1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የማሽን አከራዮች ሥራ በኢትዮጵያ ገበያ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 15 2011

ኢትዮጵያ የተለያዩ ሸቀጦች እና ቁሳቁሶች የሚያመርቱ ኩባንያዎች የሚያስፈልጋቸውን ግዙፍ ማሽኖች በኪራይ ለሚያቀርብ ኩባንያ የመጀመሪያውን ፈቃድ ሰጥታለች። ኢትዮ-ሊዝ የተባለው ይኸው ኩባንያ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ብቻ በ200 ሚሊዮን ዶላር የተለያዩ ቁሳቁሶች ለኢትዮጵያ ገበያ በኪራይ እንደሚያቀርብ አስታውቋል። 

https://p.dw.com/p/3OHgu
Äthiopien Eröffnung der ITACA Textilfabrik in Tigray
ምስል DW/M. Haileselassie

የማሽን አከራዮች ሥራ በኢትዮጵያ ገበያ

ኢትዮ-ሊዝ የተባለ ኩባንያ ግዙፍ ማሽኖችን በኪራይ ለገበያ ለማቅረብ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ተሰጥቶታል። ኩባንያው ትራክተሮች፣ የጥልቅ ጉድጓድ መቆፈሪያ ማሽኖች እና ለሕክምና ምርመራ የሚያገለግሉ የኤም.አር.አይ. ስካነሮች (MRI scanners) በኪራይ ለኢትዮጵያ ገበያ እንደሚያቀርብ ሮይተርስ ዘግቧል። የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ግሩም ተስፋዬ እንዳሉት በሁለት ዓመት ውስጥ 200 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ መሳሪያዎች በኪራይ ለኢትዮጵያ ገበያ ለማቅረብ ተዘጋጅተዋል። 
ኢትዮ-ሊዝ መቀመጫውን በኒው ዮርክ ያደረገው አፍሪካ አሴት ፋይናንስ የተባለ የመሳሪያ አከራይ ኩባንያ ንብረት ነው።  የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍራንስ ቫን ሻይክ በኢትዮጵያ በርካታ ኩባንያዎች የሚፈልጓቸውን መሳሪያዎች የማግኘት ፈተና እንደገጠማቸው መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።  ዋና ሥራ አስፈፃሚው “እያንዳንዱ በኢትዮጵያ የሚገኝ ፋብሪካ የመሳሪያ እጥረት ወይም ሌላ እክል የሚያካሒዱትን ግንባታ አሊያም ሌላ ሥራ እያዘገየባቸው እንደሆነ ይናገራሉ” ብለዋል።  ኩባንያው ከአንድ ዓመት የገበያ ጥናት እና ለሁለት ዓመታት ገደማ ከባለሥልጣናቱ ጋር ከተደረገ ድርድር በኋላ በሐምሌ ወር ፈቃድ ማግኘቱን በድረ-ገጹ ገልጿል። ከኩባንያው ሰባት የቦርድ አባላት መካከል የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ግርማ ዋቄ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ኃላፊ አቶ ጋብሬል ንጋቱ ይገኙበታል።
ኢትዮጵያ ኢትዮ-ሊዝ ያቀደው አይነት የማሽኖች ኪራይ የሚያቀርቡ አምስት ኩባንያዎች አሏት። አዲስ ካፒታል ጉድስ ፋይናንስ በአዲስ አበባ፤ ደቡብ ካፒታል ጉድስ በደቡብ፤ ካዛ ካፒታል ጉድስ በትግራይ፤ ኦሮሚያ ካፒታል ጉድስ በኦሮሚያ እንዲሁም ዋልያ ካፒታል ጉድስ በአማራ ክልል ሊሰሩ የተቋቋሙ ናቸው። ሌሎቹ ክልሎችም ሆኑ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መሰል ተቋማት የላቸውም። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ እንደሚሉት ሥራው ጫን ያለ ገንዘብ የሚያስፈልገው በመሆኑ የግል ባለሐብቶች ሳይደፍሩት ቆይተዋል። 

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ