1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ሰኔ 18 2013

ትግራይ ክልል ከርዕሰ ከተማ መቀሌ ወጣ ብሎ ዶግዋ ተንቤን ወረዳ ቶጎጋ በተበለ ሥፍራ የኢትዮጵያ ጦር አንድ የገበያ ሥፍራን በተዋጊ ጄት በመደብደቡ ሠላማዊ ሰዎች ተገደሉ፤ አልተገደሉ የሚለዉ ፅንፍ የተጠጋ ተቃራኒ ክርክርም ወትሮም በአብዛኛዉ በግል ፍላጎትና ስሜት

https://p.dw.com/p/3vZYE
Parlamentswahl in Äthiopien 2021
ምስል T. Dinssa/DW

በምርጫዉ ሒደትና በቶጎጋ መደብደብ ላይ የተሰጡ አስተያየቶች

ባለፈዉ ሰኞ በአብዛኛዉ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተደረገዉ የብሔራዊና የክልል ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ፣ የድምፅ አሰጣጥ ሒደቱና የመጀመሪያ ደረጃ ዉጤቱ የኢትዮጵያን ጉዳይ በሚዘግቡ መገናኛ ዘዴዎች ዘንድ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ነበር።የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተከታታዮችም ሥለ ምርጫዉ፣ ሒደትና የመጀመመሪያ ደረጃ ዉጤት በሚያወሱ ዘገቦች ላይ የየራሳቸዉን አስተያየት ሰጥተዋል።
ትግራይ ክልል ከርዕሰ ከተማ መቀሌ ወጣ ብሎ ዶግዋ ተንቤን ወረዳ ቶጎጋ በተበለ ሥፍራ የኢትዮጵያ ጦር አንድ የገበያ ሥፍራን በተዋጊ ጄት በመደብደቡ ሠላማዊ ሰዎች ተገደሉ፤ አልተገደሉ የሚለዉ ፅንፍ የተጠጋ ተቃራኒ ክርክርም ወትሮም በአብዛኛዉ በግል ፍላጎትና ስሜት የሚነዳዉን የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ አስተያየት ሰጪን እብዙ ሥፍራ ከፍሎ ሲያነታርክ፤ ሲያሰዳድብ አልፎ ተርፎ ጉዳዩን የዘገቡ መገናኛ ዘዴዎችንም ሲያዘልፍ ነዉ የሰነበተዉ።በዛሬዉ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ቅኝት ዝግጅታችን በሁለቱ ጉዳዮች ላይ ከተሰጡ በርካታ አስተያየቶች በተቻለ መጠን ምክንያታዊ የሚመስሉን ነቅሰን ለማቅረብ እንሞራለን።ከምርጫዉ ነዉ የምንጀምረዉ።
ባለፈዉ ሰኞ የተደረገዉ ምርጫ ድምፅ ከመሰጠቱ በፊት ብዙ እንደተፈራዉ የጎላ ሁከትና ብጥብጥ ሳያጋጥመዉ በሰላም ተጠንቅቋል።ይሁንና የኢትጵያ የፌደራል ፖሊስ ባለፈዉ ሮብ እንዳስታወቀዉ በኦሮሞያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ሁለት ወረዳዎች የድምፅ አሰጣጡን ሒደት ለማወክ የሞከሩ ፖሊስ «ሸኔ» ያላቸዉ ታጣቂዎችና ፀጥታ አስከባሪዎች ተጋጭተዉ ቢያስን ሁለት ሰዎች መገደላቸዉን አስታዉቋል።ምርጫዉን ለማወክ አሲረዋል የተባሉ ከ120 በላይ ሰዎች መታሰራቸዉንም ፖሊስ አስታዉቋል።
አማራና ደቡብ ክልሎችም ዉስጥ የድምፅ አሰጣጡን ሒደት ለማወክ የተደረጉ ሙከራዎች በፀጥታ ኃይላት መክሸፋቸዉን የየአካባቢዉ ባለስልጣናት አስታዉቀዋል።የድምፅ አሰጣጡ ሒደት በሰላም መጠናቀቁ፣ ቆጠራና ዉጤቱ ሲዘገብ ባለፈዉ ሮብ ኤፍሬም ኤፍሬም የተባለ የፌስ ቡክ ተከታታይ በፃፈዉ አስተያየት «የምን ምርጫ» ይላል በቃል አጋኖ ና በጥያቄ ምልክት ባጀበዉ ፅሑፉ «ሥልጣን እኮ በጉልበት ሆኗል።» ኤፍሬም ኤፍሬም ነዉ እንዲሕ ያለዉ።
ሔጉ ማረጉ ግን ተቃራኒዉን ባይ ነዉ።«ሕዝብ መሪዎቹን መርጧል» አለ-ባጭሩ-በፌስቡክ።አቡ አሚን ከሔጉ ማረጉ ጋር ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥቷል።«ሕዝብ መርጧል፣ የተመረጡት ሐገር ይመራሉ።ሌላ ወሬ አንፈልግም።በቃ» የአሚን አባት በፌስ ቡክ።
«ሌላ ወሬ እንዲቀር»  በመፈለግ ቢሆን ጥሩ ነበር።ግን አልቀረም።የእነ አቡ አሚን አስተያየት ሲነበብ ከወደ ሐዋሳ የደረሰን ዜና ደቡብ ክልል ዉስጥ የድምፅ አሰጣጡን ሒደት ለማወክ የሞከሩ የተባሉ 194 ተጠርጣሪዎች መያዛቸዉን የክልሉ ፖሊስ አስታዉቋል።
ታመነ አዳል በፌስ ቡክ ይጠይቃል።«ማን አሰማርቷቸዉ ነዉ፣ ወንጀለኛዉ ማነዉ?» እያለ።
ሕይወት እንደዋዛ (ወንድ ይሁን ሴት አናዉቅም) «የብልፅግና ካድሬ አይታሥርም» ትለለች ወይም ይላል።አክሊሉ መንገሻ በፌስ ቡክ ካሰፈረዉ ረዘም ያለ አስተያየት ገሚሱ እንዲሕ ይላል፣-«የሰዎች ጅምላ ጭፍጭፉ ምንም ጥፋት የሌለበት ሰው፣ በገዛ ሃገሩ በዘር እየተለየ (መገደሉ) መቆም አለበት ፣የብሔር እና የሃይማኖት ግጭት መቆም አለበት። ሰላም ፣ፍትህ እኩልነት የሰፈነባት አንዲት ኢትዮጵያ፣ የግድቡ መጠናቀቅ እና የተጀመሩ ሰፋፊ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ አለባቸዉ።»
ምንተስኖት ቸሩ አምላክ፣ በፌስ ቡክ «ምርጫው ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ይበጀኛል ያለውን በነፃነት የመረጠበት፣ እንከን የለሽ ታሪካዊ ምርጫ ነው።» ብሏል።
የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ሥለ ኢትዮጵያ ምርጫና ሐገራቸዉ ቢሆን ሥለምትሻዉ ቀጣይ ፖለቲካ የሰጡት አስተያየት የብዙዎችን አስተያየት ጋብዟል።ቃል አቀባዩ ከምርጫዉ በኋላ ኢትዮጵያዉያን ልዩነታቸዉን ለማስወገድ በጋራ እንዲሰሩ መክረዋል።
አቤ መብ ግን በፌስ ቡክ፤ አሜሪካኖችን ይመክራል።«እስኪ እናንተ የአሜሪካ መሪዎች ፈጣሪ ልብ ይስጣችሁ!!! » ይላል በሶስት ቃል አጋኖ።«አይናችሁን ክፈቱ እና ተመልከቱ !!! በፈጣሪ ፊት ምስኪኗ ኢትዮጵያ እያሸነፈች ነው !!!» ሌላ ስድስት ቃል አጋኖ ጨምሮበታል-አቤ መብ።
እስራኤ ጀማል ደግሞ አሜሪካኖች ከኢትዮጵያ እንዲማሩ ጋብዟል።ያዉም ዴሞክራሲን «ዴሞክራሲ ።ከኢትዮጵያ ተማሩ።» ይላል» እስራኤል።
እስማኤል ካሳዉ በፌስ ቡክ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያሰፈረዉ አስተያየት «ለማንኛዉም፤ አሜሪካን እናመሰግናለን።ጥያቄያችን ግን እባካችሁ፤ በዉስጥ ጉዳያችን ጣልቃ አትግቡ» የሚል ነዉ።
**አስራት ደምመላሽ የዶቸ ቬለን አንድ የፌስ ቡክ ዘገባን አንብቦ ስለ ፊደል ግድፈቱ የሰጠዉን አስተያየት አለመጥቀስ አይቻልም።«DW Amharic አማርኛ እንዴት ነው?»  ይጠይቃል።ሶስት የቃላት ግድፈቶችን ይጠቅሳል።የዶቸ ቬለ ዘጋቢና አርታኢ ምዕራብን-ምዕብ፣ ሙከራን ሙከሪያ፣ ሸኔን  ሸነ ብለዉ ፅፈዉታል።ስሕተት ነዉ።አስራትን እናመሰግናለን።በተቻለ መጠን እንጠነቀቃለን።
ወደ ሁለተኛዉ ርዕሥ እንለፍ።

Äthiopien Luftangriff Tigray-Region
ምስል Tigray Guardians 24/REUTERS
Äthiopien Dire Dawa | Parlamentswahl 2021
ምስል M.Teklu/DW

ከትግራይ ክልል ርዕሠ ከተማ ከመቀሌ በጥቂት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘዉ ቶጎጋ በተባለች አነስተኛ መንደር ባለፈዉ ማክሰኞ የኢትዮጵያ የጦር ጄቶች በጣሉት ቦምብ 80 ሠላማዊ ሰዎች ተገደሉ መባሉ አዲስ ዉዝግብ፣ ስድድብና ንትርክ አስከትሏል።
የአዉሮጳ ሕብረትና ዩናይትድ ስቴትስ በጥቃቱ ሠላማዊ ሰዎች ተገደሉ መባሉን በተለይም ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ ሐኪሞችና አምቡላንሶች ወደ መንደሪቱ እንዳይገቡ ተከለከሉ መባሉን አዉግዘዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሚንስቴር ትናንት በሰጠዉ መግለጫ ግን ጥቃቱ ያነጣጠረዉ መንግሥት በአሸባሪነት በፈረጀዉ በሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት) ደፈጣ ተዋጊዎች ላይ እንደነበረ አስታዉቋል።
ቢም ቦኬ ዎን የሚል የፌስ ቡክ ስም ያለዉ አድማጭ «በወያኔ ምክንያት ገና ሕዝቡ ዋጋ ይከፍላል» ይላል።«በደርግ ሰዓት በወያኔ ምክንያት እንደከፈለዉ ሁሉ።» ዘርይሁን ከበደም እንደ ቢም ቦኬ፤«ኦነግ የኦሮሞን ሕዝብ እንደ ጎዳዉ ሁሉ፣የሕወሓት ማንኛዉም መፈራገጥ የተጋሩ የስቃይ ምንጭ ነዉ» ይላል።

ዘይነባ ዓሊ ግን በነ  ዘርይሁን አስተያየት አትስማም።«በወገን ላይ የዚሕን ያክል ጭካኔ አይቼ አላዉቅም።አዝናለሁ።» ብላለች።ኤፍሬም ኦርቶን በፌስቡክ የሰጠዉ አስተያየት አይ-አዎ አይነት ነዉ።እንዲሕ ይላል።«ማንም ይሁን ማን፣ የትም ይሁን የት፣ ንፁሐን ዜጎች የጥቃት ሠለባ መሆን የለባቸውም።» አለ። ግን ቀጠለና «ነገር ግን ከወያኔ ወግኖ፣ ደግፎ የተገኘ አብሮ መዉደም፣ መወቀጥ አለበት።» የኤፍሬም ኦርቶን አስተያየት ነዉ።

Äthiopien Getnet Adane
ምስል Seyoum Getu/DW

የጀራድ ጄን ስልጤ አስተያየት አጭር ነዉ።ጥያቄ ብጤ።«የሐዉዜን ታሪክ ተደግሞ ይሆን?» 
ዮሐንስ ገረሱስ በረጅም የፌስ ቡክ ፅሁፉ ማስተላለፍ የፈለገዉ መልዕክት ምፀታዊ ነዉ።«ከሰሜኑ ጦርነት፣ ከትግራይ ርሃብና ጉስቁልና፣ ከኦሮሚያው ያሸባሪዎች ተደጋጋሚ ጥቃቶች፣ ከቤንሻንጉሉ የተደራጀ የሽምቅ ውግያ፣ ከሱዳኑ የኢትዮጵያ መሬት መውረር፣ ከምርጫው ውዥንብር፣ ከሻቀበው ገበያ፣ የ"ኢሱ"በእጁና እግሩ ከነግብረሃይሎቹ እስከ 4 ኪሎ መግባት፣ ከዚህ ሁሉ በስተቀር ኢትዮጵያ በጥሩ ሁኔታ ላይ ትገኛለች።» የዮሐንስ ገረየሱስ አስተያየት ነዉ።
በዚሁ ይብቃን። መልካም ምሽት።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ