1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ግንቦት 26 2014

የኤርትራና የሕዋሓት ግጭት፣ «ዘመቻ» የመሰሉ እስራቶች፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወቀሳ፣የሰላም ጥሪ፣ የአፍሪቃ ሕብረትና የዩናይትድ ስቴትስ ዲፕሎማቶች የሰላም ጥረትና ሹመት የጎሉት ርዕሶች ነበሩ።በየርዕሶቹ ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች መረን ከለቀቀ የጋጠወጦች ስድብ የፀዱትን መልዕክቶች ቃርመናል

https://p.dw.com/p/4CD9i
Symbolbild I BigTech I Social Media
ምስል Nicolas Economou/NurPhoto/picture alliance

ዘመቻ የመሰለዉ እስራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ፣ የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልዕክተኞች ጥረትና ሹመት

 

ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።ኢትዮጵያዉያን ግጭት፣እስራት፣ የፖለቲካ ዉዝግብ፣ የሰላም ጥሪና የዲፕሎማሲ ጥረትን  የየዕለት ዜና ርዕሶቻችን ካደርን ዓመታት ተቆጠሩ።ያገባደድነዉ ሳምንትም የተለየ አልነበረም።የኤርትራና የሕዋሓት ግጭት፣ «ዘመቻ» የመሰሉ እስራቶች፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወቀሳ፣የሰላም ጥሪ፣ የአፍሪቃ ሕብረትና የዩናይትድ ስቴትስ ዲፕሎማቶች የሰላም ጥረትና ሹመት የጎሉት ርዕሶች ነበሩ።በየርዕሶቹ ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች መረን ከለቀቀ የጋጠወጦች ስድብ የፀዱትን መልዕክቶች ቃርመናል።አብራቹሁን ቆዩ።

                                    

የኤርትራ ጦር ሺራሮ ከተማን በከባድ ጦር መሳሪያ መደብደቡንና የሕወሓት ጦር አፀፋ መሰንዘሩን የሕወሓት ባለስልጣናት ያስታወቁት በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ነበር።በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ባለስልጣናት በየፊናቸዉ የሰጡትን አስተያየት ዋቢ ጠቅሰን ዘግበናል።በዘገቦቹ ላይ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች ፅፈዋል።ሁሉም ግን ዶቸ ቬለን ጨምሮ አንዱን ወይም ሌላዉን ተፋላሚ ኃይል ከመሳደብና ማበሻቀጥ ያለፈ «አስተያየት» ሊባል የሚችል  መልዕክት ስለሌለዉ ዘልለነዋል።

የኢትዮጵያ የፌደራልና የአማራ ክልል መንግስታት «ዘመቻ» በመሰለ እርምጃ በአብዛኛዉ አዲስ አበባና አማራ ክልል የሚኖሩና የሚሰሩ ጋዜጠኞችን፣ የፀጥታ አስከባሪ ባልደረቦችንና የፋኖ ታጣቂዎችን አስረዋል።

የፌደራል ፖሊስና የአማራ ክልላዊ መንግስት በየፊናቸዉ በሰጡት መግለጫ የታሰሩት ሰዎች «ሰላምን ለማደፍረስ ሲንቀሳቀሱ ነበሩ ተብለዉ የተጠረጠሩ ናቸዉ» ብለዋል።እስከ ትናንት ድረስ ከ5500 እስከ 6000 የሚደርሱ ሰዎች መታሰራቸዉ ተዘግቧል። እስራቱን የሰብአዊና የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቾች ተቃዉመዉታል።እስረኞች ባስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ እየጠየቁም ነዉ።

Oluseguni Obasanjo, President von Nigeria
ምስል dpa

Mahir Usri Yusra  ግን እስራቱ «ገና ይቀጥላል።» ይላል- በፌስ ቡክ።  «ህግ ማስከበሩ ከጎጀም ወደ ጎንደርም ጀባ ማለት ኣለበት።» Tedor Myadrasha ባንፃሩ አንዲት ቃል መረጠ «አፈና» የምትል።በፈቃዱ ምስራቅ ይስቃል-በፌስ ቡክ።የምፀት የመሰለ ሳቅ።«ሃሃሃሃሃሃ» ሳቁን «ነውረኛ አገዛዝ።» ብሎ አሳረገ።

ጨለቃ ጎለልሻ መንግስትን «አበጀሕ» ዓይነት ይላል ወይም ትላለች።«እሰይ አሁን ገና መንግስት መሠላችሁ። ያሁሉ ጥይት ፀጥ እረጭ አለ። የመንደር ዱርየ አሁንም አልፎ አልፎ መሳሪያ የያዙ ሠወች አሉ እነሡንም በነካ እጃችሁ መላ በሉልን።» Sahlu Tekle ለመንግስት ባለስልጣናት በመሰለ መልዕክቱ «እናንተስ በየትኛው ሕግ ነው የምትጠየቁት?» ብሎ ይጠይቃል በፌስ ቡክ።

Teshome Worcho «አቦ ይመቻቸው» ይላል።በዚሕ አላበቃም  «እንዲያ ነው እንጂ።  እንዲያውም ህግ ማስከበሩን በድሮንና በታንክ ቢያረጉት አሪፍ ነበር።» እያለ ቀጠለ።እኛ በዚሕ ርዕስ ላይ እዚሕ ላይ እናብቃ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ሕግና ሥርዓት እንዲያስከብር፣ የዘፈቀደ የመሰለዉ እስራት እንዲቆም፣ተፋላሚ ኃይላት ሰላም እንዲያወርዱና የታሰበዉ ብሔራዊ ምክክር ሁሉን እንዲያሳትፍ የተለያዩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራና በተናጥል ጠይቀዋል፤ መንግስትን ወቅሰዋል።

የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) እና እናት ፓርቲ በጋራ፣ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ሴት ፖለቲከኞች የጋራ ጥምረት በተናጥል የሰጧቸዉ መግለጫዎች ለሳምንቱ ተጠቃሾች ናቸዉ።

Äthiopien | Gizachew Muluneh
ምስል Alemenew Mekonnen/DW

Hussein Afar በፌስ ቡክ የፓርቲዎችን ጥሪ፣ወቀሳና ማሳሰቢያ «ወቅቱን ያገናዘበ» ይለዋል። Eluzay Elias Mis በተለይ ሶስቱን ፓርቲዎች «ሶስቱንም አላዉቃቸዉም» ብላቸዉ እርፍ። የTariku Hamesso አስተያየትም ከኤሉዛይ ጋር ተመሳይ ነዉ።«የት ያሉ ናቸዉ?» ይጠይቃል ታሪኩ።

Minilu Ayale ግን በነ ታሪኩ አስተያየት ቆጣ ያለ ይመስላል «ወደድክም ጠላህም የሶስቱም ፓርቲዎች መግለጫ ወቅቱን ያገናዘበና ህዝባዊ ሮሮን የዋጀ መግለጫ ነው!!!» ይላል።በሶስት ትዕምርተ አጋኖ ባኮሸዉ አስተያየቱ።Sibira Legesse ተቃራኒዉን ትላለች።«ፋኖ ለምን ተነካ ማለታቸዉ ነዉ።የትነበሩ ትግራይ ላይ ሲዘመት?የትነበሩ ኦሮሚያ ላይ ሲዘመት? ጠየቀች፣ጠየቀችና ባጓጉል ቃላት አሳረገች።አንደግመዉም።

Nur Salih የሴት ፖለቲከኞች ጥምረት መሪዎችን መግለጫ ይደግፋል «ሐሳባችሁ አይከፋም።» ብሎ። ግን እዚያዉ በዚያዉ ይተቻል-በጥያቄ «አሰከ ዛሬ ያ ሁሉ ሲሆን የት ነበሩ? ደግሞ ይህ መግለጫ በዚህ ወቅት መሰጠት ለምን ፈለጉ?»

Negatu Aragaw «ጅብ ከሄደ ውሻ ጮህ ሆንባችሁ። የሚሰማችሁ መንግሥት የለም እዳትታፈኑ» ሴት ፖለቲከኞቹን መምከሩ ነዉ በፌስ ቡክ።

የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ካነሳቸዉ ጉዳዮች አንዱ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሊደረግ በታቀደዉ ብሔራዊ ምክክር ላይ ፓርቲዉ እንደማይሳተፍ ማረጋገጡ ነዉ።ዋቆ ጉቱ (ይሕን ስም ታስታዉሱታላችሁ?) ብቻ የፌስ ቡኩ ዋቆ የአፋሩን ፓርቲ አቋምን «ትክክል» ብሎታል።ምክንያቱ «ሰዎች ሰላጨበጨቡ ብቻ ማጨብጨብ ምን ያህል እንደሚጎዳ በአቡሽ  አይተናል!!!!» አራት ቃል አጋኖ ደርድሮበታል።

Teddy Dekama ገና ይጠይቃል።«ብሔራዊ ምክክር እየተሰራበት ነዉ እንዴ?» ብሎ። Fikeru Bekele ለነ ቴዲ መልስ አልሰጠም ግን አለ፣- «ሽሽት።»

                                          

ዩናይትድ ስቴትስ ለአፍሪቃ ቀንድ አዲስ ልዩ መልዕክተኛ ሾማለች።አዲሱ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር ይባላሉ።ልዕለ ኃሊቱ ሐገር ለአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ስትሾም በ13 ወራት ዉስጥ ሐመር ሶስተኛዉ ናቸዉ።ሁለቱ ሥልጣኑን እየያዙ ለቅቀዋል።

Dinku Damene በፌስ ቡክ «ምን ልትሆን?» ጠየቀ አሜሪካን። Alemu Daniel ደግሞ፣ «አይ ጭራሽ ሐመር ላከችብን? ቅኔው አፈርሳችኋለሁ መሆኑ ነው?» እያለ ጠየቀ።መልስ የለንም «ሐመር» ማለት ግን መዶሻ ነዉ። Kanbata Durame «ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም» ባይ ነዉ። Anes Geberil ግን ብዙ ያሳሰባት ወይም ያሳሰበዉ የአሜሪካኖች ዓላማ፣ የዲፕሎማቱ ተልዕኮ፣ ልምድና ኃላፊነት ዓይደለም፤የሰዉዬዉ መልክ እንጂ  «ፊቱ ግን» አለች ወይም አለ አነስ እና አስተያየቱን ጨረሰች ወይም ጨረሰ።

Äthiopien Addis Abeba |  Tefera Mamo
ምስል Solomon Muchie/DW

ዩናይትድ ስቴትስ ለአፍሪቃ ቀንድ አዲስ ልዩ መልዕክተኛ መሾሟ በተነገረ ማግስት ትናንት በአፍሪቃ ቀንድ የአፍሪቃ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦሌሴጎን አባሳንጆ የአዲስ አበባና የመቀሌ መሪዎችን ለመሸምገል የጀመሩት ጥረት አዝጋሚ ግን በጎና ተገቢ ለዉጥ ማሳየቱን አስታዉቀዋል።

ኡም ፈራሀን «የመጣውን ለውጥ ባናውቅም (ባናይም)ጦርነት በቃ» አለች በፌስ ቡክ። Zed Zanks ደግሞ «ሰላም ለሁሉም»ትላለች ወይም ይላል።Ku Ka ይፀልያል ወይም ትፀልያለች። «ኦባሳንጆዬ ጥረትህ እንዲሳካ ጸሎቴ ነው።» እያለ ወይም እያለች።የሰዉ ነገር ብቻ፣- በሚል የፌስ ቡክ ስም የሚጠራዉ አስተያየት ሰጪ ግን ጥያቄ ለበስ ትዝብት አለዉ «ኦባሳንጆ፣ ለምን መጀመሪያ ከቦኮ ሐራምጋ አይደራደርም ?» የሚል።ፅጌ ዘ አብ እንዲሕ አለ «ቸር ያሰማን ኢትዮጵያ» ምኞቱን እንመኝ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ መልካም የሳምንት መጨረሻ።

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ