1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ የካቲት 6 2012

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ተከታታዮችን በብዛት ያሳተፉ ሶስት ርዕሶች መርጠናል።የኤርትራ ፕሬዝደንት እና የትግራይ ምክርትል ርዕሠ መስተዳድር መግለጫዎች፣ የታገቱ ተማሪዎች፣ ማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ዘገባና ወላጆች፣እንዲሁም የአፍሪቃ ሕብረት ጉባኤ ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/3Xn2z
Symbolbild Apps Facebook und Google Anwendungen
ምስል picture-alliance/dpa/S. Stache

የኤርትራና የትግራይ መሪዎች፣ የታገቱ ተማሪዎች ወላጆች ሮሮ፣ የአፍሪቃ መሪዎች

 

ጤና ይስጥልኝ እንደምን ሰነበታችሁ።ሳምንቱን የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ተከታታዮችን በብዛት ያሳተፉ ሶስት ርዕሶች መርጠናል።የኤርትራ ፕሬዝደንት እና የትግራይ ምክርትል ርዕሠ መስተዳድር መግለጫዎች፣ የታገቱ ተማሪዎች፣ ማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ዘገባና ወላጆች፣እንዲሁም የአፍሪቃ ሕብረት ጉባኤ ናቸዉ።አብራችሁን ቆዩ

የኤርትራ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባለፈዉ ሳምንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮ-ኤርትራን ሥምምነት የድንበር ዉዝግቡ ያለበትን ደረጃ ጠቃቅሰዋል።የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ሊቀመንበርና የትግራይ ምክትል ርዕሠ-መስተዳድር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ለፕሬዝደንት ኢሳያስ አስተያየት አፀፋ የመሰለ መልዕክት ባለፈዉ ሮብ አስተላልፈዋል።ጉዳዩ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አስተያየት ሰጪዎችን የሳበ መስሏል።

ብዙዎቹ አስተያየቶች ነቀፋ፤ ተራ ስድብ እና ርግማን የተፀባረቀባቸዉ ናቸዉ።ሰከን ያሉትን ለመምረጥ መክረናል።

ተስፉ በርሄ በፌስ ቡክ «በጣም የሚገርመው ጉዳይ የዚሕ ሰዉዬ ንግግር ነዉ።» ብለዉ ይጀምራሉ የፕሬዝደንት ኢሳያስን ማለታቸዉ ነዉ። «የራስዋ ኣሮባት የሰው ታማስላለች እንደሚባለው የኣገሩ ህዝብ ሰላምና ደህንነት ምንም ሳይመስለው ኣሁን ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ ሰላምና የምርጫ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ኣፉን ሞልቶ መናገሩ፣ ምን ያኽል ወዴታቸዉ የጠነከረና በኢትዮጵያ ጉዳይ እጁን ያስገባ መሆኑን በግላጭ ነግሮናል።» እያሉ ይቀጥላሉ።ረጅም መልዕክታቸዉን በትግሪኛ ቋንቋ ባሰፈሩት መልዕክት ነዉ የዘጉት።

Äthiopien Ankunft von Eritreas Präsident Isayas Afewerki
ምስል Getty Images/AFP/E. Soteras

 

አባ ኮስትር ጎድፌይ የተባሉት ደግሞ፤ ፕሬዝደንት ኢሳያስ የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ሁኔታ በከፋ ሁኔታ ላይ ነዉ ማለታቸዉ ሳያስቆጣቸዉ አልቀረም።« አኛ እንዲህ እንድንናቆር ማን አደረገንና ነው?  አሁን አዛኝ መስሎ በከፋ ሁኔታ ላይ ነው የሚለው-------» አባ ኮስትር ይሳደባሉም።አንደግመዉም። «ስልጣኑን በቃኝ በልና ለአዲሱ ትውልድ አስተላልፍ ።»ጨረሱ አባ ኮስትር።

 

ሲራክ ባሕልቢ በቲዊተር ገፃቸዉ ከፕሬዝደንት ኢሳያስ መግለጫ በኤኮኖሚ ላይ ያተኮረዉን መርጠዉ አስተያየት አስፍረዋል።«ፕሬዝደንቱ ስለ ኤኮኖሚ ያስተላለፉት መልዕክት ግልፅና የማያሻማ ነበር» ይላሉ ሲራክ በእንግሊዝኛ ባሰፈሩት ፅሁፍ፣ «ዘላቂና የማይቀለበስ ምጣኔ ሐብት ስለመገንባት ነዉ» እያሉ ይቀጥላሉ።

የዳግም ባንቺ፣ አስተያየት የሕወሓት ሊቀመንበርና የትግራይ ምክርትል ርዕሠ መስተዳድር በሰጡት መግለጫ ላይ ያነጣጠረ ነዉ።ያዉ ትችት ነዉ።«ህወሃት ፈርታለች ማለት ነው። አቅራራች ህውሃት። በ4 አቅጣጫ ድምጥማጧ ሊጠፋ ነው»------በዚሕ አላበቁም።እኛ ግን ሌላዉን አንጠቅስም።

Äthiopien l PK - Dr. Debretsion Gebremichael
ምስል DW/M. Haileselassie

 

ባለፈዉ ሮብ ላሰራጨነዉ ዘገባ የኤርትራና የትግራይ እሰጥ አገባ የሚል ርዕሥ ነዉ የሰጠነዉ።ምክንያቱ የቃላት እሰጥ አገባ የገጠሙት የኤርትራና የትግራይ መሪዎች በመሆናቸዉ ነዉ።አንደለኝ አካሉ የተባሉ የፌስ ቡክ አስተያየት ሰጪ በጣም ያሳሰባቸዉ የዘገባዉ ይዘት፤ምክንያቱና መዘዙ ሳይሆን ርዕሳችን ነዉ።«ዉዝግብ ካለ እንኳ «የኢትዮጵያና የኤርትራ» ተብሎ ነዉ የሚገለፀዉ ይላሉ የጋዜጠኞች አርታኢነት የሚዳዳቸዉ አስተያየት ሰጪ።ግን ስሕተት ነዉ።አስተያየት ሰጪ ሆይ።  ተናጋሪዎቹ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ሲሆኑ እርስዎ እንዳሉት እንላለን።

 

ታዘባቸዉ ተስፉ ግን «ባለስልጣን እንጅ ህዝብ ተጣልቶ አያውቅም» ይላሉ ከሳቸዉ በፊት አስየያት የሰጠዉን ሲወቅሱ።አሚ መሐመድ ግን የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ተባለ ወይም የኤርትራና የትግራይ ዉዝግቡን ለማስወገድ «አለም አቀፉ (ፍርድ ቤት) የበየነውን መፈፀም ብቻ ነው መፍህቴው» ባይ ናቸዉ።

 

*ባርኔጣ መለዮ የሚል የፌስ ቡክ ስም የደፉ አስተያየት ሰጪ ለየት ያለ ሐሳብ አላቸዉ።«የኤርትራ ህዝብ አንድነቱ ፈራርሶ የትግሬ መጫዎቻና እግር ዓጣቢ ከመሆኑ በፊት በጉዳዩ ዓሥቦበት ከኢሣያሥ ጋር በመሆን እንደሃገር መኖር ካልሆነ ደግሞ የበለጠ መከራና ሥቃይ ሥደትና ዉርደት እየከፋ እንዳይሄድ ያለዉ ዓማረጭ ከኢትዮጵዮጵያ ህዝብ ጋር እንደቀድሞዉ ባይሆን እንኳን በፌዴሬሽን መተሣሠሩ በኢኮኖሚዉም በፖለቲካዉም የተሻለ ሥለሚሆን ቢያሥቡበት ይሻላል።» አስተያየታቸዉ አለበቃም።በዚሕ ርዕስ ላይ እኛ አበቃን።

 

ባለፈዉ ታሕሳስ ማንነታቸዉ ባልታወቁ ሰዎች የታገቱት የደንቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጉዳይ መንግሥትን እንዳስወቀሰ፣ ባለስልጣናትን እንዳስወገዘ፣ ሕዝብን ባደባባይ እንዳሰለፈ እነሆ ሶስተኛ ወሩን ያዘ።ልጆቹ ያሉበት ሥፍራ፣ሁኔታና የአጋቾቹ ማንነትም በገልፅ አልታወቀም።ጊዜ በጊዜ ሲተካ የይሆናል ግምቶች፣ የሴራ ትንታኔዎች፣ ከሁሉም በላይ የሐሰት ዘገቦች እየተሰራጩ ነዉ።በአብዛኛዉ በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚሰራጩ የሐሰት መረጃዎች የተማሪዎቹ ወላጆችን ልብ እያደማዉ መሆኑን ባለፈዉ ሮብ ያነጋገርናቸዉ የሁለቱ ታጋቾች ወላጆች አስታዉቀዋል።

Äthiopien Addis Abeba Gipfeltreffen der Staatschefs der Afrikanischen Union
ምስል picture-alliance/AA/Palestinian Prime Ministry Office

#BringBackOurGirls የሚል ሐሽ ታግ የለጠፈ አንድ ዘለግ ያለ ፅሑፍ የተማሪዎቹ አጋቾች መንግሥት ነዉ ይላል።እገታዉን ከብሔር ጋር ያቆራኘዋልም።እንዲሕ ይነበባል

«አጋቹ መንግስታችን ሆይ ! ያለ ወንጀላቸው በማንነታቸው ምክንያት የታገቱ እህቶቻችንን ልቀቅልን አልን እንጅ 4 ተማሪዎች አዘጋጅተህ በአብን እና በአንዳንድ የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች ትብብር የተፈፀመ የአጋች ታጋች ዶክመንተሪ - ድራማ አዘጋጅልን አላልንህም ። የአብይ አስተዳደር እየሄደበት ያለው መንገድ ፍፁም ከመሳሳቱም በላይ ለታላቁ የአማራ ህዝብ ያለውን ከፍተኛ ጥላቻ እና ንቀት በግልፅ የሚያሳይ ነው ።»

Yeroo Gaarii በሚል ስም የሚጠሩ አስተያየት ሰጪ ደግሞ በፌስ ቡክ «የአማራ ህዝብ ምንም ባልተረጋገጠ ሁኔታ ይህን ያህል ስሜታዊ ሆኖ በነቂስ በመትመም ሌሎችን በመዝለፉ፣ዝቅ በማለት የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ አለበት።» የሮ ጋሪ ናቸዉ ይሕን ያሉት።

ተክለ፣ በበኩላቸዉ «ድራማ ተሠራ ግን በሚፈለገው ደረጃ አላለቀም፡፡ በደንብ ሲዘጋጅ ይቀርባል፡ ጠብቁ፡፡» ቀጠሮ ይሰጣሉ-የድራማዉ አዘጋጅ ይመስል።ከበደ ዳኜ የአማራ መስተዳድር ተቃዋሚ ፓርቲን ይወቅሳሉ።«የአብን የፖለቲካ ጫወታ እንደ ነበረ ይታወቃል» ብለዉ።

አዲያ ኡስማን፤ የኛን ዘገባ ነዉ የወቀሱት።«እናንተ ታዲያ የተጣራ መረጃ ከመንግስት አካል አጣርታችሁ አታቀርቡም፤ የፌስ ቡክ ወሬ ለቃቅማችሁ ከምታቀርቡ» ይላሉ።አዲያ ዑስማን ዘገባችንን መስማታቸዉ ያጠራጥራል።እኛ የዘገብነዉ የሁለቱን ታጋቾች ወላጆች አነጋግረን ነዉ።የሚመለከታቸዉን የመንግስት ባለስልጣናት አስተያየት ለማካተት ያደረግነዉ ሙከራ አለመሳካቱንም ጠቅሰናል።የፌስ ቡክ ወሬ ከለቃቀምን የለቅመዉ በዚሕ ዝግጅት ነዉ።የዝግጅቱ ዓላማ ስለሆነ።እንጂ አቶ ወይም ወይዘሮ አዲ አስተያየት በሰጡበት ዘገባ አንድም የፌስ ቡክ ገፅ አልጠቀስንም።ተግባባን?

ወደ ሰሶስተኛዉ ርዕሥ እንለፍ።ሥለ አፍሪቃ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ፣ ዕቅድና ዉሳኔ የተሰጡ አስተያየቶች ናችዉ።የመረጥናቸዉን እናሰማችሁ።

ስንታየው ገብረ ክርስቶስ፣« የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የአዲስ አበባ ነዋሪዋችን መንገድ እየዘጉ ከማሰቃየት ውጪ ምንም ፋይዳ የለውም። አንድም ፍሬ ነገር ጠብ አይልም።»

ከመሪዎቹ ጉባኤ ዋናዉ ርዕስ በአፍሪቃ ሕብረት አባል ሐገራት የሚደረጉ ግጭትችንና ጦርነቶችን ማስቆም የሚል ነበር።«የጠመንጃዉን ላንቃ ለመዝጋት ወይም ጠመንጃዉን ዝም ለማሰኘት» የሚል አማላይ ርዕስ ሰጥተዉታል።

አብዱል መሊክ ናስር፣ «ጥይት እንደ ሙዚቃ በሚሰማባት አፍሪካ ይሄ ቅዠት ነው» በማለት ያጣጥሉታል።በፌስ ቡክ በሰጡት አስተያየት።

ማሕደር ክፍሌ ደግሞ፣ መሪዎቹን እንዲሕ አሏቸዉ «ምንም መፍትሄ ኣያመጡም። ኣበል ከመብላት ና ከመዝናናት በስተቀር።»አልበርት ግርማ ግን፣ በፌስ ቡክ ለለጠፉት የጠመንጃና የብዕር ምስል «በጠመንጃ ሳይሆን በዕዉቀት እናሸንፋለን» የሚል ርዕስ ሰጥተዉታል።አንዋር አሕመድ የአልበርትን አስተያየት አልተቀበሉትም። «ውውውይ ህልማችው ጥሩ ነበር ግን ቀን ላይ ሰው ሳይተኛ ህልም ያያል እንዴ ?»  ይጠይቃሉ። እንጃ! 

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ