1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ሰኔ 4 2013

የኤርትራ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዩናይትድ ስቴትስን የወቀሱበት ደብዳቤ፣ የኬንያዉ ፕሬዝደንት በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝትና የኤርትራ ጦር ኦሮሚያ መስተዳድርግ ሠፍሯል፣ አልሠፈረም የሚለዉ ዉዝብ

https://p.dw.com/p/3ukt9
Symbolbild: Pinterest
ምስል picture alliance/X. Gs

የኤርትራ ደብዳቤ፣ የኬንያታ ጉብኝት፤ የኤርትራ ጦር ኦሮሚያ ሠፍሯል መባሉ

ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።ለዛሬዉ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት፣ ሳምንቱን የብዙ ተከታታዮችን ትኩረት በሳቡ ሶስት ርዕሶች ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች የጎሉትን መርጣናል።ርዕሶቹ የኤርትራ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዩናይትድ ስቴትስን የወቀሱበት ደብዳቤ፣ የኬንያዉ ፕሬዝደንት በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝትና የኤርትራ ጦር ኦሮሚያ መስተዳድርግ ሠፍሯል፣ አልሠፈረም የሚለዉ ዉዝብ ናቸዉ።በዚሁ ቅደም ተከተል እንቃኛቸዋለን።
የኤርትራ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዑስማን ሳሌሕ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት በፃፉት ደብዳቤ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት የጆ ባይደን አስተዳደርን አጥብቀዉ ወቅሰዋል።ባለፈዉ ሰኞ በመገናኛ ዘዴዎች የተሰራጨዉ የሚንስትር ዑስማን ደብዳቤ የባይደን አስተዳደር በክልሉ (አፍሪቃ ቀንድ)  «ጣልቃ በመግባትና በማስፈራራት ተጨማሪ ግጭትና አለመረጋጋትን» እየቀሰቀሰ ነዉ በማለት ይወቅሳል።
ክስ መሰሉ ወቀሳን የሚያወሳዉ ዜና በተለይ በዶቸ ቬለ የፌስ ቡክ ገፅ እንደተሰራጨ ባጭር ጊዜ ዉስጥ በመቶ ሺሕ የሚቀጠሩ ተከታታዮች አንብበዉ፣ተቀባብለዉታል፣ አስተያየት ሰጥተዉበታልም።
ይልቃል አሰፋ፣ የኤርትራ መንግስትን አቋም የሚጋራ ይመስላል።«አሜሪካና እና ሸሪኮቿ በምስራቅ አፍሪካ የሚከተሉት የተሳሳተ ፖሊሲ ውጤት» ይላል ይልቃል፣« በቀጠናው ለተከሰተው ሁለንተናዊ ቀውስ ዋንኛ ተጠያቂ ናቸው» በዚሕ አላበቃም  «የአካባቢው ሀገራት በማያቋርጥ ግጭት ውስጥ እንዲቆዩ በማድረግ ለብሄራዊ ጥቅማችን ያስፈልጉናል የሚሏቸውን የአካባቢውን ሪሶርስ (ሐብት) ለመቀራመት እየተንቀሳቀሱ ነው።»
ወይ ኢትዮጵያ፣ የሚል የፌስ ቡክ ስም ያለዉ ተከታታይ ግን ተቃራኒዉን ባይ ናቸዉ።«በጣም የሚያሳዝን እኮ ነው።» ይላል ወይ ኢትዮጵያ፣ በጥያቄ የሚያሳርግ አስተያየቱን ሲጀምር «የኤርትራን ሕዝብ ጨቁኖ ከሰውነት በታች አድርጎ ለ30 አመታት የገዛዉ----ኢሳያስ አፈወርቂ አሁን ደግሞ በትግራይ ሰብአዊ መብት አየጣሰ አለም ዝም ብሎ እንዲመለከተው ይፈልጋል?» 
የሙሴ ኒራዮ አስተያየት አጭር ነዉ፣ «የኤርትራ መንግስት ሞራል የለውም።» የሚል።ከማል መሐመድ ግን ኤርትራን ያመሰግናል፣ «ኤርትራ መቸም የማንረሳዉ የቁርጥ ቀን ወዳጃችን፣ ሁሌም እንወዳቹሀለን ከጎናቹሕ ነን» እያለ።መሐረነ ቦጋለ በዚያዉ በፌስ ቡክ ያሰፈረዉ አስተያየት የነከማልን ይቃረናል እንዲሕ እያለ።«እድሜ ዘመናቸውን በመእቀብና በዴሞክራሲ እጦት አገራቸውን ከመበደልም በላይ የሚሰጣቸውን በጎ ትችት በበጎ ህሊና አይመለከቱትም ። ዞሮ ዞሮ አንድ ቀን ዋጋቸውን ያገኙታል።»
አበበ በርሔ «ወሬ ሳታበዙ፣ የኤርትራ ጦር መዉጣት አለበት።» ብሎ አበቃ።ምህረተአብ ገብረስላሴ በእንግሊዝኛ ያሰፈረዉ አስተያየት ትርጉም እንዲሕ ይነበባል «ሳይናሳዊና ተጠየቃዊ ያልሆነ ወቀሳ በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ላይ ምንም የሚያመጣዉ ነገር የለም።በጭፍን አዕምሮና ሕሊና በጭፍን መዉቀስ ቀላል ነዉ።»

EU-Afrika-Gipfel in Brüssel | Eritreas Außenminister Osman Saleh Mohammed
ምስል picture-alliance/dpa/S. Lecocq

የኬንያዉ ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ባለፈዉ ማክሰኞ ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል።የጉብኝቱ ዓላማና ፕሬዝደንቱ ከጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ጋር ያደረጉት ዉይይት ዉጤት በዝርዝር አልተነገረም።ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት የሚቆጣጠራቸዉ መገናኛ ዘዴዎች ባለፈዉ ማክሰኞ እንደዘገቡት ኬንያታ ከጠቅላይ ሚንስር ዓብይ ጋር ሆነዉ ችግኝ ተክለዋል።ጠቅላይ ሚንስሩም  «ወድሜ» ያሏቸዉ ኬንያታ ኢትዮጵያን የጎበኙት «ኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ደረጃ 6 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል እና 1 ቢሊየን ችግኞችን ለጎረቤት ሃገር በማዘጋጀት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን ወደ ቀጣናው በምታስፋፋበት ወቅት ላይ ነዉ» ማለታቸዉ ተጠቅሷል።
ጉተማ ፕሬስ የተባለ አስተያየት ሰጪ በፌስ ቡክ እንዳሰፈረዉ  የጉብኝት ዉይይቱ ሒደት፣ መልዕክትና ዉጤቱ ያሳሰባዉ አይመስልም።ኬንያታ ከናይሮቢ አዲስ አበባ የተጓዙበትን ምክንያት ግን ባጭሩ ገምቷል።«ምርጫዉን አራዝሙ።ከአሜሪካ ጋር ሰፋጣችሁን አቁሙ።የህዳሴዉን ሙሌት ትንሽ አዘግዩ ነዉ በቃ ምናለ በሉኝ።» ብሎ
የሜናሴ ወልደማርያም፦ፅሑፍ፣ አስተያየትን ከምኞች የቀየጠ ነዉ።«ኬንያ ሰላማዊ ጎረቤታችን ነች» አለ በቃለ አጋኖ፣ ቀጠለም «ግንኙነታችን ተጠናክሮ ንግድና ኢኮኖሚ ለህዝባችን እንዲስፋፋ እንዲሰምር እንመኛለን።» ሜናሴ ነዉ ይሕን ያለዉ።

ኢብራሒም ኑርሁሴን የኬንያታን ጉብኝት «አሜሪካና አውሮጳ የሰጡትን መልዕክት እንዲያደርስ ነው የተላከው። መልዕክቱ የመጨረሻቸው ማስጠንቀቂያ እንደሆነ ይገመታል። እንቢ ካለ ዋጋውን ለመስጠት ነው።» ይላል።ፍቃዱ አድምቄ፣ ኢትዮጵያ ጎረቤቶችዋን ለማባበል ጊዜ ማጥፋት የለባትም ባይ ነዉ።«የኢትዮጵያ ጎረቤቶች ጥንካሬዋ ላይ የተመሠረቱ ስለሆነ፣ እነሱን ለማባበል ብዙ ጊዜ ማጥፋት የለብንም።እግራችን ላይ የሚወድቁበት ሁለት ቁልፍ ስራዎች ከፊታችን አሉ። ይህውም ግድባችንን ውሃ መሙላትና ምርጫውን ሰላማዊና ዲምክራሲያዊ አድርጎ የህዝብ ይሁንታን ያገኙ/ያገኘ ፓርቲ፣ መንግስት እንዲመሰርት ማድረግ፣ ዝቅተኛ የህዝብ ድምፅ ያገኙ ፓርቲዎች ለገዢው ፓርቲ እውቅና ሲሰጡ ነው።» የፍቃዱ አድምቄ አስተያየት።
ተስፋ መኬ፣ ጉብኝቱን «ትልቅ ጉዳይ አይደለም» ብሎታል-በእንግሊዝኛ በፃፈዉ አጭር አስተያየት።ወደ መጨረሻዉ ርዕሳችን እንለፍ።የኤርትራ ጦር ከትግራይ አልፎ በሌሎች የኢትዮጵያ ግዛቶች በተለይም «በኦሮሚያ ክልል ሠፍሯል» የሚል መረጃ በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ብርዥ-ጥርዥ ሲል ሁለት ሳምንት ሆኖታል።በአቶ ዳዉድ ኢብሳ የሚመራዉ ኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ባለፈዉ ሮብ መረጃዉን «ዕዉነት ነዉ» ብሏል።የኦነግ ጊዚያዊ ቃል አቀባይ እንዳሉት የኤርትራ ሠራዊት በምዕራብና ደቡብ ኦሮሚያ እየተንቀሳቀሰ ነዉ።የኦሮሚያ መስተዳድር ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ግን መረጃውን «መሰረተ ቢስ» በማለት አጣጥለዉታል።
ደሜ ሰዉ አሰፋ፣-«እና ኦነግ ምን አገባው፡ ለካ እዚያ አካባቢ ማስተዳደር ጀምሯል¡¡¡» ይላል በትዕምርተ ስላቅ።ማነሕ ልበለዉ፣ በሚል የፌስቡክ ስም የሚጠራዉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ «የኤርትሪያ ጦር አዲስ አበባም ገብቷል።በየሰፈሩ ያዉም» ባይ ነዉ፣« «ኦሮሚያ እንኳ ብዙ የነጻነት ተዋጊዮች ስላሉ የትም አይደርስም። ወራሪን እንዴት እንደሚመለስ ኦሮሞ ያውቃል።» ብሎ አሳረገ።ደሜ ሰዉ አስፋዉ።
ስሙን፣ «ሰዉ ፍለጋ» ያለዉ ደግሞ «ሲጀመር ኦነግ የኤርትራን ጦር ከሶ?» ይጠይቃል።ጃሕ ጃሕ የሚል የፌስ ቡክ ስም የለጠፈዉ ደግሞ «የመንግስት ሹማምንትን መጠየቅ አያስፈልግም፤ ምክያቱም ከዚህ በፊት ኦሮሞን ሲያስጨፈጭፉ የነበሩት ባለስልጣን በሽልማት ጡረታ ወተዋል ታዲያ እነዚህም ቢዋሹ ምን ይገርማል የሻቢያ ወታደር ከመቀሌ ኦሮሚያ እየገባ ነው።»ይላል።ለዛሬ አበቃን።

 Logo Oromo Liberation Front
Bildcombo I Abiy Ahmed und  Uhuru Kenyatta

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ