1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ነሐሴ 29 2012

ሰሞኑን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርካቶች ሲቀባበሏቸው ከነበሩ ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ወይም ኢዜማ «በአዲስ አበባ ከተማ ህገ ወጥ የመሬት ወረራ እና በከተማዋ የተገነቡ የጋራ መኖርያ ቤቶች ለማይገባቸው ሰዎች መሰጠታቸዉን» በጥናት ደርሼበታለሁ ያለውን መግለጫ መስጠቱ አንዱ ነበር።

https://p.dw.com/p/3hxVR
Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ሰሞኑን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርካቶች ሲቀባበሏቸው ከነበሩ ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ወይም ኢዜማ «በአዲስ አበባ ከተማ ህገ ወጥ የመሬት ወረራ እና በከተማዋ የተገነቡ የጋራ መኖርያ ቤቶች ለማይገባቸው ሰዎች መሰጠታቸዉን» በጥናት ደርሼበታለሁ ያለውን መግለጫ መስጠቱ አንዱ ነበር። ኢዜማ « የመሬት ወረራ» ባለው አንደኛው ክሱ በተለይም በከተማዋ ውስጥ እና ዙርያ የሚገኙ አርሶ አደሮች እና የአርሶ አደር ቤተሰብ ነን በሚሉ ሰዎች መፈጸሙን ገልጾ፣ የከተማዋ ባለስልጣናት አይቶ እንዳላየ አልፈዋል፤ አልያም  በወረራው ተሳትፎ ነበራቸው ብሏል። ኢዜማ አስጠናሁት ባላቸው አምስት ክፍለ ከተሞች ውስጥ 213,900 ካሬ ሜትር መሬት በህገ ወጥ መንገድ  መያዙን ነው። በከተማዋ ተገንብተው የተጠናቀቁ  የጋራ መኖርያ ቤቶችም በተመሳሳይ በህገ ወጥ መንገድ ለማይገባቸው ተላልፎ ተሰጥተዋል በሚል ይፋ በተደረገው የኢዜማ ጥናት በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ወደ ሁለት ጫፍ የተለጠጡ ሃሳቦች ተስተናግደውበታል።

አህመድ ቱሃር አሚ «የዘገያችሁ ቢሆንም መቅረት ስላልሆነ አሁንም ከሚመሳሰላችሁ ለአዲስ አበቤ ከሚለፉት ጋር በህብረት መሥራት እና መታገል ያስፈልጋል ። በየሳምንቱ በሚሆን እና በማይሆን ሀሳብ አጀንዳ እየሰጡት መሠረታዊ ጥያቄውን እንዲረሳ ከሚያደርጉ ጉዳዮች ህዝቡን ማንቃት ነው ።»

ነጻነት አበራ «አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት አጣብቂኝ የፖለቲካ እና የህልውና እንዲሁም ከየቦታው ካለው ችግር አንፃር ችግሩ እውነት ቢሆንም ጉዳዩን ውስጥ ለውስጥ ጨርሶ ለሌሎች ቀዳዳ በማይከፍት መልኩ መፍትሔ ቢፈለግ ጥሩ አይሆንም ወይ ?»

ኢትዮጵያ ወይራራ « መጀመሪያ ቦሌን ቡልቡላን መካኒሳን ያካን ጉለሌን ጎሮን ቆየፈጬን ጃሞን ላቡን..... ወዘተ ተቀምተው ለተባረሩት ገበሬዎች ልክ እንደዚህ ጥናት ስሩና ጉዳታቸውን አሳዩን.. ከዛ ይሄን የናንተን ጥናት እንሰማለን»

EZEMA Party in Mekelle
ምስል DW/M. Haileselassie

ገዳ ኤም ቱፋ «ከምዝገባ እና 15 አመት ቁጠባ በላይ ዕድሜ ልክ ከኖሩበት መሬት የተፈናቀሉት ዜጎች ሊያሳስበን ይገበናል፡፡»

ጆህን ጌታሁን « ይሄ ህዝብ ማንን ይመን? ሁሌ ይሰረቃል ሁሌ ይበደላል! ሌባ እና የቀን ጅብ ስንላቸው የነበሩ የሚያደርጉትን ዛሬም ከተደረገ ነገም የሚመጣው እጁ ንፁህ አፉ ቀላጤ አጭቤ ከሆነ ማነው ታዲያ ለዚህ ህዝብ ለእውነት የቆመ ? ዶክተር አብይስ ይህን ጉዳይ እንዴት ችላ አለው ወይስ......?»

ዘሪሁን ታ «"ሌባ ከሄደ ውሻ ይጮሃል እንዳይሆን !" ...የዛሬው የኢዜማ መግለጫ ለብልፅግና ፓርቲ መደገፊያ ወይም ማወደሻ ከሆነ ነው እንጂ መቃወሚያ አይመስልም ።የታከለ ኡማ ከአዲስ አበባ ከንቲባነት መነሳት ልክ ነበር ብሎ ለማሳበቅ ካልሆነ በስተቀር ግዜውን የጠበቀ አይደለም ።»

ወንድሙ አብቹ « ኢንጅነር ታከለ የደሀ ልጅ ቀና ያለበት ከተማችንን እጅግ ወደ ዘመናዊነት በእብዛኛው የቀየረ ህዝቦችን በአንድነት እንዲፋቀሩ የሰራ በአሉባልታ ምንም አይመጣም ሀገር ይፈርሳል እንጂ»

ጌታሁን አለሙ «በሽታውን የበለጠ መለየቱ ጥሩ ነው ትልቁ ጉዳይ ግን መድሃኒቱን ማግኘትን ይጠይቃል»የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ወይም ኢዜማ ይህንኑ ጥናት ይፋ ማድረጉን ተከትሎ የቀድሞው ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ ለኢዜማ መግለጫ በፌስ ቡክ አድራሻቸው መልስ ሰጥተዋል።« በሃሰተኛ መረጃ ሀገር ማፍረስ ይቻል ይሆናል እንጂ ሀገር አይገነባም፤ የፖለቲካ ትርፍም የለውም።» ሲሉ ክሱን አጣጥለዋል።

ቴዎድሮስ ከበደ « በየትኛውም አለም የከተሞች መስፋፋት እራሱን የቻለ ጣጣ አለው። መፈናቀልንም ሊያስከትል ይችላል። ለሚፈናቀሉ ዜጎች በህጋዊ መንገድ ተመጣጣኝ ካሳ መክፈል የተለመደና ችግሩን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የሚቀርፍ አሰራር ነው። ያልተለመደው አሰራር ሌሎች ወገባቸውን አስረው፣ በችግር ቆጥበው የሰሩትን ቤት ልክ እንደ ሰንበቴ ዳቦ እያነሳህ ልታድለውና ልትመጸውተው አትችልም። ምክንያቱም ግልጽ ነው። ህገ ወጥ አሰራር ነው!"መሬት ላራሹ" እንደተባለ ሁሉ አሁን ላይ "ቤት ለባለቤቱ" ወይንም "ቤት ለቆጣቢው" የሚል ህዝባዊ ንቅናቄ ሊያስነሳ ይችላል። ህዝብ የብልጥግና መና ጠብቆ ባዶ እጁን ከቀረ ችግር ነው።እውነት ለመናገር ከ15 አመታት በላይ ሲቆጥብና ሲጠብቅ ለኖረ ህዝብ ኮንዶሚኒየሞቹን በነጻ አደልናቸው ከሚለው ዜና ይልቅ ጠፍተው ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመተባበር በማፈላለግ ላይ ነን የሚለው መግለጫ የተሻለና ጊዜ ለመግዛት ትንሽም ቢሆን ለሁሉም እፎይታ ይሰጥ ነበር። ጥሩ ማካካሻ ነው»

ሰሞኑን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ትኩረትን ስበው ከነበሩ ጉዳዮች ሌላኛው ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ በክልሉ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ከተማ የገዳ ስረዓት እንደ አንድ የትምህርት  አይነት  ለማስተማር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ማስታወቁ ነው። ቢሮው ከቀጣዩ የትምህርት ዘመን ጀምሮ በተለይ  በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትምህርቱን ለማስጀመር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ሲገልጽ ፤ ትምህርቱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በሚገኙ ትምህርት ቤቶችም ተግባራዊ ይደረጋል መባሉ ደግሞ ድጋፍም ትችትም እንዲያስተናግድ አድርጎታል።

ልዑል ተስፋዬ ተሰማ «እጅግ በጣም ደስ ይላል የገዳ ስርዓት በሚገባ ለትውልድ ስነምግባር በተላበሰ መልኩ ሊሰጥ ይገባል። ትውልድን ከክፋት ከምቀኝነት እና ከመሳሰሉት ክፉ ተግባራት ለመታደግ በዚህ በገዳ ስርዓት ውስጥ መታቀፍ አቻ የማይገኝለት ሲሆን ሁሉም ነገር በዚህ በኩል መፍትሄ እንደሚያገኝ ተስፋ አለኝ!»

Äthiopien Irrecha Feierlichkeiten in Mekele
ምስል Solomn Geda

ፈልመታ ገዳ « እኛ የገዳን ሥርዐት በትምህርት መልክ ለራሳችን ልጆች ማስተማር ግዴታችን የመሆኑን ያክል በሌሎች ማህበረሰብ ላይ በግድ እንዲማሩ አንሻም።ሰሞኑን በቋፍ ያለዉን የህዝብ ግንኙነት ለማጦዝ በገዥዉ ፓርቲ የሚደረገዉ ክብሪት የመጫር ሁኔታ ኃላፊነት የጎደለዉ ነዉ።»

ልጅ ኢያሱ «አንዱ የአንዱን ባህል ማወቁ ደስ ይላል ግን ሀገራችን ሰፊ ናት ከሁሉም ብሄረሰብ መልካም እሴት ተጨምቆ ቢዘጋጅ መልካም ነው ካለበለዚያ ወደ አሀዳዊነት መመለሳችን ነው ።»

ሽኮሪና ጓል ኤርትግራይ « እውቀት ጥሩ ነው አዲስ አበባ ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩባት ናት አንዱ የሌላውን ቋንቋ ባህል ማወቁ ይበል የሚያስብል ነው ማንም እስከዛሬ አማርኛ በመማሩ የሚከፋው የለም አሁንም እኛ ብቻ ከማለት ወተን የሌላውንም ለማክበርና ለመማር መዘጋጀት ነው ቀጣይም የሌሎች ብሔሮችን እንደሚያካትት አምናለሁ»

ያሬድ አሰፋ ይመር «የሁሉንም ጎሳዎች የሚያስተዋውቅ የትምሀርት ሥርዐት ቢቀረጽ መልካም ነው! የአንዱን ብቻ ማጉላት 'የባህል ወረራ' ሊያስመስል ይችላል። የመደመር ፍልስፍናም ተቃራኒ ነው። በኦሮሞ ሊህቃን የሚደረገውም "እኛ ብቻ" የሚለው አመለካከታቸው ቢታሰብበት ጥሩ ነው።»

ዩናይትድስቴትስ በቅርቡ ለኢትዮጵያ ትሰጥ የነበረውን የ130 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ ማገዷ ተሰምቷል። ዕገዳው እንደተሰማ የተለያዩ መላ ምቶች በምክንያትነት ሲንሸራሸሩ የነበረ ሲሆን የኋላ ኋላ ኢትዮጵያ ከግብጽ እና ሱዳን ጋር በህዳሴው ግድብ ላይ ከምታደርገው የሶስትዮሽ ድርድር እንደሚያያዝ ተነግሯል። ድርድሩ ከአንዳች መቋጫ ሳይደርስ ኢትዮጵያ የግድቡን ሙሌት መጀመሯ ለትራምፕ አስተዳደር መቀጣጫ መዳረጓን ዘገባዎች አመልክተዋል። በዩናይትድስቴትስ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ ዩናይትድስቴትስ የገንዘብ ድጋፉን ያገደችው በጊዜአዊነት መሆኑን ከባለስልጣናት መረዳታቸውን በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል። የዩናይትድስቴትስ የገንዘብ ድጋፍ ዕገዳን ተከትሎም በርካቶች ሃሳባቸውን አንሸራሽረውበታል።

ዲቦራ ባሰፈሩት « ኢትዮጵያውያን ለሀገራችን አናንስም ። መተባበር ካለ የማንም እርዳታ አያስፈልገንም ነበር።ነገር ግን መተባበር ያንሰናል። አንድ የማናስተውለው ነገር አንድ ሰው በግሉ ቢሊየነር ሊሆን ይችላል። ነ,ገር ግን እንደ ሀገር የምንታወቀው በድህነት እና በልመና ነው ። ልብ እንግዛ » ብለዋል።

ሙሉቀን ሊም «እና እሷ ያለችውን ካልተቀበልን ወይም የትራምፕ አስተዳደር በምርጫ ካልተወገደ ቋሚ ክልከል መሆኑ ይቀራል? አስገድደው ውሳኔያቸውን እንድንቀበል የተደረገ አይደለም? ለምን ታገደ ለምን ይነሳል? ለማንኛውም ዕርዳታው ይቅርብን እንጂ የመጪውን ትውልድ ተስፋና ብሔራዊ ጥቅማችንን አሳልፈን ልንሰጥ አይገባም።»

የሱነህ ወልዴ « የተለመደውን በድርድሩ ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር የተወሰደ እርምጃ ስለሆነ ነቅቶ መደራደር እና የወደፊት ትውልድ የመልማት ፍላጎትን ያማከለ ሆኖ የአገርን ጥቅም ማስከበር ከጀግኖቻችን ተደራዳሪዎች ይጠበቃል ።»

መሪሁን መንገሻ ዩናይትድስቴትስ ለኢትዮጵያ ትሰጥ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ ያገደችው « በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ርገጣ ስለነገሰ በተለያዩ በውጭ ሀገራት ያሉት ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በተለይም ቄሮዎች ለዓለም ባሰሙት ምክንያት ነው ይህ ማዕቀብ በኢትዮጵያ ላይ ሊጣል የተቻለው።» ሲሉ የሻለ ከፈለኝ ለዚሁ አስተያየት በሰጡት ምላሽ « አሜሪካ በሰብአዊ መብት ረገጣ ማእቀብ ጥላ አተውቅም የራሷን እና የአጋሮቿን ሀሳብ ለመጫን ካልሆነ» ብለዋል።

አድማጮች ለዕለቱ ያልነው የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ዝግጅታችንም ይኸንኑ ይመስል ነበር ። ለአብሮነታችሁ ምስጋናዬ ከልብ ነው ።ታምራት ዲንሳ ነኝ ጤና ይስጥልኝ።

ታምራት ዲንሳ

ነጋሽ መሐመድ