1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ጥቅምት 25 2015

በጦርነት የተገዱ አራት ከተሞችና አካባቢዎቻቸዉ ዳግም የኤሌክትሪክ መብራት ማግኘታቸዉ፣ የጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ የደቡብ ኢትዮጵያ ጉብኝትና የሰጡት አስተያየት ከሳምቱ ዘገቦች የጎሉት ናቸዉ።ይሁንና ባለፈዉ ሮብ ማታ ከወደ ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ የተማዉ ዜና ከቀዳሚዎቹ ሁሉ በልጦ የአብዛኛዉን ኢትዮጵያ ቀልብ የሳበ መስሏል።

https://p.dw.com/p/4J2Tu
Äthiopien Ministerpräsident Abiy Ahemed im Süden
ምስል Southern Ethiopian regional office

የሰላም ስምምነት፣ የጠቅላይ ሚንስትሩ መልዕክትና መብራት ለአማራ ከተሞች

ለዛሬዉ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝ ዝግጅታችን ሳምንቱን በተዘገቡ 3 ርዕሶች ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን ቃርመናል። አብራችሁኝ ቆዩ።በአማራ ክልል በጦርነት የተገዱ አራት ከተሞችና አካባቢዎቻቸዉ ዳግም የኤሌክትሪክ መብራት ማግኘታቸዉ፣ የጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ የደቡብ ኢትዮጵያ ጉብኝትና የሰጡት አስተያየት ከሳምቱ ዘገቦች የጎሉት ናቸዉ።ይሁንና ባለፈዉ ሮብ ማታ ከወደ ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ የተማዉ ዜና ከቀዳሚዎቹ ሁሉ በልጦ የአብዛኛዉን ኢትዮጵያ ቀልብ የሳበ መስሏል።

የኢትዮጵያ የፌደራዊ መንግስትና ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ተወካዮች ከዘጠኝ ቀናት ድርድር በኋላ የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት ከኢትዮጵያ አልፎ የአብዛኛዎቹን የዓለም ትላልቅ መገናኛ ዘዴዎች ትኩረት የሳበ፣ በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎችም ብዙ አስተያየት የተሰጠበት ርዕስ ነዉ።የዕለቱ ቅኝታችን የመጀመሪያ ርዕሠ አድርገነዋል።

እንደተከታተልነዉ «ግጭትን በዘላቂነት የማስወገድ ስምምነት» የሚል ጥቅል ስያሜ የተሰጠዉ ስምምነት ባንዳዶች ግምት ግማሽ ሚሊዮን ሰዉ የፈጀዉን ጦርነት ለማስቆም ሁነኛ ዉል ነዉ።በስምምነቱ ከተጠቀሱት ግጭት ይቆማል፣  ሕወሓት በ30 ቀናት ዉስጥ ትጥቁን ይፈታል።የኢትዮጵያ መንግስት በጦርነት ለተጎዳዉ አካባቢ መሰረታዊ አገልግሎቶችን መስጠት ይጀምራል።ለችግረኛዉ ያለምንም ገደብ ርዳታ ይደርሳል የሚሉት የጎሉት ናቸዉ።

 

ጂጂ በፌስ ቡክ «ለመጀመሪያ ግዜ ጥሩ ዜና ስስማ በዚህ በጦርነት ሰአት አላህ ያስማማቸው በተግባር ስናየው ደግሞ ደስ ይላል» ጂጂ ናት እንዲሕ ባይዋ።መሐመድ ያሲንም በፌስ ቡክ---«በጣም ጥሩ ዜና ነው» ይላል---- «የሰላም የፍቅር፣ የአንድነት ያድርገው ለሁለታችሁም» አከለ።ቴዎድሮስ አሰፋ ግን ምዕራባዉያንን ይወቅሳል።ምክንያት ግን የለዉም ብቻ «ምእራባውያን ካወደሱት ችግር አለ ማለት ነው» ይላል በደፈናዉ።ትዝብቱ ይበልጣል----አድረን እንይ ዓይነት ባይ ነዉ----«ዝርዝሩን እናየዋለን!!ምን ማለት ነው? ይህ ድርድር ጊዜ መግዣ ነው ወይስ---ዘላቂ ነውን?» ይላል በፌስ ቡክ።ዋል አደር ብሎ ማየቱ ክፋት የለዉም ግን ይሕ ድርድር ሳይሆን ስምምነት ነዉ።

አቶ ሪድዋን አሕመድና አቶ ጌታቸዉ ረዳ ሰነድ ሲለዋወጡ
አቶ ሪድዋን አሕመድና አቶ ጌታቸዉ ረዳ ሰነድ ሲለዋወጡምስል SIPHIWE SIBEKO/REUTERS

 

ዑም ፈራሕን (ቋሚ አድማጫችን ናት) በፌስ ቡክ «ቃል የለኝም» ትላለች።ፀሎት ብጤ አክላበታለች«አላሕ ዕዉነት ያድርገዉ» ብላ።----ሱመያ አሕመድ «አሁን ኢትዮጲያውያን በሙሉ ትጥቅ መፍታት አለባቸዉ ሰላም ናፍቆናል። ሰው ሞተ የሚል ዜና ሰልችቶናል። ሁሉም ዜጋ በየትም ቦታ ተቀሳቅሶ ሰርቶ መብላት አለበት» ይላል በፌስ ቡክ።ሡመያ አሕመድ

 

ምሕረት ማለዳ-----በትዊተር ፍትሕ ይከበር ዓይነት ባይ ነዉ።«በሀገር እና በምስኪኑ ህዝብ ደም እንደ መቀለድ ነው።ፍርድ ለባለጊዜዎች፣ ፍትህ ለተፈናቀሉእና በጦርነቱ ለተጎዱ ፣ካሳ በጦርነቱ ህይወታቸውን እና አካላቸውን ለገበሩ ዘመዶቻችን» የምሕረት ማለዳ የትዊተር አስተያየት ነዉ።ባርኮት----እሱም በትዊተር »የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላም ይፈልጋል።» ይላል።«አሁን ስለሰላምና ሰላም ብቻ ነው መናገር ያለብን። በሙሉ ልብ አማራን አፋርን አና ትግራይን መገንባት ያስፈልጋል።»

 

ረዑፍ ዑስማን የባርኮትን አስተያየት በሌላ አባል ደግመዉ በፌስ ቡክ እና በእንግሊዝኛ «ከጦርነት ሊያተርፍ የሚችል ማንም የለም» ብሎ----ሲራጅ ጣሒር ግን በነረዑፍ አባባል የሚስማማ አይመስልም።ከጦርነት አትራፊ አለ ባይነዉ----«በመጨረሻም» ይላል ሲራጅ እንደ ግጥም  ቤት በሚመታ የፌስ ቡክ መልዕክቱ----«በመጨረሻም፣ ሕዝብ ያልቃል።ጦርነት ያበቃል።ንጉስ ይታረቃል።» ሲራጅ ጣሒር ነዉ-ገጣሚዉ (ግጥም ከሆነ)

 

ወደ ሌላዉ ርዕስ እንለፍ። ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ባለፈዉ ማክሰኞ ደቡብ ኢትዮጵያ በተለይም ጋሞ ጎፋን ሲጎበኙ አቀባበል ላደረገላቸዉ ሕዝብ ባሰሙት ንግግር «በጦርነት የተገኘዉ ድል በሰላም ይደገማል።በሰላም የተገኘዉ ደግሞ በብልፅግና» ማለታቸዉ ተዘገቦ ነበር።ኢትዮጵያ አማራ---የሚል የፌስ ቡክ ስም ያለዉ ወይም ያላት አስተያየት ሰጪ «ጀግኔ» በማለት ጠቅላይ ሚንስትሩን ያደንቃል ወይም ታደንቃለች።«ዛሬ ዓለምን ነዉ ያሸነፍከዉ» ቀጠለ ወይም ቀጠለች ኢትዮጵያ አማራ።በሐይል ቤቤቶ ግን ጠቅላይ ሚንስትሩ ከዚሕ ቀደም ብለዉታል ያለዉን ይጠቅሳል እና ይጠይቃልም።«ይህ አሸባሪ ለፍርድ ካልቀረበ ለድርድር አንቀመጥም ያልከንስ?»

ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ በጋሞ ጎፋ ጉብ
ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ በጋሞ ጎፋ ጉብኝትምስል Southern Ethiopian regional office

 

ይርጋ ፍሰሐም ይጠይቃል በፌስ ቡክ እና ሌላ እና ተመሳሳይ ግን ብዙ ጥያቄ «በጦር የትኛው ድል ነው የተገኘው? ህዝበ ስላለቀ? ስለተፈናቀለ ወይስ ስለ ተራበ? ለማንኛውም ኣሁንም ኣልመሸም በጦርነት ማንም ኣሸናፊ ኣይኖርም እርሰበርስ መተላለቅ ካልሆነ » ይርጋ ፍሰሐ በዚሕ አላበቃም።

 

ሲራጅ ጣሒር በጠቅላይ ሚንስትሩ አስተያየት የተገረመ ይመስላል። ግን ፖለቲካን ነዉ የታዘበዉ። «አይ ፖለቲካ ለዚሕ ነው ያ ሁሉ ወጣት የረገፈው!! ድንቄም ሰምምነት ግጭት ለማስቆም ደቡብ አፍሪካ መሄድ አይጠበቅም ነበር። መንግስት ግጭት እናቁም በማለት ስንት ግዜ ነው ጉጀሌው ህወሓትን የጠየቀው? እያለ ይዘረዝራል ሲራጅ ጣሒር።

ወደ ሶስተኛዉ ርዕስ እንለፍ።አማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ይደረግ በነበረዉ ጦርነት ምክንያት መብራት ተቋርጦባቸው የነበሩ የአላማጣ፣ የዋጃ፣የቆቦና የላሊበላ ከተሞች ሰሞን የኤሌክትሪክ ብርሐን ማግኘታቸዉን የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ባለስልጣናት አስታዉቀዋል።አብዛኞቹ አካባቢዎች ኤሌክትሪክ መብራት ከተቋረጠባቸዉ አንድ ዓመት ከአራት ወር በልጧቸዋል።ከተሞቹ ሰሞኑን መብራት አገኙ መባሉንም የአንዳድ ከተማ ነዋሪዎች «ዕዉነት» ብለዉ ሲያረጋግጡ፣ ከተቀሩት ገሚሱ ካጭር ጊዜ በኋላ መልሶ ተቋርጧል ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ዜናዉ ባጠቃላይ ሐሰት ነዉ ይላሉ።

ሊዲያ ሐበሻ (ቋሚ አድማጫችን ናት) በፌስ ቡክ----«ክብር ለባለሙያዎቹ» አለች።«እጃችሁ ይባረክ» አከለች።መቅደስ መኮንን ግን ---«አትዋሹ» አለች ቅጭም ባለ ቃል።«ቆቦ እስካሁን ድረስ መብራት አልተለቀቀም።»ቆቦዎች----እባካችሁ እዉነቱን ንገሩን---መብራት አለ የለም? ጥላሁን ነጋ በፌስ ቡክ---ዕቅጩን መልስ የለዉም ግን አለ በፌስ ቡክ---«የሚወራዉ ሌላ፣ ተግባሩ ሌላ»----መዩ መየ  (ተባዕት ይመስለናል)---«ጀግኖቹ የኢተዮጰያ ልጆች አነዲህ ናቸው ጁንተው ያፈርሳል አኛ አነሰራለን ፈጣሪ ፍርዱን ላንተ!!» ምልጃዉን በሁለት ቃል አጋኖ አሸብርቆታል።

ኑራ መሐመድ ጣሒር «ወደ ትግረይም ይከፈት» ትላለች በፌስ ቡክ።በሰላም ስምምነቱ መሰረት ሁሉም ጋ ይከፈታል ብለን ተስፋ እናድርግ።አልታዬ ተኮላ ግን ጥያቄ አለዉ «ምዕራባውያን አልሰሙም» የምትል ጥያቄ።አበቃን።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ