።

የሴት ልጅን ግርዛት ለማስቆም የግንዛቤ ማስጨበጫው ሥራ የተጀመረበት አካባቢ ላይ የተገኘው ለውጥ አበረታች በመሆኑ ከንባታ ሜንቲ ጌዝማ ሥራውን ወደሌሎች አካባቢ አስፍቷል። ኅብረተሰቡን የማሳወቁ ተግባር እየተስፋፋ በመሄዱም ውጤቱ አዎንታዊ እንደሆነም አጫውተውን ነበር። ይህ ዶክተር ቦጋለች ገብሬ ከእህታቸው ጋር በመተባበር የመሠረቱት ድርጅት የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም ከሚያደርገው ጥረት ባለፈ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችንም ለመከላከል እየሠራ ይገኛል። የሥራ ባልደረባቸው እና የድርጅቱ የፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ መንበረ ዘነበ ገብረ ሚካኤል ቦጌ እያሉ የሚጠሯቸው ዶክተር ቦጋለች ለማኅበረሰባቸው የኖሩ ይሏቸዋል።

Dr. Bogalech Gebre Frauenrechtsaktivistin und Gründerin von KMG
ምስል KMG Äthiopien

እንደባልደረባ ሲመለከቷቸው ደከመኝ ሰለቸኝ የማይሉ እንደነበሩ የገለጿቸው ዶክተር ቦጋለች የጀመሩትን ተግባር የድርጅቱ ባልደረቦች የማስቀጠል ቁርጠኝነትም እንዳላቸውም አመልክተዋል።

ዶክተር ቦጋለች ተወልደው ባደጉበት አካባቢ የመሰል ሴቶችን ሕይወት ለመለወጥ የወጡበት ኅብረተሰብንም ጠጋ ብለው የማስተማር ተግባራትን በማከናወናቸው የብዙዎችን ትኩረት ስበው ቆይተዋል። ይህም ለተለያዩ ሽልማቶች እና እውቅናዎች አብቅቷቸዋል። በጎርጎሪዮሳዊው 2005፤ የሰሜን ደቡብ ሽልማት በ2007 ለዓለም አቀፍ ጤና እና የሰብዓዊ መብት ጥረታቸው የጆናታን ማን ሽልማት፤ በ2013 ዓ,ም ደግሞ ብራስልስ ላይ በፖለቲካው መስክ እውቅና ያለውን የ«ንጉሥ ቦዷንን የአፍሪቃ ልማት ሽልማት አግኝተዋል። ከዚህም ሌላ በጎርጎሪዮሳዊው 2014 ባለ መልካም ምግባር ሴት የሚል እውቅና ተሰጥቷቸዋል። ኢትዮጵያ ላይም በ2008 ዓ,ም የዓመቱ በጎ ሰው ተብለው ተሸልመዋል። ዶክተር ቦጋለች ይህን ብቻ አይደለም ያከናወኑት የእናቶች እና ማሕፀን ሆስፒታል ከንባታ ላይ እንዲሠራ ከፍተኛ አስተዋፅኦም አድርገዋል። በሚሊየኖች የሚቆጠር ችግኝ በማስተከልም የአካባቢውን ስነምህዳር ለመጠበቅ ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጋቸው ይነገርላቸዋል። ዛሬ  የከንባታ ሴቶች ራስ አገዝ ድርጅቱ ከመቶ አርባ በላይ ሠራተኞች እንዳሉት ነው የሚነገረው። ከስድስት እስከ ስምንት ሺህ የሚደርሱ የበጎ ፈቃድ ተባባሪዎችም አስባስቦ የተነሳለትን ዓላማ በከንባታ እና አቅራቢያው ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አካባቢዎች አስፋፍቶ እየሠራ ይገኛል።

ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት የዓለም የጤና ድርጅት ያወጣው መረጃ በ30 ሃገራት 200 ሚሊየን የሚሆኑ ሴቶች በዚህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ውስጥ ማለፋቸውን ያመለክታል። በየዓመቱን 3 ሚሊየን  ገደማ አዳጊ ሴት ልጆች ለዚሁ ድርጊት የተጋለጡ መሆናቸውንም ይገልጻል። ኢትዮጵያ ውስጥ 74 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች እና አዳጊ ልጃገረዶች የዚህ ጎጂ ድርጊት ሰለባ መሆናቸውን ጥናቶች ያሳያሉ። ለሴቶች መብት እና ሰውአዊ ክብር ለረዥም ዓመታት ሲታገሉ የነበሩት ዶክተር ቦጋለች ገብሬ ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩም ሥራቸው ግን ሕይወታቸውን በለወጡላቸው ወገኖች ዘንድ ሲገልጻቸው ይኖራል። ሥርዓተ ቀብራቸው በመጪው ሳምንት እንደሚከናወን ይጠበቃል። ነፍስ ይማር! አድማጮች ከረዥም በአጭሩ ራሳቸው ተምረው ባገኙት ዕውቀት ወገኖቻቸውን ለመርዳት ሲጥሩ የኖሩትን ድንቅ ኢትዮጵያዊት ሴት የዘከረው መሰናዶ በዚሁ አበቃ።

ሸዋዬ ለገሠ 

አዜብ ታደሰ